>
5:26 pm - Wednesday September 17, 7687

የተረሳው የድንበር ውዝግብ ..!!! (አማረ መላኩ)

የተረሳው የድንበር ውዝግብ ..!!!

አማረ መላኩ

 

     የአራዳ ልጆች ደረጃዋን የጠበቀች  ጥቅስ ሲጠቅሱ (ወይም ለትውልድ እና ለታሪክ ሲያስቀምጡ ምናልባት ነገሩን አጦዝከው አትበሉኝ እንጂ ሲያወርሱ! አሪፍም የራሱ የሆነ ታሪክ አለው ና ነው)  “የጊዜ ግልባጭ እግር ራስ ያካል ‘ ይላሉ። አባባሉ ሁኔታዎች ሁሉ በብርሃን ፍጥነት  ሲገለባበጡ የሚሆነውን እና የሚፈጠረውን ክስተት ለማመላከት ነው እንጂ ፣ ተአምር ቢፈጠር እንኳን እግር ከተፈጠረለት አላማ አፈንግጦ ወይም ተንጠራርቶ ፣ ራስ ሊያክ ከቶውንም አይችልም ።
       አዎን ያለ እና ምናልባትም የሚኖር የሚመስለን ነገር እንደቀልድ ተለውጦ ስናየው” የጊዜ ግልባጭ እግር ራስ ያካል ‘ ስንል ለመቀኘት እንገደዳለን።
     እናም ነገሮች አብዝተው የተገለባበጡባት የብልጽግናዋ ኢትዮጵያ ፣በእብሪት አብጣ የወረረቻትን ሱዳንን እየለመነች ትገኛለች።  ልመና ብቻም አይደል የሚያማልዷትን አገሮች ፍለጋ ላይ. ናት እና ፉተታ የሚመስል ነገር ግን ጥሬ ሃቅ የያዘውን አባባል እዚህ እና አሁን ለመጥቀስ ተገደድን።
      እነሆም “ኢትዮጵያ ፍቅር ያሸንፋል” እያለች የጠብ መንገድን ለመዝጋት ብትሞክርም ጠላቶቿ ግን የሚሰሙ አይነት አይደሉም ።  እነሱ የሀይል መንገድ ያዋጣል እያሉ ሌትተቀን የጥል ዜማ ያቀነቅናሉ የእኛዎቹ ተቃራኒውን አሁን ድረስ ተስፋ ያደርጋሉ።
     በእርግጥ ፣ በኃይል የተያዘ ሰፊ ለም መሬት በጉልበት ከማስመለስ ይልቅ ልመና እና አቤቱታ ማቅረቡ ነገሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ያደርጋል ። የሚለው ገራገሩ የብልጥግና የግጭት እና ድንበር አፈታት ፓሊሲ መሬት ላይ ያለውን እውነት ፣ በአንዳች ስንዝር እንኳን መለወጥ ባይችልም፣ ከአስር ወር በላይ ለማደናገሪያነት እያገለገለ ግን አለ። ከአንዳንድ ሁኔታዎች ተነስተን ማደናገሩ  የሚቀጥል ይመስላል ስንል መናገር እንችላለን ። ከእዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተማጽኖ እና ልመናዎችንም መስማት እንደምንቀጥል መናገር ድፍረት አይሆንብንም።
     እናም ዲና ሙፍቲ በአገኘው አጋጣሚ መገናኛ ብዙሀንን እየጠራ ..”ሱዳንን አስታግሱልን የጎረቤት ሱዳን ድርጊት ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሰ ነው። ከአፍሪካዊ መርሆ እና ስምምነት ውጭ ድንበሮችን በሀይል ለመቀየር የሚደረግ የጉልበት ድርጊት ነው። ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሀይ ሊል ይገባል” እና ወዘተ እያለ ቢማፀንም ሰሚ ማግኘት አልቻለም።
     ደመቀ መኮንንም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችን ከአንድም ሁለት ሶስቴ ሰብስቦ በፍሬም በይዘትም ተመሳሳይነት ያለው ተማጽኖ ቢያቀርብም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው አጋር ለመሆን ቃል የገቡለት ወዳጅ ሀገራትን ማግኘት የቻለ አይመስልም። ትንሽ ቀልብ ቆንጥጦ ኢፍትሃዊነትን ለዓለም ሰላም ሲባል በጋራ ለመታገል የሚያስችል የጋራ አጀንዳ ለመሆን እንኳን ያልበቃ ጉትጎታ እና ውትወታ ሆኖ ነው የቀረው። የሀገራችን የዲፕሎማሲ ክሽፈት አንዱ ማሳያም ነው ማለት ይቻላል።
