>

ጠያቂ... ተጠያቂ... ተጠያያቂ  (በእውቀቱ ስዩም) 

ጠያቂ… ተጠያቂ… ተጠያያቂ

(በእውቀቱ ስዩም)

በቀደም ዩቲዩብ ላይ ስርመሰመስ አንድ ለየት ያለ ፕሮግራም አየሁ፤ ሁለት አርቲስቶች  መድረክ ላይ ይቀርቡና  ርስበርስ ቃለ መጠይቅ ይደራረጋሉ፤ ይካካባሉ ፤ ይሸነጋገላሉ ማለት  ይሻላል :; ቃለ መጠይቁ  በገሀዱ አለም ያለውን እውነታ አያንጸባርቅም!  በገሀዱ አለም፤ አርቲስት አርቲስትን ይቦጭቃል፤ አርቲስት ባርቲስት ላይ ይሸምቃል፤ አርቲስት እና አርቲስት እሳትና ጭድ ፥ አቤልና ቃየል፤   ኦባማና ቢንላዲን  ናቸው::   በጠቅላላውም ባይሆን ባመዛኙ  “ እንዲል መንጌ ::
ባነሳሁት ፕሮግራም   ላይ ወንድና ሴት አርቲስቶች ቀርበዋል፤ እና ወጋቸው እንደሚከተለው አካባቢ ነው  ፥
 እሱ –   ጎበዝ ተዋናይት መሆንሽ  መላው አለም የመሰከረው ሀቅ ነው ! በበጎ አድራጎት ስራሽ  ትንሿ አበበች ጎበና የሚል ስያሜ አግኝተሻል፤  ቁንጅናሽም በጣም  አደገኛ ነው!  ትዝ እሚለኝ የመጀመርያ ፊልማችንን ስንሰራ ፤  አንድ ካሜራማን ከጣራ ላይ ሆኖ ሲቀርጽ ውበትሽ ስቦት ተከሰከሰ!  በአደጋው   ካሜራማኑ ግራ እግሩን ፤ ፕሮዲሰሩ  ካሜራውን  ሊያጣ ችሏል !  ይሄ ከምን   የመነጨ ነው ትያለሽ?
 እሷ –  ያው የፈጣሪ ጸጋ ነው  !  አንተም  ከትወናህ ውጭ ህብረተሰቡ እማያውቀው  ብዙ ተሰጥኦ አለህ፤  ስትሰብክ እንደመጋቢ ሀዲስ ፤ ስትጽፍ እንደ አቶ ሀዲስ ነህ!  ሙያህ አክተር ! ማእረግህ ተጠባባቂ ክቡር ዶክተር!  ግርማ ሞገስህ እንደ ሃይለስላሴ ፥ ደምጽህ እንደ አለምነህ ዋሴ !   በዚህ  ድምጽህ  ህገመንግስቱን ብትተርክልኝ ራሱ አይሰለቸኝም!  ይህንን  ሌላም ሰው ብሎህ ያውቃል?
  እሱ፤-  መስማት የተሳናቸው ሰዎች ሳይቀሩ እንደዛ ይሉኛል!   ፊልሙን በምንሰራበት ጊዜ በጣም ብዙ ውጣ ውረድ አይተናል፤ በተለይ አንቺ የከፈልሺው መስዋእትነት አይረሳኝም፤ አንዳንዴ በስራ ከመጠመድሽ የተነሳ የረባ ምግብ እንኳ  የምትበይበት  ጊዜ እያጣሽ   ሁለት  ቢቸሬ ጭማቂ   አንድ መካከለኛ  ሰሀን ቅንጨ፥   አንድ ትሪ ፍርፍር ለኮፍ ለኮፍ አድርገሽ ቀምሰሽ የምትውይበት ጊዜ ነበር! ይሄ ጽናት ከምን የመነጨ ነው?
 እሷ፤-   የፊልም  ስክሪፕት የምታጠናበት ፍጥነት ብዙ ጊዜ ያስደምመን ነበር፤ አንዳንዴ ደራሲው  ፊልሙን  ከመጻፉ በፊት አንተ ስክሪፕቱን አጥንተህ  ትመጣ ነበር፤  ሌላው ድንቅ የሚለኝ ነገር  ቀረጻ በተጀመረ ባስረኛው ደቂቃ ላይ ሰውነትህ በላብ ይታጠባል!   ያ ሁሉ ላብ ከምን የመነጨ ነው?
 እሱ- ከልምድ የመነጨ  ይመስለኛል :;
እሷ- በመጨረሻ ለወጣቱ  የምታስተላልፊው መልክት  ካለ፥
  እሱ – መጀመርያ አንቺ አስተላልፊና የተረፈውን እኔ አስተላልፋለሁ  ::
ከዚህ በተቃራኒ ትዝ የሚለኝ የዋልታው ጋዜጠኛ  የስሜነህ ቢያፈርስ ቃለመጠይቅ ነው፤  ስሜነህ  ስቱዲዮ ውስጥ ተቀምጦ፤  መዝገበ- ሀጢአት  የመሰለች ማስታወሻ ደብተሩን ገለጥ ገለብ ያደርጋል፤ ከዚያ  ቀና ብሎ ከፊትለፊቱ ያለውን እንግዳ በሚያስቦካ አስተያየት ያፈጥበታል፤  እና ወደ አእምሮው የሚመጣለት ጥያቄ እንዲህ የሚል ይመስለኛል፤
“ ጥሪየን  አክብረው ስለመጡ አመስግናለሁ፤ ደደብ ነዎት እየተባለ በሰፊው ይነገራል፤ እርስዎ ምን አይነት ደደብ ደረጃ ላይ ራስዎን ያስቀምጣሉ?  ከመጽሀፍና ከመከራ መማር የሚችል ደደብ ነዎት? ወይስ  ጭንጫ ደደብ ነኝ ብለው ያስባሉ? ወይስ ጭራሽ አያስቡም?”
Filed in: Amharic