>
5:13 pm - Wednesday April 20, 8811

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሕገመንግሥቱ እንደማይሻሻል አረጋገጡ!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሕገመንግሥቱ እንደማይሻሻል አረጋገጡ!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

  ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በአገዛዙ ሚዲያዎች የቀጥታ ስርጭት እንደተከታተላቹህት የሕዝብ ተወካዮች ከተባሉ ግለሰቦች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ጊዜ ነው ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሕገመንግሥቱ እንደማይሻሻል ያረጋገጡት!!!
በነገራችን ላይ ስርጭቱ የቀጥታ ስርጭት አልነበረም፡፡ ስብሰባው ከተጀመረ ከሐምሳ ደቂቃ በኋላ ነው የቀረጹትን የቀጥታ ስርጭት አስመስለው አላስፈላጊ ያሏቸውን ንግግሮች እየቆረጡ ሲያስተላልፉ የነበረው፡፡ ይሄ ነገር ከበፊት ጀምሮ የነበረ ዘዴያቸው የነበረ ቢሆንም አሁንም ለሕዝብ ታማኝ የሕዝብ ተወካዮች ባለመኖራቸው ይሄው መሠሪ አሠራር አሁንም ሊቀጥል ችሏል!!!
ወደ ነጥቡ ስመለስ   ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደምም “ለአንድ ክልል ብለን ሕገመንግሥቱን አናሻሽልም!” በማለት እንቅጩን የተናገረ ቢሆንም ዘገምተኛው መንጋ ግን ከየት አምጥቶ ተስፋ ሊያደርግ እንደቻለ አይታወቅም “ምርጫ ተደርጎ ዐቢይ በሕዝብ የተመረጠ ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆንና ሕጋዊ እውቅና ወይም legitmacy ሲያገኝ ሕገመንግሥቱን ያሻሽለዋል!” ብሎ ተስፋ ሲያደርግ እንደቆየ ይታወቃል!!!
  ዶ/ር ዐቢይ ዛሬ ከአንድ የፓርላማ አባል በድጋፍ ሞሽኑ ላይ “በክልሎች አንዳንድ ችግሮች በሚፈጠሩ ጊዜ የክልል መንግሥታት የፌዴራል መንግሥትን ጣልቃ እንዲገባ ጥያቃ ሲያቀርቡ የፌዴራል መንግሥት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ጣልቃ የሚገባ ይሆናል!” ለሚለው አንቀጽ “ባለፉት ጊዜያት የክልል መንግሥታት ችግሮች ሲፈጠሩ ለችግሮቹ መፍትሔ ለመስጠት ያልቻሉባቸውና ያልፈቀዱባቸው ሁኔታዎች የተስተዋሉ በመሆናቸውና ሆን ብለውም የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጥ ጥያቄ የማያቀርቡባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ስለሚታወቅ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ክልሎች የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ እስኪጠይቁ መጠበቅ የለበትም፡፡ ጉዳዩ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የፌዴራሉ መንግሥት ያለ ክልሎቹ ጥያቄ ጣልቃ በመግባት ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ይኖርበታል!” በማለት ለቀረበላቸው የሞሽን ማሻሻያ ጥያቄ መልስ በሰጡበቅ ወቅት ነው ሕገመንግሥቱ እንደማይሻሻል ያረጋገጡት!!!
  ዶ/ርዐቢይ አሕመድ ለዚህ ተገቢ የሞሽን ማሻሻያ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ “ሕገ መንግሥቱ እያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ሰጥቶበት በስምምነት እስኪሻሻል ድረስ ሕገመንግሥቱን ማክበር ይኖርብናል፡፡ ስለሆነም ጣልቃ ለመግባት የክልሎች ጥያቄ አስፈላጊ እንደሆነ ይቀጥላል….!” በማለት በሰጠው መልስ ነው ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሕገመንግሥቱ እንደማይሻሻል የገለጡት!!!
በርካታው ሰው ግን ይሄ አልገባውም፡፡ አቶ ዐቢይ አገዛዙ የአማራ ክልል ከሚለው የሀገሪቱ ክፍል በስተቀር ሌሎቹ ክልል የሚሏቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ሕገመንግሥቱ እንዲሻሻል እንደማይፈልጉ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እንኳን የአገዛዙ የክልል መዋቅሮች ይቅርና አገዛዙ የአማራ ክልል ከሚለው የሀገራችን ክፍል ካለው ሕዝብ ውጭ በተቀረው የሀገራችን ክፍል የሚኖረው ሕዝብ እራሱም ከጊዜ ወደጊዜ በአገዛዙ መርዘኛ የጠባብ ብሔርተኝነት ስብከት እየተመረዘ ስለመጣና ኢትዮጵያንና አንድነትን እንዲረሳ እንዲሁም እንዲጠላ ስለተደረገ ወይም ከኢትዮጵያ በላይ “ክልሌ!” የሚለውን እንዲወድ ስለተደረገ የዚህ ጠንቀኛ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ሰነድ የሆነው የወያኔ ሕገመንግሥት ከፋፋይና ጠንቀኛ አንቀጾች “ይሻሻሉ ወይ?” ተብሎ ቢጠየቅ እንደ ልኂቆቹ ሁሉ እሱም “አይሆንም አይቀየርም!” የሚል መሆኑን ወይም ሙሉ በሙሉ ባይባልም አብዛኛው የየሕዝባቸው ክፍል የማይቀበለው መሆኑን ለመረዳት በየክልሉ ያለውንና የተንሰራፋውን የጠባብነትና የጥላቻ መንፈስ መመልከት ብቻ በቂ ነው!!!
