>

ልደቱ አያሌውን ምን ነካው...?? (በአሳዬ ደርቤ)

ልደቱ አያሌውን ምን ነካው…??

(በአሳዬ ደርቤ)

አቶ ልደቱ በርካታ ኳሊቲዎች ያሉት ፖለቲከኛ በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት አድናቆቴን ገልጨለታለሁ፡፡ ከሆነ ጊዜ ወዲህ ግን በብአሩም ሆነ በንግግሩ የሚሠጣቸው አስተያየቶች ሚዛናዊነት የጎደላቸውና እውነትን ማየት የተሳናቸው ሆነው ስላገኘኋቸው ይሄን ትዝብቴን ልጽፍበት ወደድኩ፡፡
ይሄንንም ትዝብቴን አቶ ልደቱ ከዘረዘራቸው አገራዊ ችግሮች ስጀምር እንደ አብዛኛው የዚህችን አገር ችግር ፈጣሪ ለመለየት አስበን ፕሮብሌም ትሪ ብንሠራ ሩት ፕሮብሌም ሆኖ የሚገኘው ህወሓት ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ በሁለተኝነት ደግሞ መንግሥትን አስቀምጣለሁ፡፡
አቶ ልደቱ ግን በንግግሩም ሆነ በብዕሩ የአገራችንን ችግር ሲገልጽ መንግሥትን እንጅ ህወሓትን በድፍረት የተጋፈጠበትን ቀን አላስታውስም፡፡ ከዚህ ይልቅ እንደውም የአቶ ልደቱ አስተያየት ለህወሓቶች የሚጥም ሲሆን ይታያል፡፡
ከዚህ ባለፈ ደግሞ አቶ ልደቱ አያሌው በድርድርና በንግግር የሚያምን ፖለቲከኛ እንደመሆኑ መጠን ‹‹ከእኔ የሰላማዊ የትግል አቅጣጫ በተቃራኒ የተሰለፈው ማን ነው?›› ብሎ ሲጠይቅ ብቸኛ መልስ ሆኖ የሚታየው  የአራት ኪሎው መንግሥት እንጂ ህወሓት አይደለም፡፡
በእኔ እይታ ግን የአቶ ልደቱን ሰላማዊ ትግል በመከተል ረገድ ከህወሓት ይልቅ መንግሥት የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ ከሰሜን እዝ ጥቃት በፊት በህውሓት የጥፋት እጆች ኢትዮጵያ ስትታመስ መንግሥት ግን ተመሳሳዩን ባለማድረጉ ትግራይ ክልል የሰላም አየር ስትተነፍስ እንደነበር ማስታወስ ይበቃል፡፡ ከዚህ ባለፈም መቀሌ ከደረሱ በኋላ ተዋርደው የሚመለሱ የሀገር ሽማግሌዎችን ይልክ ነበር፡፡
ይህ የሰላም መንገድ ግን በህወሓቶች ዘንድ እንደ ድክመት ታይቶ ሰሜን እዝ ላይ ክህደት ለመፈጸምና የጦርነት ነጋሪት ለመጎሰም አበቃቸው እንጂ ወደ ሰላም ጎዳና አላመጣቸውም፡፡
አቶ ልደቱ ግን ‹‹ወደ ጦርነት መገባት አልነበረበትም ነበር›› በማለት የሚወቅሰው ሰሜን እዝን ያጠቃውንና ጦርነቱን የጀመረውን አካል ሳይሆን እጁን ተስቦ ወደ ጦርነት የገባውን መንግሥት ነው፡፡
ሌላው ደግሞ ህውሓት ከፌደራል ከተባረረበት ጊዜ አንስቶ ‹‹የትግራይና የኤርትራ ሕዝቦች ወንድማማቾች ናቸው›› በሚል መግለጫ ለኢሳያስ አፈወርቂ ‹‹የአገር አፋርሰኝ›› ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ አቶ ልደቱ ግን ‹‹ህወሓትና ሻእቢያ ቢስማሙ አገሬ ምን ትሆናለች›› የሚል ስጋት አልተሰማውም፡፡  ከዚህ ባለፈ ደግሞ ‹‹ከጎረቤታችን ይልቅ ሱዳኖች ወገኖቻችን ናቸው›› በሚል ንግግሩ የሚታወቀው ዶክተር ደብረ ጽዮን ኢትዮጵያን የሚወጋ ጦሩን ሱዳን ላይ ሲያሰለጥን አቶ ልደቱ ድምጹ አልተሰማም፡፡
ሰሜን እዝ ከተወጋ በኋላ የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ ሲገባ ግን ‹‹ካንተ ወገኖች ይልቅ ሱዳኖች ይቀርቡኛል›› ካለው ፕሬዝዳንት ጎን ተሰልፎ ‹‹ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ይልቅ ደብረ ጽዮን ይቀርበኛል›› የሚል አቋሙን ይዞ ሲመጣ ታዝበናል፡፡
