>

ድብቁ የሳኡዲ አጀንዳ በኢትዮጵያ ላይ፣የግብጽና ሳኡዲአረቢያ ኢትዮጵያን የማዳከም ስትራቴጂ ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ድብቁ የሳኡዲ አጀንዳ በኢትዮጵያ ላይ፣የግብጽና ሳኡዲአረቢያ ኢትዮጵያን የማዳከም ስትራቴጂ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


እንደ መግቢያ

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መስከረም 7 2021 ግብጽን የጎበኘው ብሩንዳዊው  የኤፍኤም ራዲዮ ጋዜጠኛ  አልበርት ሺንጊሩ (Albert Shingiro) እንደተናገረው ከሆነ ለግብጽ የውሃ አቅርቦት ሊስተጓጎል የማይቻለው፣ ኢትዮጵያ በድህነት ስትዳክር ማየት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህቺ ሰሜን አፍሪካዊት ሀገር በቂ ውሃ ስለማግኘቷ ሳይሆን የምትጨነቀው፣ ኢትዮጵያ የበለጸገች ሀገር እንዳትሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዝንተ አለም ከድህነት አረንቋ እንዳትወጣ ነው፡፡ ምንም እንኳን   አንደነቷ በተጠበቀ ኢትዮጵያ፣ የህዝቧ የኑሮ እድገት የተሻለ በሆነባት ኢትዮጵያ ወደ ግዛቷ የሚፈሰው የአባይ ወንዝ የውሃ ሊጎዳት በሚያስችል መጠን ሊቀንስ እንደማይችል ብትረዳም፣ ግብጽ ለብዙ ዘመናት ያለምንም ከልካይ በቂ የውሃ አቅርቦት እንዳላት ልቦናዋ ቢያውቅም፣ ለወደፊቱም ቢሆን አስተማማኝ የውሃ መጠን እንደሚኖራት የታወቀ ቢሆንም ኢትዮጵያ ወደ ልማት ጎዳና ለመገስገስ መፍጨርጨር በማሳየቷ ብቻ የውሃ አቅርቦቴ ሊቀንስ ይችላል ወይም ይቀንሳል በሚል የምተሸርበው ሴራ ምክንያታዊ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ  ወደ ሱዳንም ሆነ ግብጽ የሚፈሰውን የአባይ ወንዝ ውሃ መጠን ለመቀነስ ፍላጎትም ሆነ እቅድ እንደሌላት ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡

ግብጽ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባቷ ምክንያት የናይል ወንዝ የውሃ መጠን ይቀንሳል የሚል ስጋት እንደሌላት ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ የግብጽ መሰረታዊ ችግር  ለወደፊቱ ላሰበችው እና ላቀደችው ታላላቅ የመስኖ እርሻ ፕሮዤ ማለትም በሲናይ በረሃ እና በሌሎች አካባቢዎች ለምትገነባው የመስኖ እርሻ ፕሮዤ የውሃ አቅርቦት ችግር ወይም የውሃ እጥረት ሊያጋጥመን ይችላል የሚል ብርቱ ስጋት አላት፡፡ ግብጽ በየግዜው አዳዲስ የመስኖ ልማት ፕሮዤዎችን ገቢራዊ ከማድረግ ተቆጥባ አታውቅም እኛ አርስበርሳችን ስንተራመስ፣ስንጠቋቋም፣ አለም ወደ የታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ የዶለውን ፣ አፋጀሽኝ የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ መርዝ ተሸክመን፣አንዱ ለሌላኛው ወንድሙ ጉድጓድ ሲቆፍር፣ ግብጻውያን ግን በአንድነት መንፈስ፣ በብሔራዊ ስሜት ሀገራቸውን ገንብተዋል፣እየገነቡም ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያም ሆነች ግብጽ የረዥም ዘመን የስልጣኔ ታሪክ ያላቸው ሀገር የታወቀ ነው፣ግብጽ በታላቋ ብሪታኒያ በቅኝ ተገዝታ የተቀጠቀጠች ሀገር ብትሆንም፣በአንጻሩ ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎች ያልተገዛች፣ቅኝ ገዢዎችን አሳፍራ፣አሸንፋ ያባረረች ሀገር መሆኗ በታሪክ ፍንትው ብሎ የተቀመጠ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  የታሪክ ፌዝ ሆነና የቅኝ ገዢዎች ውርዴ በሆነው የጎሳ ፖለቲካ በመከፋፈላችን ግብጽ በውስጥ ፖለቲካዊ ህይወታችን ውስጥ ለመፈትፈት መብቃቷ ሲታሰብ ያማል፡፡

