የ’82ኛ’ ዓመት የልደት በዓል
ጌቱ አዲሱ
በዓሉ ግርማ የተወለደው በቀድሞ አጠራሩ በኢሊባቦር ክፍለ ሀገር ሱጴ በምትባል ሥፍራ በ1930 ዓ.ም ሲሆን ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በዘነበወርቅ ት/ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በጀኔራል ዊንጌት አጠናቁአል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በፖለቲካል ሳይንስና ኢንተርናሽናል ሪሌሽን የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኘ ሲሆን በዚሁ ተመሳሳይ መስክ ከአውሮፓ የማስተርስ ዲግሪውን አግኝቷል። በዓሉ ግርማ በተለይ በልብ ወለድና በፈጠራ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ተወዳጅነትና ዝናን ያተረፈ ዕውቅ ደራሲ ነበር፡፡
ከፃፋቸው በርካታ ድርሰቶች መካከል በ1962 ዓ.ም
የታተመው “ከአድማስ ባሻገር” የተሰኘው መፅሀፉ በሩሲያ ቋንቋ ተተርጉሞ ለቀድሞዋ ሶቪየት ኀብረት አንባቢያን ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም በጋዜጠኝነት ሙያም ስሙን ያስጠራ ነበር፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ፣ የመነን መጽሔት፣ የአዲስ ሪፖርተር መጽሔትና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ሠርቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ብዙ ወጣት ጋዜጠኞችን ለማፍራት ጥረት አድርጓል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ይታተም የነበረው አዲስ ሪፖርት የተባለውን መጽሔትም ደረጃው ከፍ እንዲልና በዓለም አቀፍ ደረጃም እንዲገመገም አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮም በኃላፊነት ቦታ ሠርቷል፡፡ በዓሉ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረከተና ብዙ ሥራዎችን የሰራ ደራሲ ነው፡፡
የመጨረሻው መጽሀፉ “ኦሮማይ” በወቅቱ በነበረው መንግሥት ሊደገፍ ባለመቻሉ በ1976 ዓ.ም ለሕይወቱ መጥፋት መንስኤ ሆኗል፡፡ በዓሉ ካሳተማቸው መጽሐፍት መካከል “ደራሲው” “የሕሊና ደወል” “የቀይ ኮከብ ጥሪ” በ1966 ዓ.ም እና “ሀዲስ” በ1972 ዓ.ም. ይገኙበታል፡፡