>
5:16 pm - Monday May 23, 3808

ቀለብ/አስቴር/ስዩም ማን ናት? (ጌጥዬ ያለው)

ቀለብ/አስቴር/ስዩም ማን ናት?

ጌጥዬ ያለው

‘ቀለብ’ ቤተሰቦቿ ያወጡላት መጠሪያ ሲሆን ከእነ እስክንድር ነጋ ጋር በቀረበባት ሐሰተኛ ክስም የምትጠራበት የመዝገብ ስሟ ነው። ‘አስቴር’ ደግሞ ከአርበኝነት ጊዜዋ ጀምሮ የምትጠራበት የትግል ስሟ ነው።
ቀለብ ስዩም መስከረም 16 ቀን 1979 ዓ.ም. በሰሜን ጎንደር፤ በታች አርማጭሆ ወረዳ፤ ሰፊ ባሕህር ቀበሌ ተወለደች። ለትምህርት ስትደርስ ሰፊ ባሕር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባች። በሳንጃ 1ኛ ደረጃና ጎንደር ፋሲለደስ መሰናዶ ት/ቤቶችም ተማረች። በመቀጠል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ተፈትና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ የካቲት 27 ቀን 1998 ዓ.ም. ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲን ተቀላቀለች።
በኬሚስትሪ የትምህርት ዘርፍ በድግሪ ተመርቃ ሰሜን ጎንደር፤ ደባርቅ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት ተቀጥራ አስተምራለች።
ከልጅነቷ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ፍትህና ነፃነትን የምትመኘዋ አስቴር ስዩም ከ1997 ዓ.ም.  እስከ 2006 ዓ.ም. በአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የሰሜን ጎንደር ዞን የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ በመሆን ታግላለች። በሰኔ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ “በኢንኦርጋኒክ ኬሚስትሪ” በከፍተኛ ማዕረግ በማሰሰትሬት ተመርቃ በማግስቱ ሐምሌ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በወያኔ ደህንነቶይ  ታፈነች። አዲስ አበባ ማዕከላዊም ገባች። ግፉንና ሰቆቃውን  በወንበዴው የህወሓት መንግሥትም ሆነ ዛሬም የለውጥ መንግሥት በተባለው ዘመን እየተጎነጨች ነው። ክሶቿ ፍፁም የቅጥፈት ናቸው። በህወሓት ዘመን በውሸት በተቀነባበረ የሽብር ወንጀል ያለምንም መረጃና ማስረጃ አራት አመት ተፈርዶባት ፍርዷን ጨርሳ ወጣች።  በዚያን ጊዜ ከደረሰባት ዘግናኝ ግፍና በደል መካከል የሚከተሉት ሁሌም ከእዝነ ህሂናዋ እንደማይጠፉ ትናገራለች፦
1. ወላጅ እናቷ ጨቅሊት መንግስቱን በሞት የተነጠቀቺው በወያኔ እስር ቤት ሆና ነበር። በላይ በአካል ተገኝታ እናቷን እንዳትቀብር መደረጓ ከባድ ሀዘን ነበር።
2. “ከእኔ ጋር በተያያዘ የባለቤቴ ወንድም የሆነውን ፋሲል ጌትነትን  ከአካባቢው አፍነው ወስደውታል። የት እንዳደረሱት ሳናውቅ 7   ዓመት ሆኖናል። ይህ የጭካኔ እርምጃ ለቤተሰቦቻችን ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትና ቀውስ ፈጥሮብናል” ትላለች አስቴር።
3. “ልጆቼ ዮሐንስ በለጠና አቅለሲያ በለጠ እኔ በግፈኞች በመታሰሬ  ምክንያት ያለሃጥያቴና ያለሃጥያታቸው ያለ እናት ለማደግ ተገደዋል።
በተለይም የመጀመሪያ ልጄ በዚህ ረገድ ዕድለኛ አልነበረም” ስትል አስቴር እናትነቷን በእስር ቤት እንደተነጠቀች በማስታወስ ነው። አስቴር የታሰረቺው ዮሀንስን በወለደች ገና በስድስት ወሯ ነው። በዚሁ ወቅት አባቱ  መምህር በለጠ ጌትነት ደግሞ ከሚሠራበት ጎንደር  ዩኒቨርሲቲ በወያኔ አድር ባይ አመራሮች አማካኝነት ተባረረ። ከዚያም ባለፈ አካባቢውን ካለቀቀ እንደሚታሰር ተነግሮት ቀየውን ለቆ ተሰደደ።
ልጆቿ ያለ እናትና ያለአባት ማደጋቸው በራሱ ወንጀል ነበር። ችግሩ በዚያ አላቆመም። ህፃኑን የማሳደግ ሓላፊነት የወደቀባቸው ወላጅ እናቷ ወደ ማይቀርበት አሸለቡ። ታናሽ እህቱ አቅለስያ በለጠም በተወለደች በ10 ወሯ  እናቷ  አስቴር ስዩም ለሁለተኛ ጊዜ በተመሰረተባት ሀሰተኛ የሽብር ክስ ምክንያት ወህኒ ወረደች።  እነሆ አቅለሲያ ያለ እናት እያደገች ትገኛለች።
4. “የእኔና የባለቤቴ ቤተሰቦች ‘እናንተ የአሸባሪ ቤተሰብ ስለሆናችሁ ከዚህ መኖር አትችሉም’ በሚል ከሥራቸው ታገዱ፣ ከቀያቸው ተባረሩ፣ ሀብት ንብረቶቻቸውንም ተዘረፉ” ስትልም ታስታውሳለች።
5. “ከምንም በላይ የሚያሳዝነው በዚህ መንግሥትም ተመሳሳይ የሽብር ክስ ተመስርቶብኝ በእስር የምገኝ ይሆናል። የልጆቼ ችግርና መከራ ያልተቋጨበት፣ እናታቸውን አጥተው መዋልና ማደር ከባድ ቀውስ የሚፈጥር መሆኑን ልጅ ያለውና የትክክለኛ ህሊና ባለቤት የሆነ ሁሉ ያውቀዋል” ስትል አስቴር አሁንም በቃሊቲ ወህኒ ቤት ውስጥ ሆና ምሬቷን ትገልፃለች።
6. በማዕከላዊና በቃሊቲ እስር ቤት በደረሰባት ከፍተኛ ድብደባና   የአዕምሮ ግርፋት (mental torch) የአካልም ሆነ የስነልቦና ጫና ደርሶባታል። በዚህም ምክንያት አሁን ድረስ በእስር ቤት በነርብና በእጢ በሽታ እየታመመች ትገኛለች። ለረዥም አመታትም በክኒንና በመርፌ እገዛ እንድትኖር ተፈርዶባታል።
Filed in: Amharic