የግብጽ ችግር ውሃ አይደለም፣ሆኖም ግን ይሁንና የወደፊቱ ልማትና የበላይነቴን አጣለሁ የሚል ስጋት ነው

በአሁኑ ግዜ ኢትዮጵያ የምታስገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወደ ግብጽ የሚፈሰውን የናይል ወንዝ የውሃ መጠን እንደማይቀንሰው የመስኩ ባለሙያዎች በሰፊው የሄዱበት ጉዳይ ነው፡፡ የውሃው መጠን ሊቀንስ የሚችለው ከአባይ ወንዝ ወደ ግድቡ ውስጥ እንዲገባ በሚደረግበት ግዜ ነው፡፡ ( ወደ ግድቡ ውሃ በሚገባበት ግዜ ማለቴ ነው፡፡)  ማለትም ከአባይ ወንዝ ወደ ግድቡ ውሃ እንዲገባ የሚደረገው ከባድ የዝናብ መጠን በሚዘንብበት ሐምሌ ክረምት ወራት ከመሆኑ ባሻግር፣በቂ የከርሰ ምድር የውሃ ክምችትም ሆነ የግድብ ውሃ ሀብት ያላትን ግብጽ የሚጎዳት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ግብጽን በብርቱ የሚያስጨንቃት በመጪዎቹ አመታት ልትገባ ያሰበቻቸው ታላላቅ የውሃ ፕሮዤ ልማት ይስተጓጎልብኛል፣ በአከባቢው የነበረኝ የበላይነት ይቀንሳል የሚለው አቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ታላቁን የአባይ ወንዝ ግድብ መገንባት እንደጀመረችው ሁሉ፣ሌሎች የመስኖ ፕሮዤዎችን ገቢራ ለማድረግ ደፋ ቀና እንደምትለው  ሁሉ፣ ግብጽም በበኩሏ የሲናይ በረሃን ለማልማት፣ እንዲሁም በምስራቅ የግብጽ ክፍል ደግሞ የናይልን ወንዝ ተከትሎ የሚገነባ፣አዲስ ትልቅ ከተማ መስርታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ለማስፈር የልማት እቅድ ዘርግታ መጓዝ ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል፡፡ የግብጽ መንግስት፣ የናይልን ወንዝ በዘመናዊ ዘዴ በመጥለፍ፣እንዲሁም  ግብጻውያን ደግሞ በጎሳ ሳይከፋፈሉ በህብረትና አንድነት በመስራታቸው ከብዙ አፍሪካውያን እና የአለም ሀገራት ሳይቀር የተሻለ ህይወት መምራት መቻላቸው አይሸፈጥም፡፡ ኢትዮጵያውያን ግብጽን ብቻ ከመወቅስ፣ግብጽ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማናጋት ትሰራለች በማለት ማላዘን ብቻውን እንዳልጠቀመን ተገንዝበን፣ ከምንም ነገር በላይ አንድነታችንን እንድናጠናክር እማጸናለሁ፡፡ በፍጥነት ከጎሳ ከረጢት ውስጥ መውጣት ይገባናል፡፡ ከጊዚያዊ የፖለቲካ ስካርና ጥቅም  ይልቅ ህብረታችን እና አንድነታችን ይበጀናል፡፡

ግብጽ የኢትዮጵያን ታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ  በተመለከተ  ለሳኡዲአረቢያ የተሳሳተ መረጃ ስለማቀበሏ

በተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት የበለጸገችው ሳኡዲአረቢያ ከግብጽ ጋር የልማት ትብብር በማድረግ አና ከግማሽ ትሪሊዬን ዶላር በላይ በማፍሰስ ‹‹ኒኦም›› የተሰኘ ታላቅ የመስኖ ልማት ውሃ ፕሮዤ ግንባታ በሲናይ በረሃ ላይ ከጀመረች አመታት ነጎዱ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የተባበረችው አረብ ኤሜሪትስና ኩዌት ዋነኞቹ የግብጽ የልማት አጋሮች ናቸው፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገሮች አይንሽን ላፈር የተባለችው እስራኤል ሳትቀር የወደፊቷ አንዷ የግብጽ የልማት ክንፍ ናት፡፡ በተለይም እስራኤልና ግብጽ በሲናይ በረሃ ልማት አኳያ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በግብጽ ምድር ሳኡዲአረቢያ ለኢንቨስትመንት ያፈሰሰችው ረብጣ የአሜሪካን ዶላር ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ማለት ይህች ሀብታም አረብ ሀገር በግብጽ የኢንቨስት ልማት ገቢራዊ ካደረጉ ሀገራት መሃከል ከፍተኛ ምዋለንዋይ አፍሳሽ ሀገራት መሃከል ሁለተኛዋ  ለመሆን በቅታለች፡፡ ሳኡዲ በግብጽ ምድር ከምታከናውነው የልማት እንቅስቃሴ ባሻግር የናይል ወንዝን ጥቅም ላይ በማዋል በዮርዳኖስ እና ግብጽ ድንበር አኳያ ከፍተኛ የመስኖ ልማት ለማከናወን አቅድ ዘርግታ መንቀሳቀስ ከጀመረች አመታት ነጎዱ፡፡ (በነገራችን ላይ ሳኡዲ ለዚህ ታላቅ ፕሮዤ እውን መሆን ከ500 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ አፍስሳለች፡፡)

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ህዝቧን ከጨለማና ችጋር ነጻ ለማውጣት ስትል የምትገነባውን ታላቁን የአባይ ግድብ በተመለከተ፣ ግብጽ ለሳኡዲአረቢያ፣እስራኤልና ለሌሎች አረብ ሀገራት የምትሰጠው መረጃ ፍጹም የተሳሳተ ነው፡፡ በግብጽ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ታላላቅ የውሃ ግድቦችን በመገንባቷ ወደ ግብጽ ምድር የሚፈሰው የናይል ወንዝ ውሃ መጠን ይቀንሳል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ከግብጽ ጋር የልማት አጋርነት የመሰረቱትን ሀገራት ኢትዮጵያ ጥቅማችሁን የሚጎዳ ልማት እያካሄደች ነው በሚል ኢትዮጵያ ላይ ጠላቶችን ታበዛለች፡፡

በዚህና በሌሎች ታሪካዊ ምክንያቶች የተነሳ ሳኡዲአረቢያ በኢትዮጵያ ላይ የጥቃት ሰበዟን መሰንዘሯ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህች በነዳጅ ሀብት የሰከረች ሀገር የታላቁን የአባይ ግድብ ፕሮዜ ለማሰናከል እረጅም እርቀት መጓዟ እሙን ነው፡፡ ለአብነት ያህል ከእኩይ ድርጊቶቿ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡

  • ለአሸባሪው የወያኔ ዘራፊ እና ነውረኛ ቡድን በብዙ መልኩ መርዳታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው
  • ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ያላት የዲፕሎማሲ የበላይነት አንደኛው ሚስጥር የሳኡዲ የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ ሳኡዲ ሎቢስቶችን በዶላር በመግዛት በኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻ በግብጽ በኩል ከፍታለች፡፤( በዲፕሎማሲ አኳያ የግብጽ መንግስት ያሉትን የዲፕሎማሲ እውቀት ባለቤቶችን ሳንዘነጋ ማለቴ ነው)
  • በሳኡዲአረቢያ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ በብዙ አስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ የቤት ሰራተኞችን፣ሴቶችን፣ህጻናትን ማበረሯ የሚያሳየን ነገር ቢኖር በቀልተኝነቷን ነው፡፡ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ማዳሸቅ ሌላኛው ስልታቸው ነው፡፡ ከረዥም አመታት በፊት ማለትም በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንስት በርካታ አረቦች  በኢትዮጵያ ምድር ተከብረው፣ሱቅ ፣የጨርቃጨርቅ መደብሮች፣ዳቦ ቤትና ፉል ቤቶችን ከፍተው በተድላና በደስታ እንዳልኖሩ፣ ዛሬ የታሪክ ፌዝ ሆነ እና ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ ምድር በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ተቀጥረው እንዳይሰሩ መከልከላቸው ሲስተዋል፣ በሳኡዲ እስር ቤቶች በርካታ ኢትዮጵውያን በግፍ መታሰራቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ መታየቱ ሀዘናችንን ያከብደዋል፡፡
  • ስለሆነም የግብጽ መሰረታዊ ችግር  ወይም ፍላጎቷ የውሃ እጥረት ወይም የውሃ አቅርቦት ሊቀንስ ይችላል የሚለው ቁምነገር አይደለም፡፡ ግብጽን በእጅጉ እንቅልፍ የነሳት ጉዳይ ቢኖር  በዋነኛነት በሳኡዲ እርዳታ፣እንዲሁም ከአስራኤልና ሌሎች አረብ ሀገራት ጋር በመተባበር የናይል ወንዝን የበለጠ ጥቅም ላይ ለማዋል ያሳበችውና ያቀደችው ታላቅ ውጥን ይሰተጓጎልብኝ  ይሆን ? የሚለው አቢይ አጀንዳዋ ወይም ጥያቄዋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ፣እስራኤልና ሳኡዲ አረቢያ ከግብጽ ጋር አጋር በመሆን ሊገነቡ ያሰቧቸውን ታላላቅ ፕሮዤ ያሰናክላል የሚለው የግብጽ መሰሪ ተንኮል በሁለቱም ሀገራት መንግስታት(በእስራኤልና ሳኡዲአረቢያ ማለቴ ነው) ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ይህ የግብጽ ማስፈራሪያ በርካታ ሀገራትን ከጎኗ ለማሰለፍ አስችሏታል፡፡ በተለይም ሳኡዲአረቢያ በተሳሳተ መንገድ እንድትጓዝ አድርጋታለች፡፡ በእርግጥ የታላቁ አባይ ግድብ ግንባታ፣ የግብጽን የመስኖ ልማት ፕሮዤ የሚያሰናክል አልነበረም፡፡ አሁን ድርስ ግብጽ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በጣሰ መልኩ ስምምነት እንዲደረስ ትፈልጋለች፡፡ የቆየ አለማዋም ይሄው ነው፡፡ የግብጽ አላማ ግልጽ ነው፡፡ የወደፊቱ የኢትዮጵያ ትውልድ እስረኛ እንዲሆን ፍላጎቷ ሲሆን ፣ በናይል ወንዝ ላይ እርሷ ብቻ ለዘለአለም መጠቀም የምትፈልግ ስግብግብ አገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ አጋጥሟት በነበረው የዲፕሎማቲክ ክሽፈት ዋጋ አስክፍሏታል  

