>
5:16 pm - Wednesday May 24, 5567

ሰው የሚመገበውን ነው (ይሆናል)!! ፋንታሁን ዋቄ

ሰው የሚመገበውን ነው (ይሆናል)!!

ፋንታሁን ዋቄ

መርዝ በልቶ የማይሞተው ወጣት የጻፈውን መጽሐፍ ለማስመረቅ ነሐሴ 8 ቀን 2013 ያዘጋጀሁትና በጊዜ መጠባብ ሳቀርብ የቀረ ጽሑፌ ነው።
 የኢትዮጵያ የትምህርትና የፖለቲካ ከባቢብዙኃንን ምን እየመገበ እና ምን እያደረጋቸው ነው?
ይህን ጥያቄ አንሰቼ ለመመለስ ያነሳሳኝ በዲ/ን ዮሴፍ ከተማ ሆርዶፋ የተጻፈ “እጅ የበዛበት የኦሮሞ ፖለቲካና ኢትዮጵያዊነት” የሚለውን መጽሐፍ  ሳነብ ነው።
ዮሴፍ ከኢትዮጵያዊነትና ግዕዝ ፊደል ጋር የተጣሉ፣ ኦርቶዶክሳዊነትን ለማጥፋት ያለመታከት ላለፉት 50 ዓመታት ደም ሲፈሱ፣አጥንት ሲከሰክሱ፣ ታሪክ ሲያልከሰክሱ፣ የሐሰት ፋብሪካ አቋቁማው ዶርክተርና ፕሮፌሰር ሲባባሉ የነበሩ ስሑታን ፖለቲከኞች በበከሉት አየር ውስጥ በግንደ በረት ተወልዶ ያደገ ነው። ይህ ወጣት ልጅ የተወለደው ኦነግ የተባለ የትሕነግና የሻቢኣ ልጅ፣ የጣሊንና የጀርመን የልጅ ልጅ፣ የአሜሪካ የጡት ልጅ፣ የሜኒሶታ አንቀልባ፣ የፍራንክፈርት ማሞቂያ  ያሳደው ኢ-ኢትዮጵያዊ ቡድን ሚፈነጭበት ግንደበረት አየር ውስጥ ነው ያደገው። የተማረውም በኦነግና ትህነግ የትምህርት ሥርዓት አና የክልሉ የኦፒዲኦ የባንዲራ መዝሙር  “የመቶ ዓመት እድፍሽን በደማችን አጠብንሽ (“ጡሪ ወጋ ዺባ ዺጋን ሲራ’ ዺቅኔ/ Xuurii  Waggaa dhibbaa dhigaan sirraa dhiqnee) ተብሎ የሚዘመርበትንና ጥላቻ እንደ ታላቅ እውቀት የሚናኝበትን አየር እየተነፈሰ ነው።  ይህ ወጧት ከልጅነቱ ጀምሮ እስከዛሬ የሚመገበው የኢትዮጵያና ኦርቶዶክስ-ጠልንት የሚያፋፋ የፕሮፓጋንዳ መርዝን ከሆነ፣ የሚመገበው ሥሁት ርእዮትና ሐሰተኛ ትርክትን አውነት ለማሰመሰል ከተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርትና በዚህ ከሠለጠኑ መምህራን ከሆነ፣ የሚማረውና ፈተና እያለፈ ከክፍል ወደ ክፍል ከዚያም ወደ ዩኒቨርሲቲ የደረሰው  ኢትዮጵያዊነትና ኦርቶዶክሳዊ ታሪክ ባልተመዘገበበት የላቲን ፊደል (ቁቤ) ከሆነ፣ ፖለቲካው የሚዘወረው ስልታዊ ጋብቻ ፈጽመው ታሪክንና የአገር ማንነትን እንደገና ለመሥራት ስልታዊ ጋብቻ በፈጸሙት በሶስቱ  መጋመድ፡- ማለትም በአክራሪ ዉሀቢያ ኢስላም፣ በአክራሪ ጀርመን ወለድ ናዚዊ ፕሮቴስታንትና በአክራሪ ሴኩላር (militant secularism) አቴይሰት(ኢአማኒን) የሶስትዮሽ ፍልስፍና (ኢትዮጵያን፣ ነባርነትን፣ ኦርቶዶክሳዊነትን ቢጠሉ) ሰዎች በሚመራ ትምህርት ከሆነ፣ ኦርቶዶክሳዊ-ኦሮሞን በሚጠላ አዲስ የ“ኦሮሙማ” ርእዮት በሚመራ ፖለቲካ ውስጥ ያደገ ከሆነ —- ይህ ልጅ እንዴት ከዚህ ሁሉ መርዝ ተርፎ ጤናማ አእምሮ፣ ፍትሐዊና እውነትኛ ስብእና፣ ከመንጋነት የተላቀቀ ራስን ሆኖ የመገለፅ አቅም አግኝቶና እትዮጵያ መንስ ለብሶ ተገኘ? እንዴት አልተመረዘም???