     በእዚሁ እርባና ቢስ ጉትጎታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ..”አሜሪካ የሱዳን ወረራን እያየች እንዳላየች ሆና አልፋለች። በግልጽ ወረራውን ማውገዝ ነበረባት “ሲል ከዲፕሎማቲክ  ቋንቋ ባፈነገጠ መልኩ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን አዲስ አበባ መጥቶ በተገናኘበት ወቅት ተናግሮት ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ይሄም ተግሳጽ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ የለም። ምናልባት አምባሳደሩ የክቡር ሚስትሩን አቤቱታ የሚያደምጥ እየመሰለ ከግጭቱ ሀገሩ አሜሪካ የምታተርፍበትን አንዳች ቀመር እያሰላ እንደነበር መጠርጠር አይከፋም። በግጭቶች መነገድ እና ብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር መሞከር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ተብሎ ይታመናል እና ነው።
       በሱዳን እና ኢትዮጵያ የድንበር ውዝግብ ላይ ዓለም የያዘው አቋም ወይም በዝምታ የሚሆነውን የመመልከት ስልት፣ አብዝቶ ተጎጅውን ሀገር ሳይሆን ጎጂውን የሚሸልም አይን ያወጣ ድጋፍ መሆኑ ግልጽ ነው። እንዲህ አይነቱ እውነትን በቁሟ የመቅበር ነገር ለዓለም ሰላም በተለይም ለምስራቅ አፍሪካ አለመረጋጋት ጠንቅ በመሆኑ መወገዝ ነው ያለበት። በዝምታ ለተሸበበው የዓለም ማህበረሰብ ምላሽ ፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ደካማ እንቅስቃሴ ወይም ለድንበር ውዝግቡ የሰጡት ትኩረት አነስተኛ መሆን የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን  መዘንጋት የለብንም። እንደ አገር የገባንባቸው መልከ ብዙ ቅርቃሮች የኢትዮጵያን ተሰሚነት እና ተፈላጊነት በዜሮ አባዝቶ ማውረዱም ሌላው ችግር ነው።
      የእኛ ዲፕሎማቶች ሀገራችን ኢትዮጵያ የተሰሚነት እና የተፈላጊነት የስበት ማእከል እንደነበረች ሆና  መቀጠል የምትችለው ፣ እንደ አገር እጄ ላይ ባለው አስተማማኝ ሃይል እና ጥንካሬ ልክ መሆኑን የዘነጉት ይመስላል ። አቅምህን በራስህ የውስጥ ችግር ጨርሰህ ከተዳከምክ በሗላ፣ የሚያደምጥህ አይደለም ዞር ብሎ የሚያይህ ወዳጅ ሀገር ማግኘት የሚቻል አይደለም።
     ማንም እና በፈለከው መጠን እውነትህን የሚረዳው ባለህ የማድረግ አቅም ነው። በኢኮኖሚውም በወታደራዊው እና በዲፕሎማሲው ጉልበትህ ልክ ተገቢውን ክብር እና ስፍራ ማንም ሳይወድ በግድ ይሰጥሃል። ” ከሌለህ የለህም “የሚለው ብሂል ለግለሰብም እንደ ሃገር ለሃገርም እንደሚሰራ እዚህ ጋር የሚገባን ይመስለኛል።
    ከእዚህ አንጻር ዓለም በተለይም ልእለ ሀያልዋ አሜሪካ መጀመሪያ ብሄራዊ ጥቅሟን ነውና የምታስቀድመው፣ ኢትዮጵያ ለያዘችው እውነት ደንታ የላትም። ምናልባትም ልዩነታችሁን በሰላማዊ መንገድ ፍቱት ስትል ገለልተኛ ሆና ለመታየት ትሞክር ይሆናል። ይሄ ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ እውነትን ፊትለፊት ከማውጣት እና ከመጋፈጥ ይልቅ ሸፋፍኖ የማትረፍ ስልት ነው። ከሁለቱም ወገኖች ያለ ማጣት ይልቁንም ደብል ትርፍ የማፈስ አይነተኛ ዘዴ ነው።
    አሜሪካ ከብሄራዊ ጥቅሟ አንጻር የሀይል ሚዛኑ ወደ አጋደለበት ነው ፊቷን የምታዞረው ካልን ዘንዳ፣ የደመቀ እና ባልደረቦቹ ጩኸት እና ልመና አንዳንዴም ተግሳጽ የታከለበት ቁጣ ከበቀቀን ጩኸትነት አያልፍም ማለት ነው። በተግባርም የሆነው ይሄ እና ይሄን መሰሉ ዝምታ ያረበበበት መልስ ነው። ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዝምታ ማን እንዳተረፈ እና የተሻለ ይዞ እንደወጣ የታዘብነው በመሆኑ እዚህ መድገም አያስፈልግም ።
      ምስጋና ለአበልጣጊው ፓርቲ ይሁን እና፣ ዛሬ ኢትዮጵያ በራሷ የውስጥ ችግር ተተብትባ ውል እስሩ እንደጠፋበት ጀልባ በወጀብ ተመታ እዚያ እና እዚህ ስትላተም፣ ይበልጥኑ በእርስ በርስ ጦርነት በመቶሺዎች ልጆቿን እንደ ቅጠል የምታረግፍ፣ ይህ አልበቃ ብሏት የጎረቤት አገር ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ ወታደሮችን በመቅጠር በሉዓላዊ ግዛቷ አሰማርታ የገዛ ዜጎቿን በጅምላ የምታስገድል፣ ሴቶችን በቡድን የምታስደፍር እና ርሃብን የጦርነት አካል ያደረገች ኮስማና ሀገር ሆናለች። የክፋቱ  ብዛት ያስገረማቸው እንዳንዶች” የጉድ ሀገር” ቢሉ የሚደንቅ አይመስለኝም።
      በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲህ አይነቱ የወደቀ የሞራል ልእልናን  የተላበሰ ደካማ መንግስት”የተዋረደ እና የተናቀ” ይሆን እንደሆን እንጂ፣ ከማንም ክብር እና ሞገስ ሊያገኝ ከቶውንም አይችልም ።እውነታውን ያስረግጥልን ዘንድ በእዚህ ወቅት እና አሁን የኢትዮጵያ ወዳጅ አገር ማን ነው? ብለን ስንጠይቅ “ኤርትራ” የሚል መልስ ነው የምናገኘው። የኤርትራ መንግስት በተለያዩ ማእቀቦች ኢኮኖሚው የደቀቀ በአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ላለፍት ሰላሳ ዓመታት እየተመራ ያለ፣ ከዓለም ተነጥሎ ብቻውን በመቆሙ “የምስራቅ አፍሪካው ሰሜን ኮርያ” የሚል ስያሜ ያተረፈ ስርዓት እና መንግስት ነው። በእርግጥ ከአለፍት ሶስት ዓመታት ወዲህ ከለውጥ ሃይሉ የብልጥግና መንግስት ጋር በመወዳጀቱ የጫጉላ ሽር ሽር ላይ ነው ያለው!…
     ወደ የድንበሩ ውዝግብ ጉዳይ ስንመለስ ኢትዮጵያ የሃይል ሰለባ መሆኗ እሙን ነው። የባእድ ሃይል ድንበሯን ተዳፍሮ ሰፊ መሬቶችን ተቆጣጥሮ ይገኛል። የምስራቅ አፍሪካ ነባራዊ ሁኔታ ከስር ከመሰረቱ በመለዋወጡ እውነት የያዘችውን ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት ነው። አጥፊውን የመሸለሙ ኢፍትሃዊ አሰራር ወደፊትም በነበረበት እንደሚዘልቅ መገመት ቀላል ነው።
     ነገር ግን በዲፕሎማሲው ረገድ የገዘፈ ስም እና የግንኙነት መስመር የነበራት ኢትዮጵያ ፣ እንዴት የሱዳንን የእብሪት ወረራ ትክክለኛ መልክ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቅ ተሳናት?..ቢያንስ የገለልተኝነት መርህን ለሚከተሉ አንዳንድ አገራት ነባራዊውን ሁኔታ አስረድቶ ከፍትህ እና ርትህ ጎን የመቆም የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው የሚያግባባ ዲፕሎማት እንዴት ጠፋ?..ስንል የመንግሥትን ዲፕሎማሲያዊ የብቃት ደረጃ ለመሞገት እና ለማጠየቅ እንገደዳለን። አንዳች ስሜት ሰጥቶት የሚመልስልን ክቡር ባለስልጣን ከአገኘን!..
     የብልጥግና መንግሥት በእፍጢማቸው ከደፋቸው መንግስታዊ ተቋማት መሃል የውጭ ግንኙነት ዘርፍ አንዱ እና ምናልባት ዋናው ነው። በሪፎርም ሰበብ ዳግም እንዳያንሰራራ ተደርጎ በመዳከም ላይ የሚገኘው የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲ ፣ ኢትዮጵያ በውጭ አገራት ካሏት ኢምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች መሃል ግማሽ ያህሉን በመዝጋት ተልእኮአቸው እንደሚጠናቀቅ መወሰኑ አይዘነጋም። ይህ ውሳኔ የአቅም ማነስ የወለደው ችግር ብቻ አይመስለንም። ይበልጥኑም የራዕይ አልባ መሪዎቻችን ከዓለም የመቀነስ ውጤት ነው። በአናቱም ሀገሪቷን ከተቀረው ዓለም ነጥሎ ብቻዋን የሚያቆማት የአላዋቂዎች ድፍረት የታከለበት ውሳኔ ነው።
     ቀደም ሲል ደጋግመን ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው፣ ግራ ገብቶት ዜጎችንም ግራ እያጋባ እና እያወናበደ የዘለቀው የብልጽግና የውጭ ግንኙነት ፓሊሲ፣ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ የትኩረት ማእከልነት ነቅሎ ሱዳንን እስከመትከል ደርሷል። የቀድሞው ወዳጅ አገር አሜሪካ ወደ ሀምሳ ቢሊዮን ዶላር ኢንቬስት አድርጋ ሱዳንን የአካባቢው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማሳያ እና የስበት ማዕከል እንድትሆን የወጠነችውን ፕሮጀክት ልብ ይሏል?..
