>

አናብስት በኢትዮጵያ፤ ቀበሮዎች በግብጽ...!!! *የአናብስት አገር ኢትዮጵያ የድሏ ምስጢር ኢትዮጵያዊነት ነው...!!! ( ጌታቸው ወልዩ)

አናብስት በኢትዮጵያ፤ ቀበሮዎች በግብጽ…!!!
*የአናብስት አገር ኢትዮጵያ የድሏ ምስጢር ኢትዮጵያዊነት ነው…!!!
 
 ጌታቸው ወልዩ

ውድ ወገኖቼ እንደምን ሰነበታችሁ? ዛሬ ኢትዮጵያዊነትን ከአናብስት ጋር አስተሳስሬ፤ ከፀረ-ኢትዮጵያዊቷ ግብጽ ምሁርና ጀማል አብ ድል ናስር ምልከታ ጋር ቀምሬ የአናብስት አገር ኢትዮጵያን የጀግንነት የግራሞት ታሪክ የተመለከተ
መጣጥፍ አስነብባችኋለሁና አብራችሁኝ ትቆዩ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ጉዳዩ እንዲህ ነው። በአንድ ወቅት አንድ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የበለጸገ “ዩኑስ” የተባለ ግብጻዊ፤ በጨዋታ መኻል “በግብጽ ውስጥ አናብስት (አንበሶች) አሉ ወይ?” ተብሎ ተጠየቀ። እናም!  ግብጻዊው “ዩኑስ” ምን አለ መሰላችሁ?
“በእርግጠኝነት የምናገረው አናብስት (አንበሶች) ያሉት፤ በከፍተኛ ሥፍራ በተከበበችው፤ ለግብጽ ሥጦታ የሆነው ዋናው ጥቁር ዓባይ ከሚመነጭባት ኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ረዣዥም ሣር ወደ በዛባቸው ሞቃታማ/ቆላማ ወይም በረሃማ አካባቢዎች ቢኬድ አናብስትን ማግኘት ይቻላል። ከብዙ ታሪካዊ ሰነዶች እንደተረዳሁት፤ ሌላው ይቅርና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚጠበቁት በአናብስት (አንበሶች) ነው። በአጭሩ በእርግጠኝነት አናብስት (አንበሶች) ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፤ ግብጽ ውስጥ ያሉት ቀበሮዎች ናቸው። ምንም ዓይነት የዱር አናብስት በግብጽ ዐረብ ሪፑብሊክ ውስጥ የሉም!” በማለት አረጋገጠ። (Certainly, there are lions in Ethiopia and foxes in Egypt. It is understood, no wild lions in Egypt Arab Republic.)
ግብጻዊው በዚህ አላበቃም። “አሁንም አስረግጬ የምናገረው በረሃማዋ ግብጽ ውስጥ የሚገኙት፦ ሚዳቆ (ሚዳቋ)፣ የኑቢያ አይቤክስ፣ ‘ጀርባስ’ ማለትም የበረሃ ዱር አይጥ፣ ቀበሮና ቀበሮዎች ብቻ ናቸው። አናብስት የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።“ ሲል በድጋሚ እማኝነቱን ሰጠ።
አዎ! ግብጻዊው ሙያዊ ግዴታው አስገድዶትም፤ እውነትና ንጋት አንገቱን አንቀውትም ሆነ ለህሊናው አድሮ ወይም በሐቅ ገመድ ተጠፍሮ፤ እውነት-እውነቱን መስክሯል። ከነአባባሉም “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል!” ይባላልና  “እውነት በመጨረሻ አሸናፊ (የበላይ) ወይም ድል አድራጊ ነው።“ (Truth is a lion.) እንዲሉ፤ ግብጻዊው እውነቱን በመናገሩ ለህሊናውና ለሙያው ታምኗል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያውያንና ታላቁ የወንዞች አባትና ንጉሥ የሆነው “ዓባይ” በአናብስት ይመሰላሉ፤ ይወከላሉም።  