>

«ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተሻግራ አጓጊ ዕቅዶቿን ታሳካለች»-  አቶ ሙስጠፌ መሀመድ

«ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተሻግራ አጓጊ ዕቅዶቿን ታሳካለች»
አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር
(ኢ ፕ ድ) 

ጅግጅጋ፡- ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተሻግራ አጓጊ ዕቅዶቿን እንደምታሳካና በሶማሌ ክልል በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ትኩረት አግኝተው ከሚተገበሩ ዋና ዋና የልማት ዕቅዶች መካከል አንዱ መንደር ማሰባሰብ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችና የውጭ ጫናዎች እያጋጠሟት ቢሆንም፤ ዛሬም ሆነ ወደፊት ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአጋጠሟት ፈተናዎች የበለጡ አይሆኑም፤ ካለፉት ሦስት ዓመታት ልምድ በመውሰድም ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ፈተናዎችንና ጫናዎችም ተሻግራ ብልጽግናን ታረጋግጣለች።

አቶ ሙስጠፌ አክለውም በሕዝብ የተመረጠው አዲሱ የሶማሌ ክልል መንግሥት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በትኩረት የሚሰራቸውን ተግባራት ለይቷል። የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ሰላምና ጸጥታን በአስተማማኝና ቀጣይነት ባለው መልኩ ማረጋገጥና መንደር ማሰባሰብ ናቸው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ሰፊ የቆዳ ስፋት እንዳለው አመልክተው፤ በአሁኑ ጊዜ በሁሉም አካባቢዎች ተበታትነው የሚታዩ በርካታ መንደሮች ያሉ ነዋሪዎችን የሚያስፈልጋቸውን የመንገድ፣ የውሃና የመብራት አገልግሎቶች ማዳረስ አስቸጋሪና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል። በመጪዎቹ አምስት ዓመታትም ሕዝቡን ሁለተናዊ ተጠቃሚ ለማድረግ እነዚህ መንደሮችን ሰብሰብ አድርጎ የልማት ማዕከሎችና መለስተኛ ከተማዎች ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል ሕዝብ ከዚህ ቀደም ተበታትኖና አርብቶ አደር ሆኖ ይኖር እንደነበር አውስተው፤ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ሕዝቡ በትንንሽ መንደሮች እየተሰባሰበ አገልግሎት የመጠየቅ አዝማሚያ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ አኳያም በፈቃደኝነት የተመሰረተ መንደር ማሰባሰብና አስፈላጊ አገልግሎቶችን የማሟላት ሥራም በቀጣይ አምስት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ መንደር ማሰባሰቡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው የተገነቡ መንገዶች፣ የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮችና የተሰሩ ትምህርት ቤቶች በሙሉ አቅማቸው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረጋል። ሕዝቡም በቀላሉና በአጭር ጊዜ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል።

በክልሉ ከለውጡ በፊት መንደሮች የሚሰባሰቡት ኦብነግ የሚገባባቸው ቦታዎች እየተባለ የጸጥታንና የጸረ ሽምቅ ውጊያን እሳቤ በማድረግ መሆኑን አውስተው፤ ክልሉ ይከተለው ከነበረው የተሳሳተ የመንደር ማሰባሰብ ፍልስፍናን በመቀየር በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሕዝቡን የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ የመንደር ማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ከተሞች እየሰፉ በሄዱ ቁጥር ከመሬት ጋር የተያያዙ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ ችግሩን ከወዲሁ ለመቅረፍ የክልሉን የጎሳ አሰፋፈሮችንና ባህላዊ አኗኗሮችን መሰረት አድርጎ ትክክለኛ የመሬት ፖሊሲና አጠቃቀም ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል።

ለክልሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ግብርናና እንስሳት ልማት ላይ ያተኮሩ በርካታ የግብርና ልማት ሥራዎች እንደሚሰሩም አመልክተው፤ እነዚህ ሥራዎችም የሚከናወኑት በመንግሥት በጀትና ድጎማ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ተሳትፎና በብድር ጭምር እንደሚሆንም ጠቁመዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ የተሰሩት ሥራዎችም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በጥቅሉ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ የተሰሩ አመርቂ የሰላም፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል እንደሚሰራ ገልጸው፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ቀጣይነት ከማረጋገጥ አኳያም የጸጥታ ተቋማትን የማድረግ ብቃት በማጠናከር በኬንያና በሶማሊያ ደንበሮች አካባቢ አልፎ አልፎ እየገባ ጥቃት ለማድረስ የሚሞክረውን አልሸባብ ከሕዝባችን ጋር በመሆን ሦስት ዓመት እንደተሰራው አመርቂ ሥራ በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ነው ያሉት አቶ ሙስጠፌ።

በትልልቅ ከተሞችም ሕገ ወጥ የሰዎችና አደንዛዥ እጽ ዝውውር ወንጀሎችና የጸጥታ ስጋቶችን የመከላከል ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቶቸው የሚሰሩ ተግባራት መሆናውን አመልክተው፤ በሶማሌ ክልል በኢኮኖሚው ረገድ የሴቶች ተሳትፎ ጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆንም በፖለቲካም ረገድ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በተያያዘ አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ የሶማሊ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ!

አዲሱ የሶማሊ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው የመጀመሪያ አመት ጉባኤው ላይ አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ ኡመርን የሶማሊ ክልል ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾሟል።

አቶ ሙስጠፋ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አማካኝነት ቃለመሃላ ፈፅመዋል። አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ ባለፉት 3 አመታት የሶማሊ ክልልን መምራታቸው ይታወሳል።

Filed in: Amharic