ይህን ጥያቄ የሚያስነሳው “ሰው የሚመገበውን ነው (ይሆናል)” የሚለውን የፌውርባችን ብሒል፣ የኦርቶዶክስን እውነት ከልቤ ተቀብዬ ነው። በኦርቶዶክሳዊያንም ትምህርት ሰው የበላውን ይሆናል። በሠይጣን የሐሰት ትምህርት ተመርተው እፀ በለስን የበሉ አዳምና ሔዋን እንደ መምህራቸው ሙት ሆነው የሕይወት ምንጭና መሠረት ከሆነው አምላካቸው ተለይተው ሞቱ፤ በሕሊና፣ በስብእና፣ በቅድስና ሁሉ ሙታን ሆኑ፣ የሚወልዱት ገዳይና ተገዳይ ሆነ። ሕያው የእግዚአብሔር ልጅን አየሱስ ክርስቶስን(እግዚአብሔርን) አምነው ሥጋውና ደሙን የተመገቡ እንደ አምላካቸው እንደ እግዚአብሔር ሕያዋን ሆኑ (ክርስቶሳዊያን ሆኑ)።  ፌዉርባች ሴኩላር ሰው ነው።  ቁስአካላዊነትን ብቻ የሚረዳ የጀርመኑ ፈላስፋና አንተሮፖሎጂሰት (ነገረሰብእ) ሰው  Ludwig Andreas von Feuerbach (German: 28 July 1804 – 13 September 1872) “The Essence of Christianity” በሚለውና ክርስትናን ክፉኛ የሚተች መጽሐፉ ይታወቃል። የዚህ ሰው አስተምህሮ ለትውልዶች እየተላለፈ ተጽእኖ አሳድሯል። ለምሳሌ በኋላ የተነሱት አሰላሳይ፣ ፈላስፋና ፖለቲከኞች እነ ቻርለስ ዳርዊን፣ ካርል ማርክስ፣ ሲገመንድ ፈሩድ፣ ፍሬደሪክ ኤንግልስ፣ ሪቻርድ ዋንገር (Artist, composer, writer)፣ ፍሬደሪክ ኒቼ   ወዘተ የበሉትና የሆኑትን የሆኑት ፌርባችን ነው።  ይህ ኢአማኒ እንኳ ሰው የሚበላውን አንደሚሆን ተገንዝቧል። እናም እንደተረዳው ሙት ምግብ ለተከታዩ ትውልድ አብልቶ ሙት የፖለቲካ ርእዮተዓለም፣ ነገረ-ሰብእና ሥነ-መንግሥት እንዲፈጠር  ብቸኛውም ባይሆን አንዱ ለመሆን ችሏል። የአገራችን የብሔር ፖለቲካ መርዝ መመንጨት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ምክኒቱብ በመደብና በግጭት የሚምነው የማርክስና ኤንግልስ አያትነውና።
  ፌርባች በ19ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ  “ሰው የበላውን ነው” የሚል የሚጠቀስለትን አባባል አስተዋወቀ።  አባባሉ አውነት ነው። የሰው የበላው ምንም ነገር ቢሆን ከደሙና ከሥጋው ይዋሀዳል። ነገሩን በጥልቀት ስንመረምረው ግን ፈዉርባች ሙሉ በሙሉ በቁስአካላዊነት የሚሠራ አእምሮ ያለው  በመሆኑ ለእርሱ ሰው ሥጋ፣ ደም፣ አጥንት ብቻ ነው። ይህን አባባል ጠጋ ብለን ስንመለከተው ምግብን ከሥጋና (ቁሳዊ) ከመንፈሳዊ አንፃር እንድንመለከተው ግድ ይለናል።
