>

እኛ ኢትዮጲያዊያን ይህንን ሀገራዊ ህልውና አደጋን እንዴት ማክሸፍ ይቻለናል?? ( ወንድወሰን ተክሉ)

እኛ ኢትዮጲያዊያን ይህንን ሀገራዊ ህልውና አደጋን እንዴት ማክሸፍ ይቻለናል??
*** ወንድወሰን ተክሉ***

*…«ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢትዮጲያ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ምንጭ ናቸው- ጄኖሳይድ የመንግስታቸው አይነተኛ መገለጫ ነው» 
አቶ ልደቱ አያሌው
፠ በአቢይ አህመድ አመራር የኢትዮጲያ ሀገራዊ ህልውና የመፍረስ አደጋ ይጠብቀዋል
« ዛሬ  ኢትዮጲያ ትፈርሳለች ወይም የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባታል ብዬ ሳይሆን የምናገረው ለእኔ ኢትዮጲያ ፈርሳለች ብዬ የምገክጽበት ሁኔታ ላይ መሆናችንን ነው የማየው። ኢትዮጲያ እንደ ሀገር ያቌማት በሙሉ ፈራርሷል። የኢትዮጲያ ህዝብ እንደ አንድ ሀገር ህዝብ አንድነቱ የፈረሰበት ህዝብ ሆኗል። ሙሉ በሙሉ ለመፈራረስ የቀረንና የያዘን እጅግ በጣም ጥቂት ጉዳዬች ብቻ ናቸው ሀገሪቷን ይዞ የምናየው። በዚህ ሁኔታ ላይ የአቢይ በስልጣን ላይ መቀጠል ለሀገረ ኢትዮጲያ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ምንጭ በመሆን መፈራረሱን ያፋጥናል» በማለት የተናገረው  ከኢትዮጲያ ፖለቲካ መድረክ በጤና ምክንያት ለወራት ያህል ርቆና  ጠፍቶ የነበረውና ከ2014 አዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ ዳግመኛ ወደ መድረኩ ብቅ ያለው አቶ ልደቱ አያሌው ነው።
አቶ ልደቱ ከሁለት ሳምንት በፊት በእኛ በኢትዮጲያዊያን አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ «ብልጽግና ሆይ በእዲሱ ዓመት እጅህ ከምን..» በሚል አርእስት ስር በዚህ በያዝነው ወርሃ መስከረም 24 ይመሰረታል ተብሎ የተነገረውን ብልጽግና መራሹን መንግስት ግቡ ያደረገ መልእክትን ካስተላለፈ በኋላ ዳግመኛ ወደሚዲያ ብቅ በማለት መጀመሪያ ከኢትዮ360ሚዲያው ጋዜጠኛ ብርኩ ይባስ ጋር በሁለት ፕሮግራም የተላለፈ ቃለመጥይቅ ያደረገ ሲሆን አሁን ደግሞ በትናትናው እለት ከርእዮቱ ጋዜጠኛ ቴድሮስ ጸጋዬ ጋር ረዘም ያለ ቆይታ በማድረግ በወቅታዊው የሀገራችን ጉዳይ -በጄኖሳይድ ጉዳይ፣በጦርነቱ ጉዳይ፣በብሄራዊ ደህንነት ስጋትና በአቢይ ጉዳይ፣በሽግግር መንግስት ጉዳይ፣በብልጽግና ጉዳይ እና ….ወዘተ በመሳሰሉት ወሳኝ አርእስቶች ላይ ጥልቅ የሆነ የራሱን እይታና ምልክታን አስደምጦናል።
የዚህ መጣጥፍ ምንጭ በትናትናው እለት በርእዮት ሚዲያ ላይ ከሰጠው ቃለ ምልልስ ተጨምቆ የተወሰደ መሆኑን እየገለጽኩ ወደ ዝርዝሩ ማምራቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።
