>

ከ ወልዲያ- ለ ኢትዮጵያ የተላከ...!!! (አሳዬ ደርቤ)

ከ ወልዲያ- ለ ኢትዮጵያ የተላከ…!!!

አሳዬ ደርቤ

የመስቀል ደመራ፥ በሚደመርበት፥ ትልቅ አደባባይ
በተጎለተ ታንክ፥ ፍጥረቱ ሲወድም፥ ጎጆዬ ሲደባይ
እንደ መስቀል አእዋፍ፥ እንደ አደይ አበባ
የአገሬ ሠራዊት፥
ምነው ቀልጦ ጠፋ? መንግሥት ወዴት ገባ?
ወልዲያ የሚል ሥሜን፥
በ ወልዳይ ቀይረው፥ ታፔላ ሲሰቅሉ፤
ተክላይና ሐብታም፥ ገዥዎቼ ሆነው፥ ልጆቼን ሲበሉ
ከእናቴ ነጥለው፥ ከተገንጣይ ካርታ፥ ምድሬን ሲከልሉ
የሰው ልጅ ይመስል- በሬ ዘር ተሰጥቶት- በባንዳ ፍረጃ
በሰነፎች እርሳስ- እንስሳቱ ሁሉ፥ ሲያልቁ በጠመንጃ
መንግሥቴ ነህ ብዬ- ግብር የምከፍለው
በባለፈው ምርጫ- ድምጼን ተረክቦ- አሸነፍኩኝ ያለው
በአንበጣ ስሰቃይ፥
ድምጹን ጸጥ ማድረጉ- በስንት ሽጦኝ ነው?
ያን አዚማም መሪ፥
ምን በድዬው ይሆን? በምን አስቀይሜ?
እንደ መጠጥ ውሃ፥ ጦርነትን ስቦ፥ ወርውሮ ከጅስሜ
ፈርዶብኝ የጠፋ፥
በእነዚህ መዥገሮች፥ ይመጠጥ ዘንድ ደሜ?
አሁን ይሄን ስጽፍ..
ይሰማኛል ለቅሶ፥ ይሰማኛል ጩኸት
ወራሪ በቡድን፥ የሚደፍራት እንስት
አውራ ጎዳና ላይ፥ የሚረሸን ወጣት
የተራበ ልጇ፥ ሲያጣጥር ማዳመጥ፥ የተሳናት እናት
ታጣቂ ስር ወድቃ፥ ገላግሉኝ ትላለች፥ ግደሉኝ በጥይት
አሁን ይሄን ስጽፍ፥ የሚሰማው ሁሉ፥ እሪታና ሲቃ
እናንተ ቀዬ ግን፥
የአዲስ መንግሥት ድግስ፥ የአውዳመት ሙዚቃ፡፡
Filed in: Amharic