           ቁሳዊ አድርገን ስንመለከተው ሰው ጤናማ ደስተኛ ለመሆን የግድ  የተመጣጠነ ምግብ ያስፈልገዋል።    ምጥን ምግብ ለቁሳዊው የሰው ማንነት የግድ ይሆናል።   ቪታሚን፣ ማዕድናት፣ ኃይል ሰጭ ምግቦች ለጤና፣ ለእድገት፣ ለአጥንትና ለጥርስ ጥንካሬ፣ ለቆዳ ልስላሴ ወዘተ ያስፈልጋል።    ኃይል ሰጭ ምግብ የማያገኝ ሰው የእለት ተእለት ተግባሩን የመፈጸም አቅም ያንሰዋል፣ ፐሮቲን ከሌለው አካላዊ እድገትና የተጎዱ ሴሎችና ሕዋሳት አይጠገኑም።  ስለዚህ በቁሳዊ አካላችን ጤናማ ለመሆን የተመጣጠነ ምግብ መብላት አለብን።
            መንፈሳዊውን ዘርፍ በሚመለከት በፌውርባች ማያ (ማኅቀፈ-እሳቤ) ሃይማኖት ትርጉም የለሽ ነው።   እንደርሱ እሳቤ ከቁሳዊው ዓለም ውጭ ሌላ ዓለም የለም፣ ማሰብም ትርጉም የለዉም። ስለዚህ እግዚአብሔር እና ነፍስ የሉም።   በእርግጥ ትልቁ ፈላስፋ የሳተው እዚህ ላይ ነው።   ምክኒያቱም የሚበላው ሰውና የሚበላው ምግብ ሁለቱም በእግዚአብሔር የተፈጠሩ ሲሆኑ ሌሎች ፍጡራን  ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር በምግብነት ተባርከው የተሰጡ ናቸው።   አዎ! እኛ የበላነውን ነን! ግን መብላት የበላነውን ከሰጠን ፈጣሪ ጋር ያስተሳሥረናል።  ምግብ ፈጣሪ ለሰው ልጅ የሰጠው የፍቅሩ ማኅተም  በመሆኑ እኛ የተባረክን ሕዝቦቹ ነን።
ከፍጥረት ጀምሮ ሰው እንዲበላ ተደርጎና ፍጥረት ምግቡ ሆኖ የተሰጠው ፍጡር ነው። ዘፍ 2፣16 -17 “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ 17 ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።”
ፈጣሪ ሰውን ሲፈጥረው ረሀብተኛና መብላት የሚገባው አድርጎታል። እግኢአብሔር ሰው የሚገበውን ምግብ ሰው ራሱ በግዘፍ  ከተገኛባት ምድር፣ ነፋስ፣ እሳትና ውሃ ተገኝተው በሚባዙ እጽዋትና እንስሳት ሰጥቶታል። እርሱ ሰው ግን ከተገኘባቸው አራቱ ግዙፋን ባሕርያተ ሥጋ በተጨማሪ ሕያዊት ነፍስና ከእግዚአብሔር ከፈጣሪው ያገኛትን መንፈስ ገንዘብ አድርጎ ፍጡራንን ሁሉ በውስጡ የጠቀለለ በዓለም የሚኖር ነገር ግን ዓለመ-ዓለማት ነው።  ይህ ስጦታ ሕይወት የሚሆነው ሰው ሕይወት ከሆነው ፈጣሪው ጋር ሲሆን ብቻ ነው። ፍጥረታት በራሳቸው ከፈጣሪ ተለይተው ሕይወት የላቸውም። ከፈጣሪው ተለይቶ የሞተ ሰው፣ ለምግቡ የሚበላው ሌላ ፍጥረት ሁሉ ሙት ነው። ሙት ሙትን ቢበላ ሕይወት አያስገኝም።  በግዘፍና በደመንፍስ እየተንቀሳቀስ እነፌውርባች የሚረዱት ሮቦት መስሎ ለሥራ (አምራች)፣ ለሆድ (ኃይል የሚሆን ማገዶ)፣ ለርደቢ (ዝሙታዊ ግኑኝነት)፣ ለመንጋነት (አምላክ-የለሽ ፖለቲካ) ለዚህ ምድራዊ ፍትወት አገልግሎት ብቻ የሚኖር ከእንስሳትና ከአራዊት ያነሰ ይሆናል። ሆኗልም። ሆኖም ዓለምን በዘረኝነት፣ በትላቻ፣ በጦርነት፣ በስስት፣ ግባ በመጋባትና በማጋባት አበላሽቷል።