፠ 1ኛ – «ዶ/ር አቢይ አህመድ ለኢትዮጲያ ብሔራዊ ደህንነት ትልቅ የአደጋ ምንጭ እንጂ እንደመሪ ለሀገር እሴት አይደሉም»  አቶ ልደቱ
በርካታ ኢትዮጲያዊያን የሀገራቸው ኢትዮጲያ ሀገራዊ ህልውና በከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቌል ብለው ያምናሉ። የሀገሪቱን ህልውና በአደጋ ላይ በመጣል ደረጃ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ምንጭ አድርገው የሚገልጹት ግን ብሹዎቹ የወያኔ ድርጅታዊ ህልውና ፣ኦነግና የወያኔ ፈጠሩ  ሕገመንግስት እድርገው በመግለጽ በአቢይ የሚመራው የብልጽግና መንግስት ወያኔንና ኦነግን ጠራርጎና ደምስሶ በማጥፋት የሀገሪቷን ህልውና ይታደጋል በሚል እምነትና ተስፋ አቢይ አህመድን የመፍትሄ አካል አድርገው የሚመለከቱት ቁጥር ቀላል በማይባል ሁኔታ በርካታ ናቸው።
የአቶ ልደቱ የሀገረ ኢትዮጲያ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ምንጭ ከዚህ ከብዙኋኑ እይታና አረዳድ እጅግ በተቃረነ መልኩ አቢይ አህመድን ለሀገራዊ ችግሮቻችን የመፍትሄ አካል ከማድረግ ይልቅ እራሱ የአቢይ አህመድ በስልጣን ላይ መቆየት ለሀገረ ኢትዮጲያ ብሔራዊ ደህንነት ትልቁና ዋነኛው ስጋት ነው ብሎ ከእነ ነጥቦቹ በዝርዝር ሲያስቀምጥ ተደምጧል።
« ዶ/ር አቢይ አህመድ ስለወንበራቸው ሲሉ ማንኛውንም ነገር ከመፈጸም ወደኋላ የማይሉ። ለዚህች ሀገር መሪነት የተፈጠርኩ ብለው የሚያምኑና ይህንን ከፈጣሪ የተሰጣቸውን መለኮታዊ ስልጣንና ተልእኮን እሳቸው እስካሉ ድረስ ለማንም መሰጠታ የለበትም ብለው የሚያምኑ በመሆናቸው ለሀገሪቱ ችግር የፖለቲካ መፍትሄ ለማምጣት የማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን የማይችሉና አቅሙና ብቃቱም የሌላቸው ናቸው» በማለት የአቢይን የአደጋ ምንጭነት በአጽንኦት ሲገልጽ ተደምጧል።  «እኔ ይህቺን ሀገር ለመምራት የተፈጠርኩ ነኝ። ከእኔ በቀር ምንም ወደስልጣን መምጣት የለበትም የሚል ሰው ለሀገሪቱ  ችግር መፍትሄ አቅራቢነቱና እራሱም የመፍትሄ አካልነቱ ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎ በሚፈልገው የሀገራችን ጉዳይ ላይ አደጋ የደቀነ የችግር ምንጭ ነው» በማለት ይገልጽና «ዶ/ር አቢይ ስልጣን  ላይ እስከቀጠሉ ድረስ የብሔራዊ ደህንነታችን ሁኔታ በከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቆ ሀገሪቷ የመበታተን እጣፈንታ ትጎነጫለች» በማለት አቶ ልደቱ ይናገራል።
