>

በጡት አባቶቻችሁ መጨከን አቅቷችሁ ጡቷን አጥብታ ያሳደገቻችሁን አገር የምታስነክሷት እስከ መቼ ነው....??? አሳዬ ደርቤ

በጡት አባቶቻችሁ መጨከን አቅቷችሁ ጡቷን አጥብታ ያሳደገቻችሁን አገር የምታስነክሷት እስከ መቼ ነው….???
አሳዬ ደርቤ

*..   እኔ እምለው ግን… 
➙ ድምጹን የሠጣችሁን ሕዝብ ከጠላት እቅፍ እየጣላችሁ ሕይወቱን የምታስገብሩት እስከ መቼ ድረስ ነው? 
➔ለመሆኑ ጁንታውን በመርዳት በኩል ግብጽና ሱዳን የመንግሥታችሁን ያህል ሚና ነበራቸው? 
➔አሸባሪው ሃይል ሦስት ጊዜ ሙሉ አፈር ልሶ የተነሳውና ምድሩን በደም እየበከለ አገር ማመስ የቻለው በብልጽግናውያን ወይስ በግብጻውያንና በምዕራባውያን ድጋፍ?
ወልዶ ያሳደጋችሁን ቡድን ስንት ጊዜ ምሕረት አደረጋችሁለት? ከአፋርና አማራ በተጨማሪ ወልዳ ያሳደገቻችሁን አገር’ስ ስንት ጊዜ አስጠቃችኋት?
እሱም ይቅር…
አሸባሪው ሲዳከም ‹‹ጨርስ›› በማለት ፈንታ ‹‹ተመለስ›› እያላችሁ፣ ጁንታው ተጠናክሮ ሲመለስ ደግሞ ከረፈደ በኋላ ‹‹ተኩስ›› እያላችሁ ግራ የምታጋቡትና የምታስበሉት ሠራዊት አያሳዝናችሁም?
እስቲ እስካሁን ከተካሄዱት ዘመቻዎች መሃከል በእራሳችሁ የጊዜ ሰሌዳ የተመራውን ለማሰብ ሞክሩ?
የመጀመሪያውን ዘመቻ ሰሜን እዝ ከተበላ በኋላ ተካሄደ፡፡ ጁንታው ለአራት ኪሎ ሥጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱን ስታውቁም ቆላ ተንቤን ላይ ተቀምጦ ያንሰራራ ዘንድ ፈቀዳችሁለት፡፡ በእራስ አሉላ ሥም የሰየመውን የክህደት ኦፕሬሽን አንጠልጥሎ ወደ መቀሌ በመምጣት ሠራዊታችን ላይ ክህደት እስኪፈጽም ድረስም እራሳችሁን በተራ ተግባራት ስትጠምዱ ከረማችሁ፡፡
ከጥቃቱ በኋላም ‹‹የተናጠል ተኩስ አቁም አድርገናል›› በሚል ምክንያት የተረፈውን ሠራዊት ደጀን ወዳለበት ስፍራ ከሳባችሁ በኋላ ‹‹ስልታዊ ማፈግፈግ›› በሚል ሥም ጦሩን እየሳባችሁ ደጀኑን አስወረራችሁት፡፡ አሸባሪው ሃይል ግን ምሕረት ባገኘ ቁጥር ጥፋት ደግሶ የሚመጣ በመሆኑ በእራሱ የትግል ሰሌዳ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት ከመፈጸም ወደኋላ አላለም፡፡
እናም ‹‹ሕዝባዊ›› የሚለውን ሠራዊት እያንጋጋ ሁለተኛ ዙር ወረራውን እስኪፈጽም ድረስ እራሳችሁን በድግስ ጠምዳችሁና ሕዝቡን አስተኝታችሁ መጠበቅ መረጣችሁ።
እንዲያ ሆኖ ግን በመንግሥት ተስፋ የማይቆርጠው የአማራ ሕዝብ ወጣት ልጆቹን በመከላከያ ሠራዊትነት ከማስመዝገቡም በላይ ልክ እንደ አፋር ሕዝብ የክተት ጥሪውን ተቀብሎ በሰሜን እና በደቡብ ጎንደር የመጣውን ወራሪ በባዶ እጁ ከመታገል ወደኋላ አላለም፡፡