ከእግዚአብሔር ተለይተው የተፈላሰፉ የዓለም ታዋቂ ሰዎቸ ሁሉ ሙታን ናቸው። ሕይወት የሌለው ሙት ፍልስፍና አባዝተዋል። ከዚህ ፍልስፍናቸው ሙትና ገዳይ የፖለቲካ ርእዮት ተፈልፍሏል። አንዱ በአገራችን ደማችንን እያፈሰሰ፣ እያፈናቀለ፣ እየቀጠፈና እየዋሸ የሚመራንን ክፉ የሞት ፖለቲካመጤን ይቻላል።
ከአዳም ጀምሮ ብንመለከት የሰው ሞት የሚጀምረው በክፉ መምህር ስሁት ትምህርትን በመቅሰም ነው። የአዳምን ንሥሓና ፀፀት ለሩቅ ተስፋ ስነቅ  አድረጎ አምላክ ሰው ሆነ እንጂ የኖኅ ዘመን ሰዎች ክፉ ትምህርታቸው፣ ክፉ ሥራን አሰርቷቸዋል። ፈጣሪም አዝኖ ከክፉ ትምህርታቸው የተለየ ሀሳብ፣ ምግባርና ኑሮ ያለውን ኖኅና ቤተሰቦቹን አስቀርቶ የጥፋትን ውሃ  በማምጣት ዓለምን አጽድቷቷል።
ከኖኅ የልጅ ልጆችም በአባታቸው መንግድ የሄዱና ትምህርት ያልለወጡ አሉ። አዲስ ትምህርት አምጥተው መከራን የጠሩ ነበሩ። ከክርስትና በኃላም የሐዋሪያትን ፍጹም ትምህርት በመለወጥ አውሮጳን ወደ ተለያዩ አዳዲስ ትምህርቶች በመምራት በመጨረሻ ዳረዊንና ሌሎች የሰው ልጅን በዘር ከፋፍለው የሚያጋድሉ አንደ ሂትለር፣ ሞሶሎኒ፣ ኦቶማን ቱርክ ወዘተ አይነት ደም አፍሳሾችን ፈጠረ። ይህ ስህተት ሕገ መንግሥት፣ ሕገ አስተዳደርና የዓለም ተቋማትን እን ዩኔስኮንና የዓለም ባንክን ርእዮት ፈጠረ።
በአውሮጳ የተወለደውና አብርሆት የተባለለት ጨለማ “ሰውን ዝንጀሮ ነው፣ የምንመለከተው በዝግመተ ለውጥና በመላምታዊ ሙከራ ሂደት ውስጥ ራሱን እንደሚፈልግ እንስሳ ነው” በሚሉት ዓለም እንድትመራ ሆኗል። ይህ አመራር “ከዝንጀሮ ዝንጀሮ ይበልጣል” ወደሚልድምዳሜ በመድረሱ “የሚበልጠው የሚያንሰውን እንደተፈሮ ሃብት መጠቀም ይችላል” ወደሚል እብደት ዘቀጠ። ዝቅጠቱን እውቀትና ሳይንስ ለማስመሰል ኢዩጄኒዝም የሚባል በርእዮተዓለም የሚመራ እውቀት የተባለ ሐሰተኛ የዘረኝነት ሳይንስ ተፈጠረ።  ከዚህም  የዘር ጦርነቶች በአውሮጳ ጋመ፣ ቅኝ ገዥነት ሞራላዊና ተገቡ ተባለ፣ አንዱ ሌላውን ባሪያ የሚያደርግበት ሥርዓት ፀና፣ አውሮጳ አሜሪካና አውስተራሊያ ወርዶ ገና በዝግመተ ለውጥ ውስጥ የሚገኝ ፍጥረቱ ያላላቀልት ብሎ የፈረጀውን የቀይ ሕንዶችን ዝርያ አትፍቶ ሰፈረ፤ አፍሪካ መጥቶ ቅን ገዛ፣ ሂትለርንና ሞሶሎኒን አሳድጎ በሰው ልጆች የዝር ማጥፋት ዘመቻ አሠማራ፣ ማርክሲዝምን ፈጥሮ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ በማለት ንጉሥን ገደለ፣ጳጳስን ሰቀለ፣ ቀይና ነጭ በሚል የመገዳደል ብራንድ ትውልድን በሥጋም በአእምሮም ገደለ፣ ዝቅጠቱ ቀጥሎ የጎሣ ነፃ አውጭዎችን እንቁላል ጣለልን፣ እነዚህ ተፈልፍለው ዛሬ የምንቀበለውን የማንነት ፖለቲካ ጦርነት አፈሩልን።   