የአቢይ አህመድን የሶስት ዓመት አገዛዝ በአንክሮና በጥልቀት ለተከታተለ ሰው ይህንን የአቶ ልደቱን ሀሳብና ግምገማን ተጨባጭነት የሌለው መሰረተ ቢስ እይታ ብሎ ለማጣጣል የሚያስችል ማስረጃን ማቅረብ የሚሳነው ይሆንና የአቢይ አህመድን የሀገር ህልውና ስጋት ምንጭነት ማየትና መረዳት እንደሚቻል መናገር ይቻላል።
ሆኖም ሶስቱን ዓመት አቢያዊ አገዛዝን  ተመልክቶ የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ምንጭ መሆኑን ተረድቶ ከተቀበለው ህዝብ ይልቅ ይህንን ሁሉ ተጨባጭ ተግባሮችን እያየ ግን አቢይ አህመድ የመፍትሄ አካል ነው ብሎ የሚያምነው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥሩ መመናመን የሚገባውን ያህል ያልተመናመነ መሆን ሀገራዊ የመፍረስ አደጋን ተጨባጭ በማድረጉ ደረጃ ላይ የአንባሳውን ድርሻ የሚጫወት ነው ብሎ ይህ ጸሃፊ ያምናል።
ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትንሽ ምሳሌያዊ ማብራሪያ ይበልጥ ለማሳየት ልሞክር። ከ20ና ከ30ዓመት በፊት በኤች አይ ቪ H.I.V የተያዙና የሚያዙ ሰዎች ከ99% በላይ የሆኑት በቫይረሱ የመሞት እጣፈንታን የተደቀነባቸው ነበሩ። ይህ የሆነበት ምክንያት 1ኛ-እድሜ ማራዘሚያው አንቲ ሪትሮ ቫየራል መድሃኒት በስፋትና በነጻ ስላልተሰራጨና 2ኛው- የኤድስ ቫይረስ ፖዘቲቭ የሚባሉት/የተባሉት አብዛኞቹ (በተለይ በኢትዮጲያ) በሽታውን ደብቀው እድሜ ማራዘሚያውን (ማግኘት የሚችሉትና ማግኘት የቻሉት) መድሃኒት መጠቀም ባለመቻላቸው ምክንያት በርካቶች ተግፈዋል። እድሜ ማራዘሚያውን መድሃኒት ለማግኘት ፖዘቲቭ የተባለ ሰው የያዘውን ህመም ሳይደብቅ በግልጽ በመንገርና በማሳወቅ የሚጀምር ሲሆን ያኔም መድሃኒቱን መቀበል ይጀምርና ህይወቱን ከመቀጨት ማትረፍ ይቻለዋል። በሌላ በኩል ግን በህመሙ መያዙን የደበቀ ያላመነው መድሃኒቱን አጥቶ ለሞት ሲዳረግ ይታያል።  የኢትዮጲያ ህዝብ የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ምንጭ የሆነውን አቢይን እንደ የአደጋው መፍትሄ አካል አድርጎ መመልከቱን እና መደገፉን እስካላቆመ ድረስ በሀገሪቷን አፍራሹ አቢይ አመራር እጅ አይኑ እያየ የሚፈራርስበት ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ እናያለን።
የሀገራችንን ህልውናን በማፈራረስ ደረጃ የቫይረሱን ሚናን የያዘውን አቢይን ሀገር አፍራሽ ቫይረስነቱን የኢትዮጲያ ህዝብ አለመቀበልና አለማወቅ ማለት ህዝባችን አውቆም ሆነ ሳያውቅ ለመፈራረስ ተባባሪ ሆኖ እናያለን። የአቢይን ሀገር አፍራሽ ቫይረስነት ማወቅና እውቅና ሰጥቶ በዚያ ደረጃ ማስተናገድ ማለት የመፍትሄያችንን ቁጥር አንድና የመጀመሪያውን ወሳኝ ተግባር መፈጸም ማለት ነው።
አዎን አቢይ ሀገራዊ ህልውናችንን የሚያፈርስ ጸረ ሀገርና ጸረ ህዝብ ቫይረስ ነው!!