ስለሆነም   ዶ/ር ዐቢይ በሚለው መንገድ ሕገመንግሥቱ ፈጽሞ ላይሻሻል ነው ማለት ነው፡፡ ይሄንንም ስለሚያውቅ ነው “ለአንድ ክልል ብለን ሕገመንግሦቱን አናሻሽልም!” በማለት አስቀድሞ የተናገረው አቶ ዐቢይ አሕመድ ሕገመንግሥት የሚለው ፀረ ኢትዮጵያ የውንብድና ሰነድ እንዲሻሻል ስለማይፈልግ “እያንዳንዱ ዜጋ ተጠይቆ ድምፅ ከሰጠ በኋላ ስምምነት ከተደረሰ!” በማለት በሕዝበ ውሳኔ የማሻሻል መንገድን የመረጠው!!!
ዘገምተኛው መንጋ ግን ሕገመምግሥቱ ጠንቀኛ መሆኑ ታምኖበት በመግባባትና በፖለቲካዊ ውሳኔ ነው “ይቀየራል!” ብሎ ተስፋ ያደርግ የነበረው እንጅ   ዶ/ር ዐቢይ እንዳለው እያንዳንዱ ዜጋ “ሕገመንግሥቱ ይሻሻል ወይስ አይሻሻል?” በሚል ድምፅ ተሰጥቶበት አልነበረም “ዐቢይ ሕገመንግሥቱን ያሻሽልልኛል!” ብሎ ተስፋ ሲያደርግ የቆየው!!!
ዘገምተኛው መንጋ ይሄንን ብቻ አልነበረም “ዐቢይ ያደርግልኛል!” ብሎ ተስፋ ሲያደርግ የነበረው፡፡ “የጎሳ ፖለቲካንም ከሀገራችን ያጠፋልኛል!” ብሎም ነበር ተስፋ ያደርግ የነበረው!!! ነገር ግን የጎሳ ፖለቲካም እንደማይቀር አገዛዙ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ አድርጎ በሾመው በአቶ አገኘሁ ተሻገር በኩል “በብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መብትንና ፈቃድን የሚያረጋግጥ በመሆኑና በግዳጅ አለመሆኑን ስለሚያረጋግጥ በዚህ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት የሕዝቦችን መብት ለማረጋገጥ እንሠራለን…!” ብሎ ከገለጸው ተረድታቹሃል!!!
  ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዚህ “ሕገ መንግሥቱ እያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ሰጥቶበት በስምምነት እስኪሻሻል ድረስ ሕገመንግሥቱን ማክበር ይኖርብናል፡፡ ስለሆነም ጣልቃ ለመግባት የክልሎች ጥያቄ አስፈላጊ እንደሆነ ይቀጥላል….!” በሚለው መልሳቸው ሌላ ያረጋገጡት አደገኛ ነገር ባለፈው ሦስት የመከራ ዓመት የፌዴራል መንግሥት ተብየው “ክልሎች ከአቅሜ በላይ ነው የፌዴራል መንግሥት እገዛ ያድርግልኝ ሳይል በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ አልገባም!” እያለ ወገኖቻችንን ሲያስፈጅ የቆየበትን ዕኩይና ሸፍጠኛ አሠራር የሚያስቀጥል መሆኑንም ጭምር ነው   ዶ/ር ዐቢይ ያረጋገጠው!!!
እጅግ የሚገርመው ነገር ግን ክልል ተብየዎቹ ሊፈቱት ያልቻሉት ችግር ካለና በአንድም በሌላም ምክንያት የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች ማስከበር ካልቻሉ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ መፍትሔ መስጠት እንደሚችል በሕገመንግሥት ተብየው አንቀጽ 74፣ 77፣ 93 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95ዓ.ም. ተደንግጎ እያለ ነው እንግዲህ አገዛዙ እነኝህ ድንጋጌዎች እንደሌሉ አድርጎ “ጣልቃ አልገባም!” እያለ ወገኖቻችንን ሲያስፈጅ በቆየበት መንገድ መቀጠል ስለሚፈልግ አሁንም የፌዴራል መንግሥት ያለ ክልሎች ጥያቄ ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅዱ ድንጋጌዎች ቢኖሩም አቶ ዐቢይ እንደሌሉ አድርጎ የገለጸውና “ሕገመንግሥቱ እያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ሰጥቶ እስኪሻሻል ድረስ በነበረው አሠራር ይቀጥላል!” ሲል የተናገረው!!! አያሳዝንም???
የሚገርመው ነገር አገዛዙ የአማራ ክልል ወደሚለው ግን ያለ ክልሉ ጥያቄ፣ ፈቃድና እውቅና እንደፈለገ እየገባ የፈለገውን ሲያደርግና እንዴት ሊገባ እንደቻለ ሲጠየቅ ግን ያለ ክልሉ ጥያቄ፣ ፈቃድና እውቅና መግባት እንደሚችል ሲናገር የቆየው እነኝህን ድንጋጌዎች በመጥቀስ ነው!!!
በመሆኑም አገዛዙ እነኝህን ድንጋጌዎች ያስቀመጣቸው የአማራ ክልል ወደሚለው እንደፈለገ ለመግባትና የፈለገውን አድርጎም ለመውጣት ብቻ ነው እንጅ በሌሎች ክልል በሚላቸው የሀገራችን ክፍሎች በዜጎች ላይ ከባባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ የዜጎችን የሰብአዊ መብትና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አይደለም ማለት ነው!!! አያሳዝንም???
Filed in: Amharic