>

አቢይ ፓርቲውን በሃይማኖቱ ስም እንዲሰይም ልዩ ፍቃድ የሰጠው አካል ማን ነው...??? ያሬድ ጥበቡ

አቢይ ፓርቲውን በሃይማኖቱ ስም እንዲሰይም ልዩ ፍቃድ የሰጠው አካል ማን ነው…???

ያሬድ ጥበቡ

አቢይ መቼም የሃይማኖቱን ስም የገዢው ፓርቲ ስም ለማድረግ በነበረው እብደት ካልታወረ በቀር ብልፅግና ል ሲጎድለው የሚሰጠው ትርጉምና BADHAADHINNA የሚለውን የኦሮሙኛ ቃል የሚያነብ ኢትዮጵያዊ የሚሰማውን ሃፍረት ለማስተዋል እንዴት አቃተው? ለመሆኑ ሃይማኖትና ፖለቲካን የሚለየውን የህገ መንግስት ድንጋጌ ማን ሰርዞት ነው አቢይ ፓርቲውን በሃይማኖቱ ስም እንዲሰይም ምርጫ ቦርድ የፈቀደለት? ይህን ጥያቄ በወቅቱ ጠይቄ ከምርጫ ቦርድ መልስ አላገኘሁም:: ይህ ማለት ነገ ኡስታዝ ጀበል ተነስቶ ዋህቢያ የሚል ፓርቲ ቢመሠርት: ወይም ዲያቆን ዳንኤል ሞቅ ብሎት የኦርቶ ጴንጤ ፓርቲ መሥርተናል ቢሉ ይፈቀድላቸዋል ማለት ነውን? ምርጫ ቦርድ አሁን እረፍት ላይ ስለሆነና ለማሰብ ጊዜ ስላለው ጉዳዩን ቢመረምረው ተገቢ ይመስለኛል::
ከምሰማው በኦሮሚያ ክልል የጨፌና ፌዴራል ተመራጮች 60 በመቶ ጴንጤ: 30 በመቶ ሙስሊምና ከ5 በመቶ በታች የተዋህዶ ክርስትና ተከታዮች መሆናቸውን ነው:: ይህ እውነት ነውን? ከሆነስ በነገው እለት የምንጠብቀው የፌዴራል ሹሙት ይህንኑ የኦሮሚያውን ስብጥር የያዘ ይሆን? ቢያንስ 55 በመቶ የሚሆን የተዋህዶ ክርስትና ተከታይ ባለባት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ላይ 5 በመቶ ብቻ የሚወከሉበት አካሄድ ፍትሃዊ ነውን? እንዴት ነው በሰሜን በሚካሄደው ጦርነት የአንድ ተዋህዶ ልጆች እርስ በርስ እየተፋጁ ከምኒሊክ ቤተመንግስት ሲችዌሽን ሩም ተቀምጦ የሚያዋጋቸው አመራር 60 በመቶ የብልግና ኢቫንጀሊስት: 30 በመቶ ሙስሊም: 5 በመቶ ተዋህዶ ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው? ያዋጣል? ያስኬዳል? አቢይ እኔን ለማሳፈር ሲል የካቢኔ ተመራጮቹን ስብጥር አስተካክሎ ቢመጣ ደስታውን አልችለውም:: ሁሌም ለፍትህ ከቆመው ትውልድ የተወለድን በመሆኑ: ዱሮ ሙስሊም በገዛ ሃገሩ ተገፋ ብለን ለሃይማኖት እኩልነት የተሰለፍነውን ያህል ዛሬ ደግሞ ተዋህዶ ክርስትያኑ ሲገፋ ዝም ልንል አይቻለንም:: ለሥራው የሚመጥኑ ዜጎች እስካሉ ድረስ: በሁሉም የሥልጣን እርከኖች ፍትሃዊ የብሄረሰብና ሃይማኖት ስብጥርን መጠየቅ ፍትሃዊ ነው ብዬ አምናለሁ:: ፍትህ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች:: በማንነታቸው መገለሉ ይብቃ! ለ30 ረጅም አመታት ከበቂ በላይ ሲገለሉ ኖረዋል::
Filed in: Amharic