፠ 2ኛ- «ጄኖሳይድ የዚህ የአቢይ መራሹ የብልጽግና ስርዓት አይነተኛ መገለጫ ነው»    አቶ ልደቱ አያሌው
«በኢትዮጲያ ውስጥ የጄኖሳይድ ወንጀል ተፈጽሟል -ዛሬም በመፈጸም ላይ ይገኛል። በኦሮሚያ ወለጋ፣በመተከል፣በትግራይና ዛሬ ደግሞ በሰሜን ጎንደርና በሰሜን ወሎ የጄኖሳይድ ወንጀል በግልጽና በስፋት እየተፈጸመ መሆኑ ግልጽ ነው። የዲ/ ዳንኤል ክብረትን እጅግ አደገኛ የሆነውን ጄኖሳይድ የቅስቀሳ ቃል በመስማት ብቻ የጄኖሳይድ ወንጀል የስርዓቱ አይነተኛ መግለጫ መሆኑንና የስርዓቱን የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱን ማየት ይቻላል። ምክንያቱም የዲ/ ዳንኤል ክብረት ንግግር  የአንድ ግለሰብ ንግግር ሳይሆን እንደ የጠ/ምሩ አማካሪ ባለስልጣንነቱ የተናገረውም ጄኖሳይድ ቀስቃሽ ንግግር በመንግስታዊ የመገናኛ ብዙሃን እንዲተላለፍ መደረግን ስንመለከት ጉዳዩ ግላዊ ንግግር ሳይሆን መንግስታዊ ዓላማና አቌም መሆኑን ያሳየናል» በማለት በቅርቡ በዳንኤል ክብረት የተላለፈውን ጸያፍ ቃልና ላለፉት ሶስት ዓመታት በበርካታ የኢትዮጲያ ክፍል የተፈጸመውን መጠነ ሰፊ ዘርና እምነት ተኮር ጭፍጨፋን በመጥቀስ ይህ ስርዓት የጄኖሳይድ መንግስት ነው ሲል ይናገራል።
በርካታና ንቁ የሆኑ ኢትዮጲያዊያን በተለይ የአማራ ተወላጆች የሆኑ በህዝባችን ላይ መጠነ ሰፊ የዘርማጥፋት ወንጀል ወይም ጄኖሳይድ እየተፈጸመ ነው እያሉ ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል።  አቶ ልደቱ ይህንን ኢኮ በማድረግ አስረግጦ ሲገልጽ የዳንኤል ክብረትን ንግግር ለምሳሌነት ጠቅሷል።  እንደ አቶ ልደቱ አረዳድ ዳንኤል ክብረት በትግራይ ሕዝብ ላይ ያነሳሳ የጄኖሳይድ ጥሪ መተላለፉን የሚያምን ቢሆንም የዳንኤልን ማስተባበያን በመቀበል አባባሉ ለወያኔ ብቻ የተባለ ነው ብለን ብንቀበል እንኴን ከጄኖሳይድነት ሊወጣ አይችልም ሲላ ያብራራል።
አቶ ልደቱ የዳንኤል ክብረትን በወያኔ ላይ ያስተላለፈውን «ከምድረ ገጽ ጠራርጎ ማጥፋት ነው። እነሱን ብቻ ሳይሆን የእነሱን አይነት አስተሳሰብን የሚያስቡትን በሙሉ ምድሪቷ ዳግመኛ እንዳታበቅላቸው አድርጎ ከምድረገጽ ማጥፋት ነው …» የሚለውን የዳንኤልን ንግግር የስርዓቱ ጄኖሳይዳዊ ባህሪ መገለጫ ድርጊቱ ሀገሪቱ ከተዘፈቀችበት ዘርፈ ብዙ ችግር አኴያ ከድጡ ወደ ማጡ የሚያስገባን አደጋ ጠሪነቱ የሚወገዝ ወይም የሚኮነን ሀሳብ ነው ይልና አንድን ሰው ወይም ቡድን በሚያራምደው የተለየ ሀሳብ ምክንያት ከምድረገጽ ማጥፋት አለብን ማለት የሚቻል ብቻ ሳይሆን ጄኖሳይዳዊ የሆነ የማይገባ ነው በማለት ወያኔ ከምድረገጽ መጥፋት የለበትም ብሏል።
