>

"ምኗ ላይ ተቀምጣ በሽንቷ ሰፌድ ትሰፋላች":-አዲሱ የአቢይ ካቢኔ አሰያዬም (ሸንቁጥ አየለ)

ምኗ ላይ ተቀምጣ በሽንቷ ሰፌድ ትሰፋላች”:-አዲሱ የአቢይ ካቢኔ አሰያዬም
ሸንቁጥ አየለ

ችግሩ ያለዉ የጎሳ ፖለቲካ ርዕዮተ ፍልስፍናዉ ላይ ነዉ::ኢትዮጵያዉያንን ሀገር አልባ ያደረገዉን የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና መሰረት ላይ የቆመ ካቢኔ ምንም አይነት መልካም ግለሰቦችን ሰብስብቦ ቢያቅፍ ከቶም የሀገር መድሃኒት አያመጣም::
ሆኖም የዚህ ስርዓት የጥቅም ተጋሪዎች እና እግር አጣቢዎች ይሄን የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ የተለያዬ የማስመሰያ መቀባቢያ በመቀባት ጸረ ሰዉ የሆነዉን የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ ለማስቀጠል እና ህዝብን ለማምታታት ብዙ ሲዳክሩ ይሰተዋላል::በአዲሱ የአቢይ ካቢኔ አሰያዬም የተከናወነዉ ድራማም ይሄዉ ነዉ::
እከሌ ከኦህዴድ:እከሌ ከብአዴን:እንትና ከአብን : እንቶኔ ከኢዜማ: እንቶኔ ደግሞ ከትግራይ ብልጽግና ተሾሙ እያሉ ብዙ የጥቅም ተጋሪዎች እና የአገዛዙ ሚዲያ ብዙ ይቀባጥራሉ::በደስታም እንኳን ደስ አለህ ይባባላሉ::ኢትዮጵያዉያን ግን አሁንም ሀገር አልባ ናቸዉ::
የኢትዮጵያ የችግር ምንጭ ሁሉ አንድ ነዉ::ይሄዉም የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና ነዉ::መለስ ዜናዊ የሀገሪቱን ጥፋት ያመጣዉ የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና በማራመድ ነበር::መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ በስሩ ብዙ በግለሰብ ደረጃ መጥፎ የማይባሉ ሰዎችን በካቢኔዉ ዉስጥ ሰግስጎ ነበር::
ሆኖም የመለስ ዜናዊ ካቢኔ እያንዳንዱ የሚመራበት መርህ በጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና እና ቀመር ስለሆነ የሚሰሩ ስራዎች ሁሉ በዚሁ መርዛማ ህሳቤ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ነበሩ::
አሁንም አቢይ የሾማቸዉ ሰዎች መጥፎ ናቸዉ ጥሩ ናቸዉ የሚለዉ አይደለም ጥያቄዉ:: ወይም ደግሞ ሰዎች ከዬትኛዉ ፓርቲ ተመርጠዉ ተሾሙ አይደለም ጥያቄዉ::
አቢይ የሚመራበትም የፖለቲካ ፍልስፍና እንደ መለስ ዜናዊ ሁሉ የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና ነዉና ያዉ ዉሃ ቢወቅጡት እንቦጭ ነዉ::ስለዚህ የተሿሚዎቹ መልካምነት ወይም የመጡበት የፓርቲ ቁም ነገር አይደለም::
ግለሰብ አምላኪ ለሆኑ ሰዎች ግን ይሄ የሰዎች የሹመት ቦታ መለዋወጥ ምናልባት እንደ ቁምነገር ይታያቸዋል::አንዳንዱ ከአዲስ ትሿሚዎች ጋር ያለዉን ትሥስር እያንሰላሰለ ምን ጥቅም እንደሚያገኝ በማሰብ ሽቅብ ሽቅብ እየዘለለ በደስታ ሰክሯል::ኢትዮጵያዉያን ግን አሁንም ሀገር አልባ ናቸዉ::
ዋናዉ ነጥብ የኢትዮጵያ መከራዋ እና ህመሟ የተቋጠረዉ ከጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና ጋር ነዉና እጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና ላይ ቆሞ እስክስታ የሚመታ ምንም አይነት ካቢኔ ሀገር የሚያድን መድሃኒት ይዞ አይመጣም::
ስለዚህ አቢይ ጀግና ከሆንክ እና የኢትዮጵያን ህመም ማዳን ከፈለግህ የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍናህን በአዋጅ ለዉጥ::ኦህዴድህን አክስም::ካንተ ጋር ያሉ የብልጽግና የጎሳ ፓርቲዎችን እንዲሁም አጋር የጎሳ ፓርቲዎችህም የጎሳ ፓርቲያቸዉን ያክስሙ::የጎሳ ፖለቲካ በህግ ይታገድ::የጎሳ ህገ መንግስታችሁን አፍርሳችሁ በሌላ ቀይሩ::የጎሳ ክልላዊ አስተዳደራችሁን አፍርሱና ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ሀገር እንዲኖራቸዉ በሚያደርግ መልክዓ ምድራዊ አስተዳደር ተኩት::ያን ጊዜ የኢትዮጵያዉያን ሁሉ መሪ ትሆናላችሁ::
ከዚያ ዉጭ አዲስ ካቢኔ እያላችሁ የምትዘባበቱ ነገር ሁሉ “ምኗ ላይ ተቀምጣ በሽንቷ ሰፌድ ትሰፋላች” እንደሚባለዉ አባባል ዝም ብሎ የገማ የጎሳ ፖለቲካ ካንሰራማ ዉሃ ዉስጥ መንቦጫረቅ መሆኑን እወቁት::እንኳን ሀገር ልታድኑ እናንተንም መዝምዞ የሚያጠፋ መርዛማ ህሳቤ ዉስጥ እየተንቦጫረቃችሁ መሆኑን እወቁት::
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ !
Filed in: Amharic