ኢትዮጵያ  ተጨባጩን  አውነታ ለሳኡዲአረቢያና ሌሎች ሀገራት ለማስረዳት ፣ ከዲፕሎማሲ አኳያ ማለቴ ነው፡፡ እንዳልተሳካላት በብዙ አዋቂዎች የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሳኡዲ አረቢያ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ካገኘችው ረብጣ ዶላር በመምዘዝ ኢትዮጵያን ለማናጋት ለሚራወጡ እኩይ ቡድኖች እረድታለች፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማንኮታኮት ብዙ ርቀት ተጉዛለች፡፡ በግብጽ ውትወታ አሸባሪውን የወያኔ ቡድን በገንዘብ ደግፋለች፡፡ በሳኡዲ አረቢያ በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ሰላማዊ ዜጎች፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ልጆቻቸውን ጭምር ከአለም የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት  ተጻራሪ በሆነ መልኩ ከሀገሯ ምድር በግፍ በግድ አባራለች፡፡ በ10ሺህ የሚቆጠሩ ቀን የጎደለባቸውን ኢትዮጵያውያንን በህገወጥ መንገድ እስር ቤቶች ውስጥ በማጎር እያሳቃየችም ስለመሆኑ እንደ ነቢዩን የመሰሉ አንጋፋ ጋዜጠኞች በየግዜው ለአለም የናኙት አሳዛኝ ዜና ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ምግባሯ ሳኡዲአረቢያ የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነትን የጣሰች ዋነኛዋ ሀገር ናት፡፡ የዛሬን አያድርገውና ያንዬ በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት በርካታ የአረብ ሀገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ምድር ከመጡ በኋላ በክብር ሱቆች፣ሻይ ቤቶች፣ዳቦ ቤቶች፣የሙዚቃ ቤቶች፣ ጨርቃጨርቅ መሸጫ ሱቆችን ከፍተው ኑሮአቸውን ማሻሻላቸው እውነት ነው፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ የታሪክ ፌዝ ሆነና ዛሬ ኢትዮጵያውያን በአረቡ አለም ከግርድና አቅም ሳይቀር የመስራት መብታቸው ተገፎ ማየቱ ህሊናን ያደማል፡፡ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡የኢትዮጵያውያን ውለታ ይሄ አልነበረም፡፡ ህሊና ያልፈጠረባቸው የሳኡዲአረቢያ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ግን በኢትዮጵያዊ ሰራተኞች ላይ ግፍ ፈጸሙ፡፡ በነገራችን ላይ አጠቃላዩን የሳኡዲአረቢያ ህዘብ መውቀስ ተገቢ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል አበጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስትም ሆነ በኮሎኔል መንግስቱ አገዛዝ ዘመን በተለይም ኤርትራውያን ወንድሞቻችንና  የነቁ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወደ ሳኡዲአረቢያ ምድር በመሄድ ለፍተው ግረው የሀብት ማማ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ዘመን በሳኡዲ አረቢያ ምድር ከ2 ሚሊዮን በላይ የግብጽ ዜጎች ሰርቶ የመኖር መብታቸው ተጠብቆላቸው የተለያዩ ስራዎች ላይ በመሳተፍ የራሳቸውን ኑሮ አሻሽለዋል፡፡ ለሀገራቸው ኢኮኖሚም እገዛ አድርገዋል፡፡ ወይም አየደገፉ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ፣አንድነቷን ለማላላት ሲሉ ሱዳን፣ ለአሸባሪው የወያኔ ቡድን ወታደራዊ መንቀሳቀሻ ወይም መተላለፊያ የፈቀደች ሲሆን፣ግብጽና ሳኡዲአረቢያ በበኩላቸው የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጋቸው ይሰማል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የታላቁ የአባይ ግድብ በሚገነባበት የኢትዮጵያ ክፍል ( ቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል) የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሀይሎችን ሱዳን በወረትም ሆነ በመሳሪያ ስትረዳ መቆየቷን ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን        ተሰምቷል፡፡ ይህ ታጣቂ ቡድን በርካታ ሹፌሮችን ገድሏል፡፡ መንገዶችን ለብዙ ግዜ ይዘጋ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሱዳን ተንኮል የታላቁን የአባይ ግድብ ስራ ለማስተጓጎል ያለመ ነበር፡፡

ሱዳንና ግብጽ በበኩላቸው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ተጠግተው ለተደጋጋሚ ግዜ ወታደራዊ ልምምድ አድርገዋል፡፡ የዚህ የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት ዋነኛ አላማ የሁለቱን ሀገራት የጦር ሀይል ጡንቻቸውን ለማሳየትና ኢትዮጵያን ለማስፈራራት ወይም ስጋት ላይ ለመጣል ያለመ ነበር፡፡

በነገራችን ላይ ግብጽና ሳኡዲአረቢያ አክራሪና ሽብርተኛ ቡድኖችን የሚረዱት ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ጎዳና እንዳትራመድ ለማደናቀፍ፣ እንዲሁም ከቻሉ የታላቁ የአባይ ግድብ ስራን ለማስተጓጎል፣ከሆነላቸው እስከመጨረሻው ለማሰናከል አስበው፣ተዘጋጅተው ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህችን በአፍሪካ የምትገኝ ትልቅና ታሪካዊት ሀገር የግዛት አንድነት ለማናጋት አቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ፣ሰላሟን ማደፍረስ ዳፋው ብዙ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚቀጣጠለው እሳት ለአፍሪካው ቀንድና ለአካባቢው ሀገራት እንደ ሰደድ እሳት የሚሰራጭ ነው፡፡

የማን ቤት ነዶ፣ለማን ይበጅ፣

……… እንዲሉ ኢትዮጵያን ጎድቶ፣ክፉ አስቦ ሰላሙን ያገኘ የአለም ሀገር አሁን ድረስ አልተገኘም፡፡ የጀብሃንና ሻቢያን ፈዳያን ታሰለጥን የነበረችው፣ሶሪያ፣የገንጣይ ሀይሎችን ትረዳ የነበረው ኢራቅ፣ወዘተ የደረሰባቸውን ስቃይና መከራ ማስታወስ ብልህነት ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ምንግዜም ቢሆን ጥሎ የማይጥል አምላክ አላት፡፡

የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል፡፡ ኢትዮጵያ ከውሰጥም ፣ከውጭም እንዲህ ተቀስፋ ተይዛ፣ የጠበቃት የኢትዮጵያ አምላክ ይመስለኛል፡፡በዚህ የምትከፉ ትኖሩ ይሆን ? ካላችሁም አፍንጫችሁን ላሱ ነው አጭር መልሴ፡፡

ሁለቱም የመካከለኛውና የሰሜን አፍሪካ አረባዊ መንግስታት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲና እድገት ጉዞ ለማጨናገፍ የሚያደርጉትን ጉዞ ቀሪው አለም ዝም ብሎ ማየት የለበትም፡፡ የሰለጠነው አለም በተለይም የምእራቡ አለምና የኢትዮጵያ ወዳጆች እነኚህ አረባዊ አምባነን መንግስታት በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች የሚየደርጉትን መጠነ ሰፊ ድጋፍ እንዲያቆሙ መጠየቅ የተባበሩት መንግስታት የጋራ ጸጥታ መርህ መሆኑን ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስንት ግዜ ነው በአለሙ የጸጥታው ምር ቤት የምትከዳው ?

በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ሳኡዲአረቢያ በምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ ግብጽ ከአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ጋር የመከላከያ ወይም ወታደራዊ ስምምነት ለመፈራረም በቅታለች፡፡ ( ግብጽ ኢትዮጵያን መክበብ በሚያስችል መልኩ ከኬንያ፣ቡሩንዲ፣ኡጋንዳ፣ዲጂቡቲ እና ሩዋንዳ ጋር ወታደራዊ ስምምነት አድርጋለች፡፡) አንዳንዶቹ ሀገራት ኢትዮጵያን ለመቅጣትና ማግለል፣አንድነቷን ለማናጋት፣ በሚል እኩይ እቅድ በብዙ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ አልሰማንም አላየንም ካላልን በቀር በኢትዮጵያ ላይ አፍጦ፣ አግጦ የመጣው አደጋ የሚታይ፣የሚጨበጥ ነው፡፡

ከአንዳንድ የጥናት ወረቀቶች ላይ ለማየት እንደቻልኩት ሳኡዲአረቢያ ፣ በግብጽ ወትዋችነት በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ተዋጊዎች ይውል ዘንድ የመድሃኒት፣ምግብና የጦር መሳሪያ አቅርባለች፡፡ ሳኡዲአረቢያ የህውሃት አሸባሪ ቡድንን ከመርዳት ጎን ለጎን፣ ግብጽ በተባበሩት መንግስታት እና በአረቡ ራቢጣ ማህበር አኳያ ለምታደርገው በማር ለተለወሰ የዲፕሎማቲክ መርዝ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ ይህም ማለት ግብጽ ለምትሸርበው የሀሰት ትርክት እውነት ለማሰመሰል፣ሎቢስቶችን ለመግዛት አትቸገርም ማለት ነው፡፡

እነኚህ በነዳጅ ዘይት ሀብት የሰከሩት የሳኡዲአረቢያ የፖለቲካ ፊትእውራሪዎች እጃቸው እረዥም ነው፡፡ በየመን የርስበርስ ጦርነት ምስቅልቅል ዋነኞቹ ሳኡዲአረቢያና ኢራን መሆናቸው በአለም የመገናኛ ብዙሃን ሰርክ አዲስ የሚነገር አሳዛኝ ዜና ነው፡፡ የሳኡዲ ንጉሶች በየመን የሁቲ አማጺዎችን ከመደገፋቸው ባሻግር፣ በየመን ለሚገኘው የሁቲብርጌድ (allow expelled Ethiopians and others to join the Houthi brigade as volunteers help the region explode ) በአረቡ አለም የሚንከራተቱ ኢትዮጵያውያንን እና ሌሎች የውጭ ሀገር ወደ ገቦችን በመመልመል በሰው አገር እሳት በማንደድ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሳኡዲ እና ግብጽን ታላቅ ሴራ በቸልታ መመልከት የለብንም፡፡ በፍጥነት ወደ አንድነታችን፣ህብረታችን፣ የመከባበር እሴታችንን በፍጥነት ማደስ አለብን፡፡