ይህ የእቶ ልደቱ የወያኔ በሚያራምደው አቌም ምክንያት  ከምድረገጽ መጥፋት አለበት ያለውን የዳንኤል ክብረትን ሀሳብ መቃወምና ብሎም ፍጹም ተገቢ አይደለም ብሎ መኮነን ከአብዛኛው ኢትዮጲያዊ ሀሳብና ፍላጎት ጋር የሚለተም መሆኑ እሙን ነው።
ከትግራይ መለስ ያለው አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ወያኔ ከምድረገጽ መጥፋት አለባት ባይ ከመሆኑ የተነሳ ዳንኤልን ለመካለከል የተኮለኮለው ሰው  ቁጥር በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ሁለቱም ዘንድ ኮንክሪት የሆነ ምክንያት እንዳላቸው ቢታይም ነገሩን በጥልቀት ከተመለከትን እና ለሀገራችን መፍትሄ የምንፈልግ ከሆነ የአቶ ልደቱ ሀሳብና እይታ ከህግ አንጻር ብቻ ሳይሆን ከስነተፈጥሮ አንጻርና ከሞራል አኴያ ሚዛን የሚደፋ መሆኑን መካድም ሆነ መሸሽ የሚቻል አይደለም።
ሆኖም በአቶ ጌታቸው ረዳ ሂሳብ እናወራርዳለን የተባለውና ከ11ዞኖቹ አምስት ያህል ዞኖቹ በወያኔ የተወረረበትና ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራን እያስተናገደ ያለው የአማራ ሕዝብ በወያኔ ከምድረገጽ መጥፋት ላይ የሚያንገራግር አይደለም።
እንግዲህ ይህ አመለካከትም ነው እንደ ትልቅ ሀገር አፍራሽ ተግዳሮት ሆኖ የሀገረ ኢትዮጲያን ህልውና ከመጠነ ሰፊው የአቢይ አህመድ አፍራሽ ሚና ጋር ተደምሮ አደጋ  ላይ ሲጥለን ማስተዋል ይቻላል።
ወደ ጄኖሳይዱ ጉዳይ ስንመለስ በእርግጥ ወያኔ እጅግ በጣም የምትፈራ የምትጠላና ከምድረገጽ እንድትጠፋ የምትፈለግ ድርጅት ብትሆንም እንደ ዳንኤል ክብረት እወጃ  ተግባራዊ ይደረግ ቢባል – ማለትም ወያኔና የወያኔን ሀሳብ የሚያራምዱ በሙሉ ከምድረገጽ መጥፋት አለባቸው – የሚለውን መተግበር ማለት ከ780ሺህ በላይ የህወሃት አባላትን ጨምሮ በብአዴን በኦህዴድና በብልጽግና ውስጥ ያሉትን የህወሃትን ሀሳብ አራማጆችን በሙሉ  መጨፍጨፍን ያስገድዳልና ይህንን ተፈጻሚ ማድረግ ማለት አቶ ልደቱ እንዳለው እርምጃው ሙሉ በሙሉ ጄኖሳይዳዊ እርምጃ  አይሆንም ብሎ መሟገት የሚቻል አይደለም።
የመጥፎ ሀሳብ ምንጭና ባለቤት የሆነን ቡድን ኋይልና ግለሰብን ከምድረገጽ በማጥፋት ሳይሆን ማሸነፍ የሚቻለው ያንን አፍራሽ አስተሳሰብን የሚያሸንፍ ሀሳብ በማፍለቅ ማሸነፍና ሀሳባቸው ተቀባይነት የሌለው ሀሳብ ማድረግ ይቻላል የሚል አማራጫዊ መፍትሄን አቶ ልደቱ ጠቁሟል።
፠ 3ኛ-  « ዛሬ የሽግግር መንግስት ከምንግዜውም በላይ በወሳኝነት ለሀገራችን እጅግ የሚያስፈልጋት የመፍትሄ መንገድ ነው»  አቶ ልደቱ አያሌው
እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በአሸናፊነት የሚደመደም ጦርነት ባለመሆኑ ብቸኛው የመፍትሄ መንገድ ቁጭ ብሎ በመነጋገርና በመወያየት አንድ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት በማቌቌም ብቻ ነው ይህንን የተደቀነብንን አደጋ እምንወጣው እንጂ  በጦርነት ችግሩን ከማባባስ በስተቀር መፍታት አይቻልም በሚለው በአቶ ልደቱ ሀሳብ የማይስማማ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል እንዳለ ሁሉ በሽግግር መንግስት አስፈላጊነት የሚያምነውም ቁጥር ቀላል አይደለም።  ልዩነቱ የአቶ ልደቱ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት አስፈላጊነትን ዛሬ ላለው የእርሰበርስ እልቂቴዊ ጦርነት መውጪያ አድርጎ በማቅረብ ህወሃትን ያካተተ መሆን አለበት ሲል ሌሎች ደግሞ በሽግግር መንግስት አስፈላጊነት አምነው ወያኔን ያላካተተ ማለታቸው ነው።
ይህ በአቶ ልደቱ የቀረበው የሽግግር መንግስት አስፈላጊነት ዛሬ የዛሬ አጀንዳ ሳይሆን ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊት ቀርቦ የነበረና የይዘት ማሻሻያ ተደርጎለት በድጋሚ የቀረበ ሆኖ እናገኛለን።
ከሶስት ዓመት በፊት አቶ ልደቱ  ባረቀቀው የሽግግር መንግስት ቻርተራዊ ሰነድ በአቢይ አህመድ የሚመራ ብሎ ብሎ ያቀረበ ሲሆን ዛሬ ግን ለወጥ አድርጎት በሚመሰረተው የሽግግር መንግስት የብልጽግና ሚና የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ በአቢይ መሪነት የሚመሰረት ሳይሆን ብልጽግና ከሌሎች ባለድርሻ አካሎች ጋር እኩል ሚና በሚኖረው ሁኔታና አቢይን በመሪነት ባላቀፈ መሆን አለበት ብሎ ሀሳቡን አሻሽሎ አቅርቧል።
አቢይ የሽግግር መንግስቱን መሪነት አይገባውም እንዲል ያደረገው የሰውዬው ብቃት ማነስና ብሎም የሶስት ዓመቱን አገዛዛዊ ውጤት በመገምገም የሀሳብ ለውጥ እንዳደረገ ይገልጻል።  እውነታው ሀገሪቷ የሽግግር መንግስት የሚያስፈልጋት መሆንና ብሎም ከአቢይ አመራር መገላገልን በወሳኝነት የምትፈግ – አሊያም የሚያስፈልጋት መሆኑ ላይ ነው።
ለዚህ የመፍትሄ ሀሳብ ደግሞ ትልቁ ተጋዳሮትና እንቅፋት ደግሞ እራሱ አቢይ ብልጽግና እና ብሎም በአቢይ ላይ የተሳሳተ አረዳድና ተስፋን በያዘው ማሕበረሰብ በኩል መሆኑ የመፍትሄውን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ብርቱ የትግል ጥረት የሚጠይቅ ሆኖ መታየቱ ነው።
መጪው መስከረም 24 ወሳኝ ታሪካዊ እለት ነው የሚለን አቶ ልደቱ ብልጽግና ከአቢይ ውጪ ሌላ አዲስ መሪ ቢመርጥ መፍትሄዎቻችንን ለማግኘት በር ይከፈት ይሆናል በሚል ተስፋ ፓርቲው አዲስ መሪ መምረጥ አለበት ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ብልጽግና የሚባለው የኢህአዴግ ክፍያና የወያኔ ወራሽ ከአቢይ አህመድ ውጪ መኖር እችላለሁ ብሎ በማመን  አዲስ መሪ ይመርጣል ተብሎ ባይጠበቅም- ይህንንም ሁኔታ አቶ ልደቱም