ሲቀጥል ደግሞ ማይካድራ ላይ ጭፍጨፋ የፈጸሙ የሳምሪ ወንጀለኞች ሱዳን ገብተው መሰልጠናቸውን ከምንም ሳይቆጥር በቸልታ ያልፈውና ‹‹የኤርትራ ወታደር እንዴት ወደ ትግራይ ምድር ይገባል?›› የሚል ጥያቄ ይዞ ይመጣል፡፡ የዚህም ጥያቄ መልሱ ‹‹ድንበሩን የሚጠብቀው ሰሜን እዝ ስለተደመሰሰ›› የሚል ቢሆንም፣ አቶ ልደቱ ግን ሰሜን እዝ ላይ በተፈጸመው ክህደት የተበሳጨው የምዕራብና ደቡብ እዝ ሠራዊት በቅራቅርና በወሎ ግንባር ጦርነት የለኮሰውን የህውሓት ሠራዊት አልፎ የኤርትራ ወታደር ጋር ግብግብ ባለመግጠሙ የተሰማውን ቅሬታ ሲገልጽ ይሰማል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ህውሓት ተሸንፎ ወደ ቆላ ተንቤን ከሸሸ በኋላም የተናጠል ተኩስ አቁም ያደረገው የአራት ኪሎው መንግሥት እንጂ ህውሓት አልነበረም፡፡ ህውሓትማ መቀሌ ላይ አርፎ በመቀመጥ ፈንታ ‹‹በአንድ ሳምንት ውስጥ አራት ኪሎ እገባለሁ›› በሚል ፕሮፖጋንዳ አፋርና አማራ ክልልን ለመውረር ነው የተነሳሳው፡፡ የኤርትራ ጦር አክሱም ላይ ጥቃት ሲፈጽም ሕመሙን የሚገልጸው አቶ ልደቱ ግን የትሕነግ ታጣቂ ላሊበላ ገብቶ ከፍተኛው ውድመት ሲፈጽም አንዲት ቃል እንኳን አልተነፈሰም፡፡
ስለ አገሩ ቀጣይ እጣም ሲያስብም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከመተቸት ባለፈ ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ እንጦርጦስ ድረስ እጓዛለሁ›› በሚል ግልጽ አቋም ዘግናኝ ወረራ የፈጸመውን ሃይል በስጋት አይመለከተውም፡፡
ከሁሉም ደግሞ የገረመኝ ባለፈው አገራዊ ምርጫ በአዲስ አበባም ሆነ በኦሮሚያ፣ በአማራም ሆነ በደቡብ ክልል ብልጽግና መመረጥ የቻለው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመልካም ዐይን የሚመለከቱ ዜጎች በሰጡት ድምጽ ቢሆንም፤ አቶ ልደቱ ግን የብልጽግናን ማሸነፍ በጸጋ ተቀብሎ ሲያበቃ ደካማው ፓርቲ የተመረጠበትን ምክንያቱን ያስወግድ ዘንድ ማሳሰቡ ነው፡፡ ከኦነግና ከትህነግ ጋር አብረው የሚሠሩ በርካታ አመራሮችን በውስጡ የያዘው የብልጽግና ፓርቲ እራሱን ያጠራ ዘንድ በመምከር ፈንታ በኦነግና በትህነግ የሚጠሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር በሌላ በመተካት ፓርቲው አገሩን ይታደግ ዘንድ ጥሪ ማቅረቡ ነው፡፡
በበኩሌ ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ጠንቅቆ ይረዳል ብዬ የማስበው ፖለቲከኛ ‹‹ኢትዮጵያን ያልተገባ ጦርነት ውስጥ አስገብቷል›› ብሎ የሚያስበውን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሥልጣኑ ይነሳ ዘንድ ሲያሳስብ ከኦነግና ከትሕነግ ጋር አብሮ መሥራት የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትር ምን አይነት ነው?›› ብሎ ማሰብ እንዴት እንዳቃተው አልገባኝም፡፡ ‹‹እነዚህ ድርጅቶች የሚፈልጉት መሪ አገሩን የሚታደግ ወይስ የሚበታትን?›› ብሎ ማሰብ ያልፈለገበት ምክንያት አልተገለጸልኝም፡፡
ሲጀመርስ በዘር ፖለቲካ በምትተዳደር አገር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር የመምረጫ ዋነኛው መስፈርት ማንነት እንጂ ብቃት እንዴት ሊሆን ይችላል?