እሰቲ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በስሜት ሳይሆን በሰከነ መንፈስ፣ በሰለጠነ መንገድ የሚከተለውን መሰረታዊ ጥያቄ ለማንሳት መንፈሳዊ ወኔ እንታጠቅ፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን በ100,000ዎች ለሚቆጠሩት ተዋጊ የጥፋት አባላቱ የምግብ.፣፣መድሃኒት፣ስንቅና ትጥቅ አቅርቦትን ሁሉ የሚያሟለው ከየት ባገኘው የገንዘብ ምንጭ ነው ? ብቻውን ድርጅቱ ይህን ሁሉ አቅርቦት ማዘጋጀት ይቻለዋልን ? እስቲ ሁላችሁም ምክንያታዊ ሃሳቦችን በማንሸራሸር በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል ሳኡዲአረቢያና ግብጽ እጅግ ግዙፍ የሆነ የሎጄስቲክ አቅርቦት እንደሚያሟሉለት ከተለያዩ የጥናት ወረቀቶች ላይ ተረድቻለሁ፡፡ ይህ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ግዛቶች ላይ ወረራ የሚፈጽመው እንደው ዝም ብሎ ብቻውን ሳይሆን ከጀርባው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አሉ፡፡

ይህቺ አአረባዊት ሀገር ለምንድን ነው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ህጋዊ ሰራተኞችን ከሀገሯ ያባረረችው ? ለምንድን  ነው የወያኔ አሸባሪ ቡድንን የምትረዳው ? ለምን ይሆን ከኢትዮጵያ ተጻራሪ አቋም ላላቸው ሀገራት ሁሉ ገንዘቧን የምትረጨው?

ሳኡዲአረቢያ ዛሬም ሆነ ወደፊት የናይል ወንዝን በበለጠ ጥቅም ላይ በማዋል እጅግ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶችን በማስፋፋት የምግብ ፍላጎቷን አሟልታ ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ ችላለች፣ወደፊትም በሰፊው የእርሻ ሰብሎችን ለማምረት ቆርጣ ተነስታለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጻውያን ኤክስፐርቶች ሳኡዲ ዛሬም ሆነ ወደፊት ላቀደችው ታላላቅ የእርሻ ፕሮዤ አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አሳምነዋቸዋል፡፡ አስረድተዋቸዋል፡፡ እንደ አንድ ምክንያታዊ  ሆኖ ለሚያሰብ ሰው በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ያለችው ኢትዮጵያ የተማሩ እና እውቀት ያላቸውን ኢትዮጵያዊ የዲፕሎማሲና የውሃ ሀብት ጥናት ተጠባቢዎችን ወደ ሳኡዲአረቢያ በመላክ በተለይ የታላቁ አባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ በናይል ወንዝ የውሃ ፍሰት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያስከትል ወይም ወደ ግብጽ ምድር የሚፈሰው የናይል ወንዝ የውሃ መጠን ሊቀንስ እንደማይችል በዲፕሎማሲ ቋንቋ ማስረዳት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንደ አንዳንድ የፖለቲካ አዋቂዎች የጥናት ወረቀት ከሆነ ልክ ኢትዮጵያ በአውሮፓና የተባበረችው አሜሪካ አኳያ የዲፕሎማቲክ ክስረት እንደገጠማት ሁሉ ፣ከሳኡዲአረቢያ ጋርም ቢሆን የዲፕሎማሲ ክሽፈት ገጥሟታል፡፡ በአጭሩ የሳኡዲአረቢያ ፈላጭቆራጭ የንጉሳውያን ቤተሰቦችን በዲፕሎማሲ ቋንቋ ማሳመን ተስኖናል፡፡ ወይም ኢትዮጵያ ከሳኡዲአረቢያ ጋር ያላትን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ችላ ያለች ትመስላለች ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ግብጾች የሀሰት መረጃ በመያዝ በዲፕሎማሲ ትግል አኳያ ጥለውን ከነጎዱ አመታት ተቆጠሩ፡፡ ስለሆነም ሳኡዲአረቢያ ለኢትዮጵያ ጀርባዋን መስጠት ጀምራለች፡፡ በነገራችን ላይ ግብጾች በዲፕሎማሲ ትግል አኳያ ጥለውን ከተራመዱ ቢያንስ 30 አመታት አልፈዋል፡፡ እስቲ ሁላችንም ለምን ብለን ለመጠየቅ መንፈሳዊ ወኔ እንታጠቅ፡፡  ይህ በእንዲህ እንዳለ ሳኡዲአረቢያ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ አክራሪዎችና ሽብርተኞችን፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ተጻራሪ አቋም ላላቸውና ወታደራዊ ስምምነት ከግብጽ ጋር ስምምነት ላደረጉ ሀገራት ሳይቀር በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የፔትሮል ዶላር በመመዥረጥ መደገፉን ተያይዘዋለች፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት በተቻለ መጠን ከሳኡዲአረቢያ ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማድረግ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማከናወን የሚጠበቅበት ይመስለኛል፡፡ ይህ አልሆነ ካለ ግን እንደ ኢራንና ቱርክ ከመሰሉ ሀጋራት ጋር፣ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ባስጠበቀ መልኩ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማድረጉ ኢትዮጵያ ላጋጠማት ብሔራዊ አደጋ ግማሽ መፍትሔ ያስገኛል ብዬ አስባለሁ፡፡

