>

በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስም ፋውንዴሽን ተመሰረተ...!!!! (ሃሚድ አወል)

በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስም ፋውንዴሽን ተመሰረተ…!!!!

ሃሚድ አወል


በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስም ፋውንዴሽን መቋቋሙ ዛሬ ይፋ ተደረገ። ፋውንዴሽኑ በሰብዓዊ መብቶች፣ ርሃብ እና ድህነት ላይ የሚሰሩ ስራዎችን የመደገፍ ዓላማ አለው ተብሏል።

የድርጅቱ ምስረታ ይፋ የተደረገው ፕሮፌሰር መስፍን ያረፉበትን አንደኛ ዓመት መታሰቢያ በማስመልከት ዛሬ ሐሙስ መስከረም 27፤ 2014 በአዲስ አበባው ኢንተር ሌግዥሪ ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። በዕውቁ ምሁር እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ስም የሚጠራውን ይህን  የመታሰቢያ ድርጅት ያቋቋሙት ቤተሰቦቻቸው እና የቅርብ ወዳጆቻቸው እንደሆኑ በዝግጅቱ ላይ ተገልጿል።

በአስራ ሶስት መስራች አባላት የተቋቋመው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፋውንዴሽን፤ ከመንግስት፣ ከሃይማኖት፣ ከጎሳ እና ከማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት ነጻ በሆነ መንገድ የተመሰረተ መሆኑ በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል፡፡ ዘጠኝ አባላት ባሉት ቦርድ የሚተዳደረውን ፋውንዴሽን  በዋና ሰብሳቢነት የሚመሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው የቋንቋ እና ስነ ልሳን መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ናቸው።

ዶ/ር በድሉ የፋውንዴሽኑን ምስረታ ዕውን ለማድረግ አንድ አመት ጊዜ መፍጀቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳደር” ተናግረዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጄንሲ ተመዝግቦ እውቅና ማግኘቱንም የቦርድ ሰብሳቢው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የፋውንዴሽኑን አብይ ዓላማ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር በድሉ “የፋውንዴሽኑ ዋና ዓላማ ሰብዓዊ መብቶች፣ ርሃብ እና ድህነት ላይ የሚሰሩ ስራዎችን መደገፍ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስም የተሰየሙ ቤተ መጽሃፍትን እና ማዕከላትን፤ በሁለተኛ ደረጃ እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱ የማድረግ እቅድ እንዳለውም ገልጸዋል።

ድርጅቱ እነዚህን ስራዎቹን ለመደገፍ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ያቀደው፤ ሐሳቡን ከሚደግፉ ግለሰቦች እና ተቋማት እንደሆነ ዶ/ር በድሉ አብራርተዋል፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ልጅ እና የድርጅቱ የቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር መቅደስ መስፍን፤ ፋውንዴሽኑ የፕሮፌሰሩን የምርምር ስራዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን በድርቅ እና ረሃብ ላይ በሰሯቸው የምርምር ስራዎች ይበልጥ ይታወቃሉ። በኢትዮጵያ ረሃብ እና ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሐፍትን በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ አሳትመዋል። በኢትዮጵያ አስከፊ ከሚባሉት የረሃብ ጊዜዎች አንዱ የነበረውን የ1966ቱን ረሃብ በህዝብ ዘንድ እንዲታወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት ምሁሩ፤ በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰተው ረሃብ ወደ ፖለቲካው ዓለም እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ደጋግመው ይናገሩ ነበር።

በፖለቲካ ተሳትፏቸው እና በአደባባይ ምሁርነታቸው ይበልጥ የሚታወቁት ጎምቱው ምሁር፤ በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት መከበር ባደረጉት አስተዋጽኦም ይዘከራሉ። በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ እና በመሰነድ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) የተመሰረተው በእርሳቸው ነበር።  የዲሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብት መከበርን ዓላማው ያደረገው ኢሰመጉ የተቋቋመው በ1984 ዓ.ም ነው።

ፕሮፌሰር መስፍን ባለፈው ዓመት መስከረም 20፤ 2013 በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በኮሮና በሽታ ተይዘው ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ባሉበት ወቅት ነበር። ዕውቁን የአደባባይ ምሁር የሚዘክር ዝግጅት ከነገ በስቲያ ቅዳሜ መስከረም 29፤ 2014 እንደሚካሄድ በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቁሟል።  በአዲስ አበባው ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል በሚካሄደው በዚህ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ በፕሮፌሰሩ እና በስራዎቻቸው ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባሉ ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Filed in: Amharic