       ሱዳን እድል እና አጋጣሚ ቤቷ ድረስ ጠቅልሎ ያመጣላትን ምቹ ሁኔታ በተገቢው መልኩ በመጠቀም የመጫወቻ ሜዳውን ተቆጣጥሮ ለመቆየት ሌት ተቀን እየሰራች ነው። በእዚህም ነጥብ እያስቆጠረች ያለች ነው የምትመስለው። ከሃያልዋ አሜሪካም ሆነ ወዳጆችዋ ከሆኑት አረብ አገራት ያገኘችውን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እና የተለየ ትኩረት ከመልካም “በረከትነቱ” በዘለለ፣ ኢትዮጵያን በዓለም እና በአካባቢያዊ መድረኮች ለማሳጣት እየተጠቀመችበት ነው።
     በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብደላ ሃምዶክ”ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ እንዳይረጋጋ እየሰራች ነው” ሲል እስከ መክሰስ የደረሰ ድፍረቱን አሳይቷል። የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ መሪ ጀነራል አልቡርሃኒ ለተደጋጋሚ ጊዜያት በትእቢት ታውሮ..”ከኢትዮጵያ ተጨማሪ የሚቀረን መሬት አለ። ገና እናስመልሳለን ፣አሁንም ወደፊት ..ወደ መሬታችን ..” እያለ ወታደሮቹን ለተጨማሪ ወረራ ሲያነሳሳ ተደምጧል።
     ከከሸፈው የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በሗላ እንኳን “የሱዳንን ጦር የትኛውም የጎረቤት አገር ሃይል ሊያሸንፈው እንደማይችል። ጦሩ ማንንም ለመግጠም ዝግጁ እንደሆነ” በአገሪቱ ሬድዮ ጣቢያ ኢትዮጵያ እንድትሰማው ጮክ ብሎ ሲናገር ተደምጧል። ድንፋታ እና ለያዥ ለገናዥ ማስቸገሩ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
      በትናንትናው እለትም አንድ የሱዳን ጀነራል”በአልፋሽቃ በኩል ኢትዮጵያ የሞከረችብንን የማጥቃት ሙከራ ተከላክለን መልሰናል። በቀጣይነትም ጥቃቶችን እንደ አመጣጣቸው ለመመለስ ዝግጁ ነን” የሚል ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቶ ነበር። እንዲህ አይነቶቹ በተጠና እና ተከታታይነት በአለው መልኩ የሚወጡ መግለጫዎች እንዳንዶች እንደሚሉት”የውስጥ ችግሮችን እና አለመረጋጋቶችን እንደማስቀየሻ ዘዴ ለመጠቀም ነው” ከሚል መላ ምት በዘለለ፣ ለኢትዮጵያ የተላከ የግጭት መልእክትም ይመስላል ።
     ዝቅ ሲል”ጠብ ያለሽ በዳቦ ..”አይነት የልጆች ጨዋታ። ከፍ ሲል ደግሞ “ውረድ እንውረድ ..!” የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ያጀበው ተጨማሪ ትንኮሳ ነው ማለት ይቻላል።
      ሀገራችን “የጊዜ ግልባጭ እግር ራስ ያካል” ከሚል የተቸነከረ መገረም ወጥታ  እና ራቅ ብላ ሌላኛውን አማራጭ የመከተያ ጊዜዋ አሁን ይመስለኛል።
    ከኢትዮጵያ ወገን የፍቅሩ እና የሰላሙ መንገድ የትም እንዳላደረሰ ከረፈደ ቢሆንም የታወቀ ይመስላል ። የተሻለው እና አቋራጬ መንገድ ከተዘጋ ሌላኛውን መጠቀም ግድ ይላል ። ተፈጥሮአዊም ነው። ራስ ተፈራዊያን” አንደኛው በር ሲዘጋ ሌላው ይከፈታል..”እንዲሉ..!
Filed in: Amharic