አንበሳነት፦ በራስ የመተማመን (confidence)፣ ጥንካሬ (strength)፣ ፍርሃትን መቀልበስ ወይም የድፍረት /ደፋርነት (fearless)፣ የጀግንነት (courage/heroic)፣ በኀይል የመሞላት (full of energy)፣ የጀብዱና ትልቅ ዋጋነት (velour)፣ ጉብዝና (brave)፣ የስኬት (success)፣ በራስ መተማመንና ኀይልን አጣምሮ የመያዝ (assertiveness) ፤ በክርክር፣ በውይይት፣ በድርድር፣ በጦርነት፣ በሩጫ ውድድር ሁነቶችና በመሳሰሉት አሳማኝነት፣ አስተማማኝነትና ኀያልነት (ferocity) ምልክት ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በጀግንነትና ድል አብሳሪነት ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚጠሩባቸው ታሪካዊው ዕለታት አንዱ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓመተ-ምህረት (በአውሮፓውያኑ ቀመር ማርች 2 ቀን 1896) ነው። ይህ ታሪካዊ ዕለት “በባዶ እግራቸው የሚሄዱና ዘመናዊ ጦር መሣሪያ የማያመርቱ አትዮጵያውያን ጥቁር ሕዝቦች፤ ዘመናዊ ጦር መሣሪያ የሚያመርቱትን፤ በዘመናዊ መንገድ ሠራዊታቸውን ያሰለጠኑትንና ዘመናዊ ጦር መሣሪያዎችን አስታጥቀው ሊያስገብሯቸውና በቅኝ ግዛት መዳፋቸው ውስጥ ሊከቷቸው የመጡትን አውሮፓውያን ጣልያኖችን፤  በሚገርም ሁኔታ በአድዋ ሰንሰለታማ፣ ክብና ጉልላታማ ተራራሮች ላይ በማያዳግም ሁኔታ አሳፍረው አሸንፈው ውርደት አከናነቧቸው።“ ተብሎ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አልበገር ባይነት፣ ጀግንነት፣ ኀያልነት፣ ድል አድራጊነት፣ አሸናፊነትና ፋና ወጊነት በደማቅ ቀለም የተጻፈበት ነው።
በተለይ “ኢትዮጵያውያን በጣልያን ሠራዊት ላይ አኩሪ ድል ተቀዳጁ።” (The Ethiopian gained victory over the Italian army.) የሚለው ትልቅ ዜና፤  ለኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን የአሸናፊነት ድል ጽዋን ሲያስጎነጭ፤ ጣልያናውያንና መላ አውሮፓውያንን የሽንፈት ቡልኮ ማልበሱ ይታወሳል።
እናም! በዚያን ጊዜ አሜሪካንን ጨምሮ እንደ ጎርጎሮሳውያን ቀመር ከኖቬምበር 15 ቀን 1884  እስከ ፌብሩዋሪ 26 ቀን 1885 በጀርመን በተካሄደው “የበርሊን ኮንፈረንስ” የተሳተፉትና ተባባሪዎቻቸው የሆኑ የአውሮፓ አገሮች መንግሥታት ዜጎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ጀግንነትና ድል አድራጊነት አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ ያደፋፈራቸው የካሪቢያን አገሮች ተወላጆች፤ የአናብስት አገር ኢትዮጵያ አሸናፊነት አስደንቋቸው “ኢትዮጵያውያን በራስ የመተማመን ስሜትና ድፍረት፤ ፍርሃት አልባነትና አልበገር ባይነት፤ ድል አድራጊነትና እጅግ ድፍረት የታዩባቸው የጀግንነት ልቦች አሏቸው።“ በማለት እስከ መግለጽ ደርሰዋል። (Ethiopian have the most heroic hearts.)
