>
5:13 pm - Thursday April 18, 0115

አንዳንድ ፅኑ ዝምድናዎቻችንና ንቅሳቶቻችን….!!! (አሳፍ ሀይሉ)

አንዳንድ ፅኑ ዝምድናዎቻችንና ንቅሳቶቻችን….!!!

አሳፍ ሀይሉ

አሁን እስቲ ልብ ብለን እንይ፡፡ እና ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ለመሆኑ እንዴት ብሎ እና ለምንስ ዓላማ ሲባል ይሆን… የላሊበላን አብያተ መቅደሶች ቅርፅ የያዙ ምስሎች ቀደም ባለው ዘመን ከ1700-2000 ዓመታት በፊት በተሰሩት የአክሱም ኃውልቶች ላይ ሊገኙ የቻሉት?? ይህ እጅግ የሚያስገርም ነገር ነው፡፡
ደግሞ እስቲ አስበው፡፡ ለምሳሌ ከወጥ ድንጋይ በሚገርም ጥበብ የተፈለፈሉት የላሊበላ ፍልፍል ቤተመቅደሶች በዓለም የዩኔስኮ መዝገብ ‹‹የሰው ልጅ ስምንቱ ብርቅዬ አስገራሚ ነገሮች›› በሚል ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ይህ በጥንታውያን አባቶቻችን ጥበብ እንድንኮራና ራሳችንን ቀና አድርገን እንድንራመድ የሚያስችል ታላቅ የጥበብ ውርስ ነው፡፡
ግን ግን… ለመሆኑ ልብ ብለህ አስበኸዋል? ለመሆኑ ምን ቢያስቡና.. ምንስ ትስስሮሽ ቢሰማቸው.. ወይስ ለምን የተለየ ተዓምራዊ ዓላማ ይሆን.. ከዘመናት ቆይታ በኋላ ከ1000 ዓመታት በፊት በተገነቡት የላሊበላ ቤተመቅደሶች ላይ (በእነ ቤተ-ጊዮርጊስ፣ በእነ ቤተ-መድኃኔዓለም፣ በእነ ቤተ-አማኑኤል፣ በእነ ቤተ-ገብርኤል፣ በቤተ-ማርያም) በሁሉም ላይ የአክሱም ኃውልትን ቅርፅ በላያቸው ላይ ተወቅሮ.. አሊያም የበር፣ የመስኮትና የደወል-ቤት ቅርፆቹ በአክሱም ኃውልት አምሳል እንዲቀረፁ የተደረጉት???
ለመሆኑስ.. ከዛሬ 400-500 ዓመት በፊት የተገነቡት የጎንደር አብያተ መቅደሶችና ቤተ-መንግስቶች እንዴት እና ለምንስ ትስስሮሽ ሲባል ይሆን መግቢያቸውና ቅፅራቸው፣ በርና መስኮታቸው፣ ቅስቶቻቸው ሁሉ የአክሱምን አናት የመሰለ ቅርፅ ይዘው እንዲሰሩ የተደረጉት??
እንዴትስ እና ለምንስ ማዛመድ አስፈልጓቸው ይሆን በጥንታዊ የጣና ገዳማት ውስጥ የደብረ-ብርሃን ሥላሴን መሠረታዊ ቅርፅና ምሥሎች የያዙ ቅስቶችና ጥንታዊ ስዕሎች ሊገኙ የቻሉት??
የጎንደርስ ከዮዲት ጉዲትም፣ ከደርቡሾችም፣ ከጣሊያኖችም ቃጠሎ ሳይነካ የተረፈው ብቸኛ ጥንታዊ ቤተ-መቅደስ (ደብረ-ብርሃን ሥላሴ – ጎንደር) እንዴት እና ለምንስ ዓላማ ሲባል.. ይሆን በውስጡ የአክሱምን የመሰሉ አምዶችና የውስጠኛው የመቅደስ በሮች ሊሠሩለት የቻሉት???  እስቲ እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ እስቲ አንዱ ካንዱ ጋር ያለውን ዝምድና እንመርምር፡፡