የሚያውቀው መሆኑን ቢገልጽም ከመፍትሄነት አኴያ ግን ቢቀበለውም ባይቀበለውም ትክክለኛ ጥቆማ ስለሆነ ብልጽግና አዲስ መሪ ይምረጥ ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፌያለሁ ከሚለን አቶ ልደቱ ሀሳብ ጋር ይህ ጸሀፊ ፈጽሞ አይስማማም። ምክንያቱም በአደጋ ላይ ያለችን ሀገር ህልውናን ለመታደግ የመፍትሄ  ውሳኔዎችን አይደለም ሊተግብር ይቅርና እራሱ የችግሩ አስኴል የሆነን ኋይል እባክህ አድነን ብሎ መማጸን አቅመቢስነትን ባዶነትንና ከአንተ በስተቀር ሀገሪቷን ማዳን የሚችል ኋይልም ሆነ ህዝብ የለምን መልእክት ከማስተጋባቱም በላይ ሀገሪቷን ለማዳን መደረግ ከሚገባው ወሳኝ ትግል እራሳን ማግለልንም ያመላክታልና እንደ እኔ እንደ እኔ የብልጽግና ተባባሪ ያለመሆንን ሙሉ በሙሉ ባረጋገጥኩበት ሁኔታ ህዝቡን ያሳተፈ መጠነ ሰፊ ንቅናቄን ለማቀጣጠል መደረግ ወደላበት ተግባር ላይ መሰማራትን ስራዬ ተብሎ ሊያዝ ይገባል ብዬ አምናለሁ።
ይህ ማለት ከብልጽግና ባሻገር  ያለን ኋይል ህዝብንና ቡድኖችን ማእከሉ ያደረገና እነዚህን ኋይሎች በማስተባበር ላይ ያተኮረ ተግባራዊ ስራ ውስጥ ተገብቶ መፍትሄዎቹን በራሳችን እጅ ለማምጣት ወሳኙን ስራና ትግልን ማካሄድ ይመረጣል እንጂ  እንደ አቶ ልደቱ ቅንጣት የምክር ሀሳብ ለማይቀበለው ብልጽግና የመፍትሄ ህሳብ በማቅረብ ቢፈጽመው እሰየው ባይፈጽመውም እኔ ድርሻዬን ተወጥቻለሁ ብሎ መቀመጥን ብቸኛ መንገድ ነው ብዬ ፈጽሞ አልቀበልም።
የሀገሪቱን ችግሮችና የችግሮቹን ምንጭ በመጥቀስ ደረጃ አቶ ልደቱ ያቀረባቸው ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ባይኖረኝም ከመፍትሄ አካያ ግን ብልጽግናን መፈትሄውን እንዲፈጽም (አቢይን ከስልጣን አውርዶ አዲስ መሪ በመምረጥ በር እንዲከፍት ) ከመጠበቅ ይልቅ በራሳችን መንገድ መፈጸም በሚቻለን እና በምንችለው ላይ ትኩረት አድርጎ መንታገልን እንደ አማራጭ መፍትሄነት ለመቀበል እችላለው።
የአቶ ልደቱ አያሌውን እይታ ማጋራት ማለት በእይታው ሙሉ በሙሉ የማመንና የመቀበልን ጉዳይ ለማንጸባረቅ ሳይሆን እንደ አንድ በሳል ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ  ያለውን ሀገራዊ ሀሳብና ምክረ ሀሳቦቹን ማሰራጨትን ጠቃሚነትን በመምረጥ መሆኑን እያስገነዘብኩ የተስማማሁባቸው በርካታ ሀሳቦች እንዳሉት ሁሉ ያልተስማማሁባቸውም ሀሳቦን ያቀፈ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ።
ከሁሉ በላይ የተስማማሁበት ሀሳቡ አቢይ አህመድ የኢትዮጲያ ብሔራው ደህንነት አደጋ ምንጭ ነው የሚለው ከእነዝርዝር አመክኒዮቶቹ ጋር ሙሉ በሙሉ የተስማማሁበት ትክክለኛ ግምገማ  መሆኑን እገለጻለሁ።
Filed in: Amharic