Ethiopia should reach out to Saudi Arabia to assuage them of their concern, If that does not succeed, call all the best of, work with the Houthi, Iran, Turkey to unhinge the rotten monarchy from the back of the Saudi people.

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከተደቀነባት አደጋ ለመውጣት፣በተለይም በታሪካዊ ጠላቶቻችን ከተከፈተባት የእጅ አዙር ጦርነት  በአሸናፊነት ለመውጣት ያስችላት ዘንድ በዋነኝነት በዲፕሎማሲ ትግሉ ላይ መበርታት ይገባታል ባይ ነኝ፡፡ በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ክቡር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ክቡር አቶ ሞክንን ሀብተወልድ. ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩን፣ በደርግ ዘመነ መንግስት ደግሞ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ አቶ ብርሃኑ ድንቄ፣ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ፣ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ፣ ዶክተር ቀንጂት ስነጊዮርጊስን፣ በፖለቲካ ሳይንስ ከፍተኛ እውቀት የተካኑ እንደ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፣ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ፣ ወዘተ ወዘተ ያፈራች ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የተማሩ ሰዎች ምድረ በዳ አይደለችም፡፡ ዛሬም ቢሆን ሀገርን የሚያኮሩ ልጆች ሞልተዋታል፡፡ ከእነኚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ፕሬዜዴንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፣አምባሳደር አጽቀስላሴ ወዘተ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ ስለሆነም የግዜው የኢትዮጵያ መንግስት በየሀገራቱ የኢትዮጵያ ልኡክ አድርጎ የሚሾማቸው ዲፕሎማቶችን በችሎታ እና ከራሳቻው ይልቅ ለኢትዮጵያ ታማኝ የሆኑ ዲፕሎማቶችን እንዲሾም በታሪክ ፊት ቆሟል፡፡ የዲፕሎማሲ ትግል በአንድ ሳምንት ዘመቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ ዲፕሎማሲው እውቀት ባላቸው ሰዎች፣ለሀገራቸው፣ለህዝባቸው ታማኝ እና ለእውነት በቆሙ ሰዎች መመራት ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከዲፕሎማሲ አኳያ ከተቀናቃኞቹ ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ወይም ለማሸነፍ ለተማሩ ኢትዮጵያውያን ግልጽ ጥሪ በማድረግ ይደግፉት ዘንድ በታሪክ ፊት ቆሟል፡፡ እውን የኢትዮጵያው መንግስት የጎሳ፣ሃይማኖት፣የፖለቲካ ወገንተኝነት የማይታይባቸው፣በአለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መርህ የሚመሩና የተማሩ ኢትዮጵያውያንን የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ልኡክ አድርጎ ለመመደብ መንፈሳዊ ወኔ ይታጠቅ ይሆን ? ግዜ የሚያሳየን ይሆናል፡፡ እስከዛው ሰላም ለመላው ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ በመመኘት ልሰናበት፡፡

መስከረም 30 ቀን 2014

Filed in: Amharic