የሚገርመው እኮ?! በአድዋ በጣልያንና በአውሮፓ ዘመናዊ ሠራዊት ላይ በደረሰው እጅግ አሳፋሪ ሽንፈት፤ የጣልያን ወታደሮች ሚስቶች የባሎቻቸውን የውርደት ጉድ ሲሰሙ “Don’t be spineless” እስከ ማለት ደርሰው ነበር እኮ?! ጎበዝ ከዚህ ዓይነቱ የሽንፈት ሽንፈት መሳለቂያ ይሰውራችሁ! ይኸውም “Don’t be spineless” ማለት በጥሬ ትርጓሜው “አከርካሪህ/ የጀርባ አጥንትህ የተሰበረ አይሁን/አትሁን!” የሚል ፍቺ የያዘ ሊመስላችሁ ይችላል። ነገሩ ወዲህ ነው። ፍቺው፦ የአገራችን ሰው ልፍስፍ/ ደካማ (weakhearted)፣ ፍርሃት ጠፍንጎ የያዘው ቦቅቧቃ (fainthearted)፣ ድፍረትና ወኔ የሌለው ፈሪ (unheroic) ማለት ነው። እናም! የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አንበሳነት እንዲህ አውሮፓን አዋርዷል። ውድ ወገኖቼ፦ ከአድዋ ጦርነት  በኋላም፤ ባለፉት በርካታ ዓመታትና የዛሬው አውሮፓ መንግሥታት ቂም ከምን እንደ መጣ ሳይገባችሁ አይቀርም። አዎ! አንበሳነት ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር እጅጉን የተሳሰረ ነውና።
አንበሳ፦ የአልበገር ባይነት (standoff)፣ ጽኑ የጋለ ስሜት (fervid)፣ ጽኑና የኀይለኝነት ስሜት (ardent) እና ጽኑነት፣ ልበ-ሙሉነት፣ ታላቅነትና ትልቅነት (greathearted) መገለጫ ነው። ለአብነት ያህል፦ ጀግናው የጦር ሰው “አባ ታጠቅ ካሳ-የቋራው አንበሳ” የሚሰኙት፤ በመደበኛ የተፀውዖ ስማቸው ካሳ ኀይሉ ወልደጊዮርጊስ ወይም ካሳ ኀይሉ፤ በስመ-መንግሥታቸው ዐፄ ቴዎድሮስ ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያዊነት ጽኑ ተከታይ ወይም አራማጅና አቀንቃኛ (በዘመነ- መሳፍንት ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ የደከሙ) ነበሩ።“ ብለው  እንኳን አገሬው ጠላቶቻቸው እንግሊዞች ሳይቀር የመሰከሩላቸው ጀግና ናቸው።
(Tewodros II, English Theodore II, original name Kassa Hailegiorgis Woldegiorgis or Kassa Hailu, (born c. 1818—died April 13, 1868, Maqdela, Ethiopia), emperor of Ethiopia (1855–68) was the ardent follower of Ethiopianism.)
አዎ! ኢትዮጵያዊያን እንኳን የጀግንነት ግብራቸው ተገልጾ፣ ተወስቶና ተዘርዝሮ ቀርቶ፤ ስማቸው ሲጠራና ሲነሳ እንደ ዱር አንበሳ ያስፈራሉ። ለዚህም ነው ድምጻዊው:-
 “የኢትዮጵያ ጀግኖች—ስማቸው ሲነሳ
ከሩቅ ያስፈራሉ— እንደ ዱር አንበሳ።” ብሎ ያቀነቀነው።
እንዲሁም አንበሳነት፦ የሥልጣንና ኀይል (power)፣ የግርም ሞገስና የዜግነት ክብር (stateliness)፣ የታላቅ ጥበበኝነት፣ የበላይነት፣ የባላባትነትና የመሳፍንትነት nobility)፣ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የመሆን (royalty)ና የግርማዊነት /ግርማ ሞገስነት (majesty) ማሳያም ነው።
ለምሳሌ:- አንበሳን በሰሎሞናዊው ሥርወ-መንግሥት ያለውን ክብርና ቦታ ካየን፤ የነገሥታት ተምሳሌትና ነገሥታቱን የሚወክል የንግሥና መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።
ለዚህም:- “ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ሥዩመ- እግዚአብሔር ንጉሠ- ነገሥት ዘኢትዮጵያ” የሚለውን የሰሎሞናዊውን ሥርወ-መንግሥት የነገሥታት መጠሪያ መጥቀስ እንችላለን።
በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 49 ቁጥር 8 እና 9 ላይም “ይሁዳ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑኻል። እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው። የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ። ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ወይም የአንበሳ ልጅ ነው። ልጄ ሆይ:-ከአደንህ ወጣህ። እንደ አንበሳ አሸመቀ። እንደ ሴት አንበሳም አደባ። ያስነሳውስ ዘንድ ማን ይችላል?” የሚሉ ኀይለ-ቃላት ሰፍረዋል።