ዛሬ ድረስስ በእናቶቻችንና በእህቶቻችን ገላ ላይ ተነቅሰው የምናያቸው… የአክሱም ሴቶች ወይም የጎጃም ልጃገረዶች ወይም የወሎ እናቶች በግንባራቸውና በአንገታቸው ላይ የሚነቀሱት መስቀልና የሚሰሩት ጥበባዊ ቅርፆች የላሊበላን መስቀሎች፣ የአፍሮ አይገባን ንድፎች .. አፍሮ አይገባ ደግሞ የአክሱምን ጉልላቶች የመሰለ (በእርግጥ የራሱ ትንታኔና ምሥጢር ቢኖረውም).. ቅርፆችን ተላብሰው የምናያቸው.. ለምን ይሆን?
በአይን መንጥረህ ልታየው በማትችለው (ያኔ ዲ.ኤን.ኤ እና አር.ኤን.ኤ ሳይመጡ) በማይታይ ሁኔታ በደማችን መካከል ያለውን የኢትዮጵያውያን ቁርኝቶች፣ ዝምድናዎችና መተሳሰሮች እንዳይጠፉ.. እንዳይረሱ.. ለዘለዓለም በአይናችን እንድናያቸው.. ዳብሰን እንድንረዳቸው… ጨፍነን እንድናምናቸው.. በጥንታውያን አባቶቻችን ሆን ተብለው የተቀመጡልን ህያው ምልክቶች ይሆኑ??
(በነገራችን ላይ.. የአክሱም አምዶችን የስነ-ህንፃ ዲዛይን የያዘ ጥንታዊ የብራና ንድፍ በጎንደር አብያተ-መቅደሶች ተገኝቷል፤ የጎንደርና የላሊበላን ንድፎች ደግሞ ተቆፍረው ከወጡ የአክሱማውያን ቤተ-መንግስቶች ውስጥ ተገኝተዋል የሚልም መረጃ አለ – ምን ያህል በማስረጃ የተደገፈ እንደሆነ ግን በእውነቱ አላውቅም፡፡)
እናማ.. የእኛን የሃበሻ ሕዝቦች ከጥንትም የነበረ.. አሁንም ያለ.. እና በእርግጠኝነትም ወደፊትም የሚኖር… የእርስ በእርስ መጋባት፣ መዋጋት፣ መዛመድ፣ መዋለድ፣ መዋኻድና መመሣሠል.. ይሄን ሁሉ የሰው-ከሰው.. የወገን-ለወገን… የሕዝብ-ለሕዝብ… ዝምድናና መስተጋብር.. አንድም ሣላስቀር እንኳ ወደጎን ልግፋው ብትል… በቃ… አትችልም!
ድፍን ዓለምን ባስደመሙ ጥንታውያን ታላላቅ ዝርያዎቻችን በታነፁልን አስገራሚና አስደማሚ አምዶቻችንና  ቤተአምልኮዎቻችን መካከል የምታየውን… አንዱ ያንዱን ቅርፅ ይዞና ተላብሶ መገኘት፣ ሌላኛው አካል ላይ የዚህኛውን ምልክት ተነቅሶት መገኘት፣ ያኛው ይሄኛውን የአካሉ ክፋይ አድርጎ የመገኘቱንስ ምን እንበለው?
እነዚህን ሁሉ የኢትዮጵያውያንን እጅግ አኩሪና እጅግ ሊደነቁና ሊወደሱ የሚገባቸው… ትስስሮሾች… አጋርነቶች.. ዝምድናዎችና.. ወገንተኝነቶች.. በቀላሉ መርሳት ወይም  ማጥፋት ይቻላል ወይ?
ከቶውኑም (እደግመዋለሁ፡- ከቶውኑም!!!!!) ማንም ቢሆን… (አሁንም እደግመዋለሁ፡- ማንም!!!) ፈፅሞ.. እና በተዓምራት መደራረብ… ሊያስቀራቸውና ሊፍቃቸው ሊያጠፋቸው ሊበጥሳቸው ከቶውኑም አይቻለውም፡፡ ባይ ነኝ፡፡
(‹‹ባይ›› ሆኖ ስለዚያ ለማለት ሳይሆን… በእርግጥም ስለሆነና በገሃድ ስላለም ጭምር የተነገረ ቃል መሆኑም እንዳይዘነጋ!!!!)
አብረን እጅ ለእጅ.. ልብ ለልብ… ተጣምረን በጋራ.. ለጋራ ብልፅግናችን.. በመተሳሰብ.. እንደ አንድ ቤተሰብ ወደፊት የምንጓዝበት…. መልካም ብሩህ ዘመን ለሁላችን ይሁንልን!!!!!!!!
Filed in: Amharic