ይህን ፍሬ አስወግደን በወደ ተፈጥሮአዊ ስብእና እንዳንመለስ የሚያደርግ  የዓለም ሕግና አስተሳሰብን ወጥ እንዲሆን የሚያስገድዱ ሕጎችን የሚስፋፉ የዓለም ኃያላን አንዚህን የእኛን አጥፊ ፍልፍሎች እየደገፉ ስቃያችንን አራዘሙት።
ሰው የሚበላውን ነውና አፍሪካ በተለይ ኢትዮጵያ በቀደመ ማንነቷ በአድዋና ከዚያም አስቀድሞ በእነ አጼ ሲሱኒዮስ ጊዜ የተሞከረውን አዲስ መንገድ ድል ነሻች። ባለ አዲስ መንገዶቹ ተቀየሙ፣ ቂም ያዙ።  በዘማነት ሂደት ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጀምረው እስከአዲስ አበባ ዩኒርሲቲ ዘልቀው አዲስ የአእምሮ ምግብ አቀረቡ። በአእምሮ በኩል ሕሊና፣ እምነትና ሰብአዊነት አዲስ ትርጉም አገኙ።
በአዲስ ልብና ሕሊና የሚመራው ትውልድ ነባሩን ሁሉ መረዳት ስለተሳነው ጠላው። ራሱን “ሳይማሩ ያስተማሩኝ” ያላቸውን ወገኖቹን በአዲስ ማያው እየመዘነ በአእምሮ ባርነት ውስጥ መያዙን ስለማይገነዘብ እኛን ነጻ የእግዚአብሔር አማኝ ሕዝቦችን “ዝንጀሮዎች ነን ለማሰኘት” “ነፃ” ላውጣህ የሚል መሲህ ሆኖ ቀረበ።
ለአገሩ እውቀት ባእድ የሆነና በባእዳን ማኅደርነት ለለክቶ የተሰፋ፣ በተውሶ ትምህርት ሊቅ የተሰኘ ሁሉ ራሱን መሲህ አደረገ፤  የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበረሰብ፣ የመሬት አጠቃቀም፣ የሰው ልጅ አካልና ብልት አጠቃቀም ሳይቀር እኔ በገባኝ ልክ ተረዱና ተጠቀሙ ወደሚል አስገዳጅ ሕግና ፖሊሲ ሊመራን ጠጋደለን። በዚህ ጉዞ ዛሬን አገኘን—
ዛሬ እውነትም የበላነውን ሆነናል።
– ግራ ገብቶናል
– በምንም ነገር እግጠኞች አይደለንም
– ከምንም የሩቅ ታሪካዊ ትውፊታዊ፣ እምነታዊና መዋቅራዊ ሀብታቶቻችን ጋር ግኑኝነት የለንም
– በማያቋርጥ፣ በማይጸድቅና በማያፈራ ንቅለ-ተከላ ተጠምደናል
– ዛሬ እንገዳደላለን — ማጥፋት እንጂ ማልማት፣ መለየት አንጂ መገናኘት፣ ማራራቅ አንጂ ማዋሐድ አናውቅም
– ለቤተሰብ ግጭት ሚኒስቴር፣ ለማኅበረ-ሰብ ግጭት አሜሪካ፣ ለሕፃናት አስተዳደግ የምሕራባዊያን ማኑአል፣ ለጽንስ አያዯዝና ወሊድ ዘመናዊ ዶክተር፣ ለሩካቤ የውጭ መድኀኒት ይቀርብልናል — ከሰውነት ወጥተን ሮቦትና ገበያ ሆነናል
 ምን ተመገብን/በላን?
