አንጋሳዊ ደዌ፤ የኦሕዴዳዊው ዐቢይ አገዛዝ ዓይነተኛ ማሳያ
ከይኄይስ እውነቱ
በርእሰ መጻሕፍቱ እንደተመዘገበው ሰብአ ትካት (በኖኅ ዘመን የነበሩ የቀድሞ ሰዎች) በፈጸሙት በደል ምክንያት እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በመፍጠሩ ተጸጽቶ አዝኖ ነበር፡፡ ተጸጽቶም አልቀረ ከታች ቀላያት ተነድለው፣ ከላይ የሰማያት መስኮቶች ተከፍተው (ጻድቁ ኖኅና ቤተሰቦቹ ሲቀሩ) በማየ አይኅ (በጥፋት ውኃ) ዓለሙ ጠፋ፡፡
አንጋሳ የሚባል ስሑት ፍጥረትም የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪም በመፍጠሩ ከሚጸጸትባቸው እፍኝት ፍጥረታት መካከል አንዱ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በሜዲያ ቀርቦ በዐደባባይ ዕዳሪ ሲወጣ ያሰማውን ዘግናኝ ድምጽ ከሰማሁ ከረምረም ብዬአለሁ፡፡ አስተያየት ለመስጠት ልቤ የፈቀደው ግን አሁን ነው፡፡ ይህ ጅምር ፍጥረት እንደ ጉማሬ በአፉ የሚፀዳዳ ይመስላል፡፡ ሰውነቱ ባጠቃላይ ዐዘቅተ ኵስሕ ካልሆነ በቀር አፉን ከፍቶ በኢትዮጵያ ላይ የለቀቀው ቆሻሻ እንዲህ ከዓይነ ምድር የከፋ አይሆንም ነበር፡፡ ዛሬ ምድራችንን በተለይም ቅድስቲቱን ኢትዮጵያ ለማርከስ ተፈትተው የተለቀቁባት ብዙ አዋልደ አጋንንት አንጋሶች አሉ፡፡ ሳይገባው በኢትዮጵያ መንበር ላይ የተሰየመው ዐቢይ ማንነቱን በአንጋሳ ውስጥ እንደ መስታወት አሳይቶናል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አንጋሳዊ ደዌ ያልሁት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን አምርሮ የመጥላት ድንቊርናና ዕብደትን ነው፡፡ አንጋሳዊ ደዌ አጽራረ ኢትዮጵያ ወያኔና ኦነግ ‹በደደቢት ሰነድ› አማካይነት በኢትዮጵያ ላይ የናኙት አደገኛ ‹ቫይረስ› ነው፡፡ የወያኔና የኦነግ የመንፈስ ልጆች የሆኑት ኦሕዴዳውያን፣ ብአዴናውያን፣ የቀድሞ ደሕዴናውያን፣ አጋር ተብዬዎችና በጐሣ ሥርዓት የሚያምኑ ሁሉ ‹የቫይረሱ› ማደሪያ (host) በመሆን በወራሽነት የተቀበሉት የአብሮነት ፀር አገር አፍራሽ ደዌ ነው፡፡
ከእውነትና ከታሪክ የተጣሉ አንጋሶች፣ የጐሣ አገዛዝን የሚያስቀጥሉ አንጋሶች፣ ሁለንተናዊ አገራዊ ቀውስ መጥመቅና ማትረፍን የአገዛዝ ስልት ያደረጉ አንጋሶች፣ ‹ብሔር÷ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› የሚል ተረትና ድንቊርና ፈጥረው የአንድ እናት ልጆችን የሚያናክሱ አንጋሶች፣ የሚጠሉትንና የሚጸየፉትን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለሥልጣን ማስጠበቂያ መያዣ ያደረጉ አንጋሶች፣ እነሱ በእጃቸው ጭብጥ በእግራቸው ርግጥ አድርገው የማይገዙት ሕዝብና አገር ይጥፋ የሚሉ አንጋሶች፣ ኢትዮጵያን ለሽርፍራፊ ሥልጣን የከዱ አንጋሶች፣ ዜጎችን በነገድ እና ሃይማኖት ማንነታቸው ለይተው የሚያርዱና የሚያሳርዱ አንጋሶች፣ የአድርባይነት ክፉ ደዌ የተጸናወታቸው አንጋሶች፣ ‹አዲስ መንግሥት› ተመሠረተ ብለው ጮቤ የሚረግጡ ለቅልውጥ የተዘጋጁ አንጋሶች፣ በጠራራ ፀሐይ አዲስ አበባንና ነዋሪዎቿን (ነፃነትና መብት አልባ አድርገው) በወረራ የያዙ አንጋሶች፣ በጦርነት÷ በመፈናቀልና በረሃብ እየተገረፈ ባለ ሕዝብ ላይ የአገር ሀብት ዘርፈው በፋሽን ልብስ የሚምነሸነሹና የሚሳለቁ አንጋሶች፣ ተረኝነት በፈጠረው ዕብደትና ድንቁርና በዝርፊያና ማንአለብኝነት የሠለጠኑ አንጋሶች፣ ሕይወትም÷እምነትም÷ ትምህርትም ‹ሰው› ያላደረጋቸው አንጋሶች፣ ቅጥረኝነትና ዘላለማዊ አሽከርነት ባሕርያቸው የሆኑ ብአዴን የሚባሉ በአማራ ሕዝብ ላይ በተለይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ባጠቃላይ የተነሡ አንጋሶች፣ ወያኔ የማይወክለውን የትግራይ ሕዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገኑ አለያይቶ ለመከራ እንደዳረገው ሁሉ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክሉት የወያኔ ውላጆች የሆኑ ኦሕዴዳውያን/ኦነጋውያን የኦሮሞን ሕዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገኑ አለያይተው ለመከራ ለመዳረግ የሚሯሯጡ አንጋሶች ወዘተ. እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ ሥር የሰደደ አንጋሳዊ ደዌ ሠልጥኖባታል፡፡
የጐሣ መድልዎ የሠለጠነበት፣ ዜጎች ለአፍታ ረፍት ያጡበት የዐቢይ አገዛዝ፤ በአንጋሳዊ ደዌ የተጠቃው ዐቢይና ድርጅቱ ኦሕዴድ በየትኛውም መመዘኛ ለኢትዮጵያ መርገም እንጂ በረከት ሊሆን አይችልም፡፡ ዐቢይና አንጋሳዎቹ ያለፉት ሦስት የግፍና የሰቈቃ ዓመታት ሳያንሳቸው በኢትዮጵያና በሕዝቧ ዳግም ሊመጣ ያለውን ውርደትና ዝቅታ ጉልህ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብላችሁ በሐሳዊ ኢትዮጵያዊነት ካባ ተሸፍናችሁ በፈርጀ-ብዙ አድርባይነት የተሰለፋችሁ አፍቃሬ ዐቢዮች ላም አለኝ በሰማይን ማንም አይከለክላችሁ፡፡ እስቲ ተጠየቁ፤ ወያኔ ትግሬን የምትጠሉበት መሠረታዊ ምክንያት ምን ይሆን? እናንተ የምታሸረግዱለት አገዛዝ ከወያኔ በምን ይለያል? ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ላይ የወረደውና በዋናነት አገዛዝ-ሠራሽ የሆነው መዓት ወያኔ ትግሬ ከአሽከሮቹ ጋር ላለፉት 27 ዓመታት ከፈጸመው ብዙ እጅ ቢያስከነዳ እንጂ ያንሳል? አገዛዙ በአፍራሽ ዓላማ ከሚያደርገው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት እንቅስቃሴ የእናንተ የአድርባዮቹ የሐሰት ጽሑፍ፣ የፈጠራ ክስ፣ የሐሰት ምስክርነት፣መርዘኛ ንግግር፣ ባጠቃላይ ከዕኩያን ጋር ኅብረት መፍጠር በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመውን ግፍና በደል ከማራዘሙም በተጨማሪ አገራችንን ወደማትወጣው ዐዘቅት እየከተታት ስለመሆኑ ከአእምሮችሁና ከኅሊናችሁ ጋር ከሆናችሁ አጥብቃችሁ እንድታስቡበት ወንድማዊ ምክሬን እለግሳችኋለሁ፡፡ ብርቅርቁም፣ ቅቡም ያልፋል፡፡ የአገዛዞች መጨረሻ ውርደት መሆኑን ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ አሳይቶናል፡፡ አሳዛኝ ገጽታው ጥፋታቸው ለሕዝብና አገር መትረፉ ነው፡፡ ቤተሰብ ካላችሁ ለልጆቻችሁ አንገታቸውን የሚደፉበት መጥፎ ውርስ አታስተላልፉ፡፡ አርነት የሚያወጣውን እውነት ይዞ መገኘት ብቻ ነው አንገትን ቀና የሚያደርግ፡፡