አንበሳ የንግሥናና የሥልጣን መገለጫ በመሆኑም በመጠሪያ ስማቸው ተፈሪ መኮንን፤ በስመ-መንግሥታቸው ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ-ሥላሴ ንጉሠ- ነገሥት ዘ-ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች (አካባቢዎች) አናብስትን እያስመጡ በታላቁ ኢዩቤልዩ ቤተ-መንግሥት ያስቀምጡ ነበር።
እናም! በአንድ ወቅት መዋቲው የግብጽ ፕሬዚዳንት ገማል አብድል ናስር፤ በአንድ የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ መጥተው ነበር። በወቅቱም ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ-ሥላሴ አናብስትን አሰባስበው ወደ ቤተ-መንግሥት ማምጣታቸውን ናስር ሰምተው ኖሮ “እኛ ግብጻውያን የዱር  አንበሳ የለንም። ኢትዮጵያ እንኳን በዱርና በየገደሉ፤ በቤተ-መንግሥቷ  ጭምር አናብስት አሏት።” (ኢትዮጵያ አንበሶች (ደፋሮች) ልጆች አሏት።)ሲሉ በአግራሞት መናገራቸው ይጠቀስላቸዋል።
ለመጥቀስ ያህል በቀዳማዊ  ኀይለ-ሥላሴ የአገዛዝ ዘመን በግል ጠባቂ ውሻቸው “ሉሉ” ስም የሚጠራው “ሉሉ” እና “ሞላ” የተባሉ አናብስት በአደባባይ ወጥተው ለሕዝብ ይጎበኙና አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ ክብረ-በዓላት ላይ በመገኘት ታቦት ያጅቡ እንደ ነበር ይታወቃል።
ከዚህ በተጓዳኝ በኢትዮጵያ አንበሳ ለጦር ክፍሎችና ለስፖርት ቡድኖች መጠሪያነትም  አገልግሏል። ለአብነት ያህል የሶማሌያ ሪፑብሊክ፤ በ1969 ዓመተ-ምህረት በአምባገነኑ ዚያድ ባሬ እየተመራች፤ በምሥራቅና ደቡብ ኢትዮጵያ ወረራ ከመፈጸሟ በፊት፤ በግብጽ እየተደገፈችና እየተመራች በዳኖትና ቶጎ ጫሌ የከፈተቻቸውን የማጥቃት ጦርነቶች በመከላከል፤ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት  ክብር አኩሪ ተጋድሎ የፈጸመው ጀግናው ሦስተኛው አንበሳው ክፍለ-ጦር፤ በአንበሳ ስም ተጠርቶበታል። ይህ ክፍለ-ጦር ከዚያም በኋላ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች፤ ለረዥም ዓመታት አስገራሚ ጀግንነትና ገድል ፈጽሟል።
በእነፊልድ ማርሻል ታንታዊ የጦር አዛዥነት ዘመን፤ ግብጽ የጎረቤት አገሮች ወታደራዊ ሁኔታ ስትፈትሽና ስትመዝን ዘወትር ከምትፈራቸውና እንቅስቃሴያቸውን እግር በእግር ትከታተላቸው ከነበሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት እግረኛ ክፍለ-ጦሮች መካከል ሦስተኛው አንበሳው ክፍለ-ጦር በዋናነት ይጠቀሳል።
በሌላ በኩል ከጦር ክፍሎችና ኀያልነት ጋር በተያያዘ የአንበሳ ታሪክ ሲወሳ በጭራሽ ሳይጠቀስ የማይታለፈው፤ በኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት የክብር ዘበኛ ጦር የመጀመሪያው አዛዥ በነበሩት ቅድሚያ ቀኝ አዝማች ኋላ ደጃዝማች በነበሩት፤ መኩሪያ ባንተይርጉ ስም ይጠራ የነበረው “መኩሪያ” የተሰኘው እጅግ ለማዳ አንበሳ ነው።
በሀምሳ አለቃ ገብሬ አበበ የቅርብ ክትትል ይደረግለትና እንደ አንድ ቤተሰብ አባል ይቆጠር የነበረው የክብር ዘበኛው አንበሳ “መኩሪያ” የክብር ዘበኛ ስፖርት ክለብ ሁሉ መጠሪያ ነበር።
በአንድ በኩል ዝርያው በየትኛውም የዓለማችን ክፍል  እንደማይገኝ በዘርፉ ባለሙያዎች የተነገረለትና በኢዩቤልዩ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት እንደ አገር መሪ በክብር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ የተፈጠረለት ባለ ጥቁር ጋማ አንበሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው።በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙት ባለ ጥቁር ጋማ አናብስትን ሳንዘነጋ ማለት ነው።
ሌላው ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ወራሪ ጠላት ሲመጣባቸውና የአገር ሉዓላዊነት የሚፈታተን ክፉ ጠላት ሲገጥማቸው “አንበሳው ልጅሽ ይኸው መጣልሽ! አንበሳው ልጅሽ ፈጥኖ ደረሰልሽ!” እያሉ ጠላቶቻቸውን እያደባዩና የእፍረት ማቅ እያለበሱ፤ የአገርን ክብር ለዘመናት ሲጠብቁና ሲያስጠብቁ ኖረዋል።
ለዚህ ደግሞ “የጥቁር አንበሳ” ጀግኖች ተጋድሎን መጥቀስ ይቻላል። የፋሺስት ጣልያን ሠራዊት በ1928 ዓመተ-ምህረት ኢትዮጵያን ሲወር፤ በቀድሞው አጠራር የሆለታ ገነት ጦር እጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኝ ወጣት መኮንኖች፤ጥቁር አንበሳ ማኅበር መሥርተው:-
አትለውም ወይ—አትለውም ወይ፣
ጥቁር አንበሳ— አይደለህም ወይ?!
