>

በአዲሱ መንግሥት የሕ/ተ/ም/ቤት ጉባዔ ትዝብቴ [መስፍን ማሞ ተሰማ]

በአዲሱ መንግሥት የሕ/ተ/ም/ቤት ጉባዔ ትዝብቴ

 

መስፍን ማሞ ተሰማ


በአዲሱ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሴት አባል ከሆኑት መካከል አራት ደቂቃ በፈጀውና በቀጥታ ስርጭት በተላለፈው ዲስኩራቸው ይዘትና መንፈስ በእጅጉ አዝኛለሁ/ተገርሜያለሁም። የፒኤችዲ – PhD – (Doctor of Philosophy) ሶስተኛ ዲግሪ በCouncilor Educator የትምህርት መስክ አለኝ ብለው የነገሩን ባለ ግዙፍ ሹርባዋ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ የት/ሚር ሆነው መሾማቸውን በመቃወም ነበር ንግግራቸው። መቃወማቸው አይደለም ችግሩ፣ የተቃውሟቸው ምክንያትና ግብ፣ እንዲሁም ራሳቸውን ያቀረቡበት አውድ እንጂ!
ሽሙጥ፣ ምፀትና ራስን በመካብ የአዋቂዎች ሁሉ አዋቂ፣ የሊቆች ሁሉ ሊቅ በማድረግ በአዳራሹና በዓለም ዙሪያ ለታደምነው ያስተጋባ ንግግር። Educator የሚለውን ጥልቅ ቃል ደጋግመው የወነጨፉት ዶ/ር የት/ሚ/ርነቱ ቦታ ለእኔ ይገባ ነበር ባይ ናቸው –
ካልሆነም እንደርሳቸው ለሆነ “Educator”።
ዶ/ር መሆናቸውን የነገሩን ራሳቸው ሲሆኑ፣ የዶ/ር ብርሀኑ ዶ/ርነት ግን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስከ ዐለም ዐቀፍ የዕውቀት ጎተራ ዩኒቨርሲቲዎቾ ተረጋግጦ የሰማነው ነው። [በበኩሌ የዶ/ር ብርሀኑም ሆነ የፓርቲያቸው ኢዜማ ወይም የሌላ የየትኛውም ፖለቲከኛ ወይም ፓርቲ ተከታይ ወይም ጭፍን አድናቂ አይደለሁም። አስተያዬቴ የሀገሩን ፖለቲካ ሳያሰልስ እንደሚከታተል አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው።)
በዶ/ሯ ንግግር ያዘንኩት/የተገረምኩትም በሁለት ጉዳዮች ነው። አንድም እንደ Educator በቋንቋ አጠቃቀማቸው፣ ሁለትም Self aggrandizement (ን) (ራስን እጅግ አግዝፎ መካብ) የተጠቀሙበት ኩነትና ግብ። ቋንቋን በተመለከተ ለምሳሌ አንድ ተማሪ ከክፍል ወደሚቀጥለው ክፍል ለማለፍ ወይም አንድ ሰው ሥራ ለመቀጠር ሁለት ምርጫዎች ያሉት ፈተና ይቀርብለታል እንበል። ትክክለኛውን ከመለሰ/ከመረጠ ወደ ቀጣይ ክፍል ያልፋል ወይም ሥራ ይቀጠራል። ምርጫዎቹም፥
A. We are educator.
B. We are educators.
በዚህ ምርጫ “A”ን የመረጠው ተማሪ መቶ በመቶ ይወድቃል፣ ሥራ ፈላጊውም ይባረራል። በሕ/ተ/ም/ቤት Educator ነኝ ያሉት ዶ/ር የተናገሩት በ”A” የሰፈረውን የተሳሳተ የሰዋሰው አጠቃቀም ነው። ይህ ቀላል የሚመስል ነገር ግን ለተማረ ሰው እጅግ ግዙፍ ስህተት ነው። ምርጫ “A”  ከቋንቋው ህግ ውጪ ስለሆነ ነው ተማሪውም የሚወድቀው፣ ሥራ ፈላጊውም የማይቀጠረው። እነሆም የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ባለ ግዙፍ ሹሩባዋ ዶ/ር Educator  ከሁሉም በላይ ትውልድን የሚያንፅ የትምህርት ሚኒስትር መሆን አይችሉም። የትምህርት ጥራት ከአስተማሪው የቋንቋ ህግጋትን መከተል ይጀምራልና!!
[የኢትዮጵያን ሁለት ትውልድ ዕውቀት ካመከኑትና በድቡሽት ላይ ካቆሙት የትህነግ አምላኪና የኢህአዴግ ቁንጮ ከሆኑት መካከል – በዶ/ሯ አጠራር ‘ንግሥት’ ገነት ዘውዴ – በዘመነ ወያኔ ት/ሚር የነበሩት ጋር ዛሬም እጅና ጓንት ሆነው እንዳሉ ነው የተናገሩት። “ንግሥቷ” የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ብቃት ዛሬ ለደረሰበት አስጊ ደረጃ ቀዳሚ ተጠያቂ መሆናቸው ይታወቃል። አፍቃሪ ወያኔን በአዲሱ መንግሥት ም/ቤት ተገኝቶ ማወደስ  ዘመነ ወያኔ ይመለስ ይሆናል ብለው በማሰብ ይሆን!?]
ሌላውና አንባቢ የራሱን ግንዛቤ ሊጨምርበት የሚገባው ጉዳይ ዶ/ሯ እንደ Educatorነታቸው ለትወልድ Role model (አፒራንስንም ይጨምራል) መሆን ይችላሉ ወይ የሚለው ይሆናል።
Self – aggrandizement – ( እራስን ከሌሎች በላይ አጉኖ መካብ/መስቀል) በእንግሊዝኛው ትርጉሙ በተብራራና ግልፅ በሆነ መንገድ እንዲህ ይላል፤ a pattern of pompous behavior, boasting, narcissism or competitiveness designed to creat an appearance of superiority. እነሆ ባለ ሹሩባዋ ዶ/ር በግላጭ ያንፀባረቁት የአራት ደቂቃው ንግግር ይህንን ከላይ የቀረበውን ነው። በዕለቱ የተላለፈውን እንደገና በአንክሮ በመከታተል በዚህ ትዝብት ላይ የሰፈረውን ማመሳከር ይቻላል። በዕለቱ ከታዘብኳቸው በርካታ ንግግሮችና ሰብዕና አንዱና ዋናው ይህ ነው።
በመጨረሻም ለትምህርት ሚኒስትሩ ለዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ቦንገርና ለመላው ተሿሚ ሚኒስትሮች ለምክር ቤቱ አበላትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም የሥራና የውጤት ዘመን ይሆንላቸው ዘንድ እንደ አንደድ ቅን አሳቢ ኢትዮጵያዊ እመኛለሁ! ሠላም ለኢትዮጵያ!!! ሠለም ለሕዝባችን!!!
Filed in: Amharic