እንደኔ ግንዛቤና እይታ እኛ ኢትዮጵያዊያን የበላነው
– ፈጣሪን የሚያስረሳ
– ሰውን ከሰውነቱ አውጥቶ የፖለቲካ ሥሪት ቡድነት በማድረግ ከፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ከተፈጠረበት የሕብረት-አንድነት ዓላማ የሚለይ
– ራስን የሚያስንቅ፣ ባእዳንን የሚያስናፍቅ
– ከእውነት የሚያርቅ፣ ሐሰት የሚያስወድድ
– ሕይወትን ውድድር፣ ሽሚያ፣ ቁማርና ቅሚያአድርጎ የሚተረጉምና ከሥን ምኅዳራዊ የተመጋጋቢነት ሕይወታዊ መንግደድየሚያስወጣ
– ከፈጣሪ የበለጠ ፍጡራንን አንደ አምላክ አድርጎ ለሆድ ሲባል ሕሊናን የሚያስቀብርና የፍጡር መንጋ የሚያደርግ  —- ምግብን ተመግበናል እላለሁ።
ከባባድ የሕይወት ጥያቄዎች በማንሳት ይህን ወጣት ላድንቅ ፈለግሁ፡-
(1) እና የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ዮሴፍ ከተማ  በተወለደባትና ባደገባት ግንደበረት ይህን አዲስ ክፉ ምግብ እየበላ፣ ቀዳማዊውን የአባቶቹን ታሪካዊ፣ መንፈሳዊና የየመንፈስና የቁስን የተዋህዶ ምግብ ሙሉ በሙሉ ሳያጣ፣ ሳይመረዝ እንዴተ ሊተርፍና በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጡትን የሰውነት ደረጃ ጠብቆ ተገኘ?
(2) ሰው የሚበላውን እንደሚሆን ከተግባባን ታዲያ በብዛት የሚቀርበው ቁሳዊ፣ አምላክ-የለሽ፣ ነፍስን የማያውቃት አዲሱን ምግብ እየበላ ዯደገ ይህ ወጣት በምንት ተአምራዊ ምትሕታት በነባሩ ምግብ የሚያድጉ ሰዎችን አይነት ሰዋዊ ማንነት ይዞ ሊገጥ ቻለ?
(3) አዲሱን የምዕራብና የአረብ ምግብ አቀላቅለው በልተው ከቁሳዊነትና ከመንፈሳዊነት ተዋህዶ በመለያየት ቁስ ብቻ ሆነው የቀሩትን ሙታን ሳይመስሉ — (ለስልት የተጋቡትን መርዘኞች ምግብ በመመገብ ቄሶችና መኖኮሳት ብሎም አንዳንድ ጳጳሳት ሳቀሩ ተመርዘዋል) ኦሮሞ  ሰው ሀኖ መገኘት እንዴት ተቻለ?
(4) የኦሮሞ መስጊድና የኦሮሞ ቤተክህነት ለመፍጠር የሚጥሩትን መርዘኛ ተከትለው የጠፉ የሃይማኖት መሪዎች ባሉባት አገር  ይህ ብላቴና መርዙን እንዲቋቋም ምን ረዳው?
እነዚህን ጥያቄዎች በትክክል ከመለስን ልጆቻችንን መርዝ ቢመገቡም ሳይሞቱ ሕያዋን የምናደርግበት ጥበብ ይገለጥልናል ብዬ አምናለሁ።
ለመሆኑ ከኢትዮጵያዊነት በተለይ በኦርቶዶክስ-ጠልነት የተሰለፈውን የፖለቲካ ርእዮት የሚመሩና የሚያስተምሩ  የኦሮሞ የንዑስ ማንነት የፖለቲካ ልሒቃን፣ ሰውን እስከ መግደል የሚጨክኑ ታጋዮችና  ሐሰትን ሳንሳዊ አስመስሎ ለማቅረብ የሚተጉ “ፈላስፋዎች”  ኦሮሞ “ሰው” መሆኑን ያምናሉ?