ለመሆኑ አቶ ልደቱ እራሱ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቢመረጥ ከዶክተር ዐቢይ በባሰ መልኩ ክንዱን አፈርጥሞ አገር አፍራሽ ሃይሎችን መደምሰስ ካልቻለ ትህነግና ኦነግ የሚፈልጓትን እንጂ እራሱ የሚያልማትን አገር መፍጠር ይችላል?  ወንበሩ ላይ በተቀመጠ ማግስት አገሩን ሰጥቶ፣ በዜግነት ፖለቲካ መቃብር ላይ የዘር ፖለቲካን አጎምርቶ እንደፈለጉ እንዲዘርፉና እንዲጨፈጭፉ የሚፈቅድ ደካማ መሪ ካልሆነ በቀር ሕግና አገርን የሚያስከብር ጠንካራ መሪ እንዲሆን ይፈቅዱለታል? በተባ አንደበቱ ብቻ እቅዱንና እንቅፋቱን፣ በሽታን እና ጤንነትን፣ ከፋፋይ ሕገመንግሥቱንና አገራዊ አንድነትን አስማምቶ መሄድ ይቻለዋል? አሁን ላይ የሚያቀነቅነውን የሰላም ስብከት ለሃይማኖት አባቶች አስረክቦ ሕመሙን በመድሃኒት ለመፈወስና፣ አማጺውን በጥይት ለመደምሰስ ካልተነሳሳ በቀር አንድ እርምጃ መራመድ ይሳካለታል፡፡
የመለስ ዜናዊን ማንነትና ብቃት ይዞ ወደ ሥልጣን በመምጣት እንደ ልባቸው የሚዘርፉበትን እና የሚፈነጩበትን ሥነ ምህዳር መፍጠር ካልቻለ በቀር በህውሓቶች ዘንድ በብቃቱ ተቀባይነት አግኝቶ የሚፈልጋትን አገር ይገነባል?
‹‹ጃል ልደቱ›› የሚል ሥም ከተጻፈበት መታወቂያ ጋር የሆነን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ፣ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ማሰብ ይቅርና ሥሟን ላለመጥራት ምሎ ወደ አራት ኪሎ ካልገባ በቀር አሀዳዊ እና ጨፍላቂ ከሚል ፍረጃ ማምለጥ የሚችለው እንዴት ነው?
ደግሞስ ከዘረኞች ጋር በሰላማዊ መንገድ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ይሄን ያህል ጥበብ ካለው ከዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ጋር የመሠረታቸው ፓርቲዎች እንዴት ሊፈርሱ ቻሉ? ከሰሞኑን የሚሰጣቸው አስተያየቶች’ስ ላሊበላ የሚገኝ ሆቴሉን ካልሆነ በቀር አገሩን ከፍርሰት ሊታደጉ ይችላሉ ወይ?            መልሱን እጠብቃለሁ!
Filed in: Amharic