>

የዛሬው የባልደራስ አመራሮች የፍርድ ቤት ውሎ...!!! (ጌጥዬ ያለው)

የዛሬው የባልደራስ አመራሮች የፍርድ ቤት ውሎ…!!!

ጌጥዬ ያለው

ችሎት፤ ጥቅምት 5 ቀን 2014
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል። ዐቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮችን በግለፅ ችሎት እንዲያሰማም ለዛሬ ከቀትር በኋላ ማለትም ከቀኑ ከ7:30 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። የምስክሮችን ስም ዝርዝር እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ቢያዝዝም ከሳሽ ማቅረብ እንደማይችል ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ምስክሮች በግልፅ ችሎት እንዲሰሙ ማዘዙን አስታውሶ ትዕዛዙን እንዲያከብር አስጠንቅቋል። “የሕግ ልዩ ሁኔታ (exception) አለ። የትዕዛዝ ልዩ ሁኔታ ግን የለም። ይሄ አዲስ እውቀት አይደለም፤ ነባር ነው። በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ  አንቀፅ 136 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ተከሳሾች የሚመሰክሩባቸውን ሰዎች ማንነት የማወቅ መብት አላቸው። ቀድማችሁ ማቅረብ ቢኖርባችሁም የሁለቱን ዝርዝር አሁን አቅርቡ፤ የሌሎችን ደግሞ ከሰዓት በኋላ ይዛችሁ ቅረቡ” በማለት ችሎቱ አዝዟል። ሆኖም ዐቃቤ ሕግ ዛሬ የሚመሰክሩትን ሁለት ሰዎች ስም ዝርዝር በፅሁፍ እንዳልያዘ ገልጿል። ከቀትር በኋላ በሚኖረው ችሎት እማኝነታቸውን ሲሰጡ የሁለቱን ስም እንዲያቀርብ ተስማምተዋል። የሌሎች 19 ምስክሮችን ስም ዝርዝርም በታዘዘው መሰረት እንደማያቀርብ ዐቃቤ ሕግ ተናግሯል። “ገና ከማህበረሰቡ ስላላገለልኳቸው ለደህንነታቸው እሰጋለሁ” ሲልም ገልጿል። ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ዐቃቤ ሕግ የታዘዘውን የማይፈፅም ከሆነ የራሱን አማራጭ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ዛሬ ይመሰክራሉ የተባሉ  እማኞች በነፃነት ታጋዩ አንደኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ ላይ ብቻ የሚመሰክሩ ናቸው። የሚመሰክሩበትን የድርጊት ጭብጥ እንዲገልፅ ቢታዘዝም ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ትዕዛዙን እንደማይፈፅም ደመላሽ ኢጄታ በተባለ ዐቃቤ ሕግ አማካኝነት አሳውቋል። በተለይም ከማክሰኞ ጀምሮ የሚሰሙ ምስክሮችን የምስክርነት ጭብጥ ቢገልፅ ማንነታቸውን ማጋለጥ እንደሚሆንበት ጠቅሷል።
ከፊታችን ማክሰኞ ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ 19ኙ ምስክሮች መሰማታቸውን እንዲቀጥሉ ታዝዟል። በአንድ ችሎት ስንት ምስክሮች መቅረብ እንዳለባቸውም ችሎቱ ዛሬ ከቀትር በኋላ ይወስናል።
ከሰአት የተቀጠረው የነ እስክንድር ቀጠሮ የቀኝ ዳኛው ሰው ታሞበት ሄዶል በሚል ብይን መበየን ሰለማንችል ለሰኞ  ተቀጥሮል !!
እንደዚህ አይነት ስበቦች አብዛኛውን ጊዜ ከላይ ትእዛዝ ለመቀበል ፍርድ ቤቶች የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች እንደሆኑ ግለፅ ነው
Filed in: Amharic