ለዚህ ጥያቄ ሶሰት ምላሽ ያለ ይመስለኛል፡-
 አዎ ብዙ ፖለተኪኞች ኦሮሞ “ሰው”፣ ሰው ብቻ (ሌላ እንዳልሆነ) ያምናሉ(እኔን ጨምሮ)፤ መንፈሳዊና ቁሳዊውን ያዋሐደ፣ ፈጣሪ ያለው፣ የሚበላውም ከፈጣሪው የተሰጠውና ሕይወቱ ከአምላኩ በተሰጠው ምግብ ውስጥ አብሮት የሚገኝ መሆኑን የሚያምኑን አያሌ ናቸው (አንዲትና ብቸኛዋን እውነተኛዋን ሃይማኖት አላቸውና)
 ጥቂቶች ደግሞ እንደ ፌውርባች ኦሮሞን ከሰውነት ለይተው ቁሳዊ ያደርጉታል፣ ከአንድ አዳማዊ ቤተሰብ የተለየ  “ሰው” መሆኑን ይክዳሉ፤ ልዩ ፍጡር ሊያስመስሉት ይጥራሉ፤
 አንዳንዶች ደግሞ ራሳቸውን አዋርደውና በመንጋነት ለመነዳት ፈቅደው ምንም ሳያሰላስሉ በኦሮምኛ ቋንቋና መናገር የቻል ሰው ሁሉ፣ የሐሰት ተስፋ ማቅረብ የሚችል ሁሉ በሚግታቸው ልክ “ኦሮሞ ሰው ብቻ ነው” ሲሏቸው አዎን የሚሉ፤ ሌላ ጊዜ “የለም ኦሮሞ አዳማዊ ሳሆን ራሱን የቻለ ልዩ ነው”  የሚል የተደረተ መጽሀፍ አንብነው የሚከተሉ ጥቂቶች አሉ።
ሁለቱን የመጨረሻ ምላሽ የሚሰጡት  የሚመሩት አንደም በስሑት ውጭ-ገብ የፌውርባች የልጅልጆች ፍልስፍና ነው ወይንም  ለወቅታዊ ፍተወታቸው መሰካት  በማድላት ኦሮሞን “የፖለቲካ ፍጡር” ብቻ አድርገው  የሚመለከቱ ናቸው።  አንዚህ ወገኖች ከፍተኛ ከድንቁርና የሚመነጭ ትእቢትና ትምህክት ያናወዛቸው በመሆናቸው ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ ባህልን የሚፈጥር፣ ሃይማኖትን ተምሮ የሚቀበል፣ ታሪክን የሚሠራና የሚመረምር፣ አስተዳደርና መንግሥትን ዘርግቶ መተዳደርና ማስተዳደር የሚችል ሙሉ ሰው መሆኑን በማረሳሳት እና በግልባጩ  ሕዝቡ ራሱ የአንዳች ባህል ሥርትና ውጤት፣ የቋንቛ እሥረኛ፣ የልሒቃን ትርክት  ሕንፃና የልሒቃን መንጋና መገልገያነት ሊያወርዱት የሚሹ ናቸው።  ኦሮሞ ግን ከማንኛውም ሌላ ክህለ ሕዝብ ያልተለዩ ሰዎች የፈጠሩት ታላቅ ማኅበረሰብ ነው፣ አባላቱም ከንደማንኛውም ሰው ያልተለየ አዳማዊ ሰው ነው።   ሥሑታኑ ይህን ላመስካድ ያላቸው መሣሪያ በጣም ደካማ ነው፡-
(1) ቋንቋ
(2) ባህል
(3) አሠፋፈር
(4) ታሪክና ትርክት
(5) የጨቋኝና የተጨቋን ማኅቀፈ እሳቤ
(6) መብል/ሀብት
ሰውነትን ለማጉላት ሳይሆን ለመለያየትና ለማዋረድ ለአገልግሎት የሚውሉትን እነዚህን ደካማ መሣሪያዎች አቅምአንዳላቸው ለማስመሰል  የሚጠቀሙበት ሌላዊ ተደራቢ ደካማስልት ጥላቻን ለማልማት ቂምን ፈጥሮ መንዛት፣  በሐሰተኛ ትርክት ሐሰተኛ ማንነት መፍጠር፣ በጉልበት ደካሞችን በማጥቃት በኦሮሞ ማኅበረሰብ ላይ ማነሳሰሳት፣ እንደ አውሎ ነፋስ የሚያንገላታና ወጣቶችን ከመንግድ የሚስወተጣ የፕሮፓጋንዳ ነፋስ መልቀቅ፣ ደም በማፍሰስ በሰዎች መካከል