በማለት ከፋሺስት ጣልያን ወራሪ ጦር ጋር የተፋለሙትና በዱር በገደሉ ለኢትዮጵያ ክብር የተዋደቁትና መስዋዕትነት የከፈሉት፤ የጥቁር አንበሳን አርማ ይዘው ነው።
ለማጠቃለል ያህል በኢትዮጵያ የአንበሳ ስም:- አንበሳ አውቶቡስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ፣ አንበሳ መድኃኒት ቤት፣ አንበሳ ጫማ ፋብሪካ (አክሲዮን ማኅበር)፣ አንበሳ ማስታወቂያ ድርጅት፣ አንበሳ ሆቴል፣ አንበሳ ባንክ፣ አንበሳ ቆርቆሮ ፋብሪካ፣ አንበሳው ክፍለ-ጦር፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ የይሁዳ አንበሳ ሐውልትና ጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ አንበሳቸው፣ አንበሳው፣ አንበሴ፣  አንበስዬና  አንበሶ የተባሉ የአገር ልጆች ተጠርተውበታል።
ከዐፄ ኀይለ -ሥላሴ ጊዜ ብንጀምር:- በበርካታ የኢትዮጵያ ሳንቲም ገንዘቦች፣ ደብተሮች፣ ትሪዎች፣ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ ብርጭቆዎችና ብርሌዎች ላይ የአንበሳ ምልክት እናገኛለን። በአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ በሮች ላይ፣ በኢዮቤልዩና ምኒልክ  ቤተ መንግሥቶች፣  በአንዳንድ አብያተ-ክርስቲያናት፣ ቴአትር ቤቶች፣ አደባባዮችና ሆቴሎች ደጃፍ፣ ግንብ አጥርና በውስጥ ግርግዳና ኮርኒስ በኩልም የአንበሳ ምስል ይስተዋላል።
 በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣ አልባሳት፣ አልጋ ልብስ፣ በገጠር አካባቢ ባሉ የመቃብር ሥፍራዎች፣ ለአዲስ አመት ዘመን መለወጫ ለዕንቁጣጣሽ በሚዘጋጁ  የስጦታ ወረቀቶች፣ የትራስና ሶፋ ጨርቆች፣ የሬድዮና ቴሌቪዥን መሸፈኛዎች ላይም የአንበሳ ምስል ልናገኝ እንችላለን። ከአገር ውጭ ካየን ደግም የፈረንሳይ ስሪት የሆነው ፔዦት መኪና አርማ አንበሳ  ነው።
*በመጨረሻም የከናብስት አገር ኢትዮጵያ:- በሚወዷት ልጆቿ አንገት ላይ እንደ ሀብልና ማተብ በክብር የተነጠለጠለች፤ እንደ ውድ አልማዝና ዕንቁ በጣት ላይ የተጠለቀች፤ እንደ እውነተኛ ውል ማሰሪያ በልብ ሰሌዳ ላይ የታተመች፤ የአናብስት ኢትዮጵያውያን የፍቅር ገነት ነች።
*የአናብስት አገር ኢትዮጵያ:- ጀግኖች ልጆቿ ደማቸውን ያፈሰሱላት፣ አጥንታቸውን የከሰከሱላት፣ ሕይወታቸውን የሰዉላት ጀግንነትን በአደራ የተቀበለች የቃል ኪዳን ምድር ነች።
*የአናብስት አገር ኢትዮጵያ:- በእውነተኛ ኢትዮጵያውያን የልብ ሰሌዳ ላይ በክብር የታተመች አገር ነች።
*የአናብስት አገር ኢትዮጵያ:- የድሏ ምስጢር ኢትዮጵያዊነት የሆነ የዘረ-ብዙ ጀግኖች ምድር ነች።
ለዛሬ እዚህ ላይ አበቃሁ። የኢትዮጵያ አምላክ የነገ ሰው ይበለን።
ኢትዮጵያ አገራችን ለዘላለም ትኑር!
ቸሩ እግዚአብሔር  አገረ-ኢትዮጵያንና ሕዝቧን  ይባርክ!
አሜን!
Filed in: Amharic