የልዩነት ግንብ ማቆም ወዘተ ናቸው። እነዚህ ልሒቃን ለዚህ ክፋታቸው ወደ ዘላቂ ፍልስፍና ማደግ ሲሉ የሰውን ልጅ ደም ይገብሩለታን፣ ከተማ አቃትለው አንደ እጣን ለሐሰተኛው አምላካቸው መሰዋዕት ያሳርጋሉ፣ የአስተዳደርና የመንግሥት መዋቅራትን በንዑስ ማንነት ፖለቲካ ሚዛን በሚመርጡት ባለሥልጣንሜሞሉታል፣ የትምህርት ሥርኣትና ዘቱን ይመርዙታል፣ ታሪክና ትርክቱን በሐሰታቸው ያደበዝዙታል፣ ለክፋታቸው አወዳሽ ዘፋንና ዘማሪ ይቀተርለታል፣ ከፈጣሪው የበለጠ ሆዱን የሚያገለግል ቄስና ሼኪይመለምሉለታል፣ ከክርስትናና እስልማና ውጭ የሆኑ በባህል ስም ሸፋፍነው አህዛባዊ የጣዖት አምልኮን ያለሙለታል። ለአምላካቸው ራሳቸውም ይሰዉ’ለታል፣ ሌላውንም የሰዉለታል
ግርምቴ እዚህ ላይ ነው፡-  የዚህ የጠቀስኩት መጽሐፍ  ጻሐፊ ሁለት ወጀብ ያሸነፈ ይመስላል፡-
(1) በብዛት በሚቀርበው ምግብም እየበላ ኖሮ አልተመረዘም
(2) በጩኸቱም ደንብሩ ሰውነቱን አላጣም — በመንጋነት አልተነዳም፣ በራሱ ጸንቶ ቆመ
በሚገርም ሁኔታ ኦሮሞ፣ ሰው፣ ፈጣሪውን የሚያውቅ፣ ቁስና መንፈስን በተዋህዶ የሚኖር == በአጠቃላይ በፈጣሪው እንደተፈጠረ በመገኘት በትምህርት ስም የባእድ ፍልስፍና ማኅደር ሆነው ግራ ከገባቸው ተለይቶ ታይቶኛል። የተመረዘው ትውልድ ማወቅ የሚገባው ኦሮሞ “ሰው” ብቻ ነው፤ ፖለቲካው ሊፈጥረው እንደሚሞክረው ሌላም ከሰው የተለየና የሚያንስ ወይንም የሚበልጥ አይደለም።  የእግዚአብሔር ፍጡር እንጂ  የፖለቲካ ፍጡር አይደለም። ቋቋ፣ የአሰፋፈር፣ የእምነት፣  የባህልና የአካል መልክ ሁሉ ከሰውንት የማያስበልጡና የማያሳንሱ  ንዑሳን ማንነቶች እንጆ  ጦርነት አሳውጀው የሚያገዳድሉ፣ የሚያሰድዱ ከአዳማዊ ሰውነት የሚልቁ ኤደሉም። የፌውርባች የልጅ ልጆች ፖለቲካ ያሳወራችሁ የፖለቲካ ልሒቃኖቻችን ተመልሳችሁ ሰው ብቻ ሁኑ። የንዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ራሱን ከሰውነት ሳያውርድ፣ መርዙን ሁሉ ተፍቶ ኦሮሞነቱን ከደማዊነቱ አስማምቶ እንደተገኘ ተመራምራችሁ አርሱን ምሰሉት!!!
ከፈጣሪ ሳይለዩ ሕይወት የሚሰጥ የሥጋና የመንፈስ ምግብ እየበሉ ለመልካምነት የሚደክሙትን ሕያዋን እግዚአብሔር  ያብዛልን።  ሙት ምግብ እየተመገቡ በሙት አእምሮአቸው በሞተ የንዑስ ማንነት ፖለቲካ አምልኮ ደማችንን የሚያፈሱትን፣ መከራችንን የሚዘልቁትን ስሑታን እግዚአብሔር ከድባቴ አንቅቶ ወደ ሕይወት ይመልስልን።
አሜን።
ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ.ም.   (በብሔራዊ ቲያቲር ለተዘጋጀው የመጽሐፍ ምርጋ ተዘጋጅቶ የነበረና በጊዜ መጣበብ በዕለቱ ሳይነበብ የቀረ)
Filed in: Amharic