ከተወሰነ ትግል በኋላም በሱዳን ኮሪደርና በአፋር መስመር የዘመተው አሸባሪ መመታቱን ስታረጋግጡ ‹‹እኛ ላይ ከባድ ችግር ካላስከተለ ሕዝቡን እንዳሻው ያድርገው›› ብላችሁ ሙሉ በሙሉ ከመደምሰስ ይልቅ ለሦስተኛ ጊዜ አፈር እንዲልስ ፈቀዳችሁለት፡፡ እናም ለትግል የተነሳሳውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተፈናቀለውንም ጭምር እርግፍ አድርጋችሁ በመርሳት በዓለ ሲመቱንና የማሣ ጉብኝቱን አጧጧፋችሁት፡፡
የተዳከመው አሸባሪ እስኪያገግም ብቻ ሳይሆን በዜጎች ሞት የተገኘው ድል ወደ ትግል ተለውጦ የበለጠ ዋጋ እስኪያስከፍል ድረስ ሕዝቡን አስተኝታችሁ የክልሉን ወጣት አፍሶና የተሻለ የትግል ስልት ቀይሶ እስኪመጣ ድረስ የግብርና ሚኒስትር ሆናችሁ ጠበቃችሁት፡፡ እና ደግሞ ሶሻል ሚዲያው ለተፈናቀሉ ዜጎች ገንዘብ ሲያሰባስብና አክቲቪስቱ መንግሥትን ወክሎ የአሸባሪውን ፕሮፖጋንዳ በትዊተርና በፌስቡክ ሲመክት የእናንተ ሚዲያዎች ግን ጭቃ ስለማቡካትና ስለ ቦሎቄ ጉብኝት ሲያትቱ ሰነበቱ፡፡
በእነዚህ ጊዜያት ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ የከረመው አሸባሪም ለዳግም ወረራ ሲንደረደር አገሩንና ሕዝቡን መጠበቅ የሚገባው መንግሥት ጤነኝነቱ እስኪያጠራጥረን ድረስ ‹‹ዝመት ክተት ማለት አያስፈልግም›› እያለ እራሱን የመጠበቅ ግዴታ የተጫነበትን ሕዝብ ያናንቅ ያዘ፡፡
ታደሰ ወረደም ጭፍራ ላይ ግዳዩን ጥሎ ‹‹ጠላቶቼን አስገብሬ ወደ አዲስ አበባ መሻገሬ ነው›› እያለ ሲፎክር ‹‹ልጆቼን አሰልጥነህ ተዋጋልኝ›› ብሎ ለመንግሥት ካሰረከበ በኋላ መንግሥት አለመኖሩን የተረዳው የዋሁ ሕዝብ ግን ‹‹በባዶ እጄ ልዝመት ወይስ ልሰደት›› እያለ ይጨነቅ ጀመር፡፡
እኔ እምለው ግን…
➙በጡት አባቶቻችሁ ላይ መጨከን አቅቷችሁ ጡቷን አጥብታ ያሳደገቻችሁን አገር የምታስነክሷትና ድምጹን የሠጣችሁን ሕዝብ ከጠላት እቅፍ እየጣላችሁ ሕይወቱን የምታስገብሩት እስከ መቼ ድረስ ነው?
➔ለመሆኑ ጁንታውን በመርዳት በኩል ግብጽና ሱዳን የመንግሥታችሁን ያህል ሚና ነበራቸው?
➔አሸባሪው ሃይል ሦስት ጊዜ ሙሉ አፈር ልሶ የተነሳውና ምድሩን በደም እየበከለ አገር ማመስ የቻለው በብልጽግናውያን ወይስ በግብጻውያንና በምዕራባውያን ድጋፍ?
አሁንም ቢሆን  ከዚህ ትግል ድል ትሰጡናላችሁ ብሎ ከማሰብ ይልቅ ‹‹ለሌላ ትግል ሌላ ታጋይ አምጡ ትሉናላችሁ›› ብሎ መገመት ይቀላል፡፡ ስለሆነም ከአገሩ ባለፈ የወገኑ ሕልውና እንደሚያሳስበው እንደ አንድ እረፍት አልባ አማራ ይሄን ጦማር ስጽፍላችሁ ወገኔን ትታደጉት ዘንድ ለመማጸን ሳይሆን እራሱን የሚስከብርበት ነጻነት ሰጥታችሁ ትተውት ዘንድ ለመለመን ነው፡፡
‹‹መንግስት መሆናችንን አውቀህ ግብር መክፈል እስከቻልክ ድረስ ከእኛ እጅ ቀጣይነት ያለው ትግል እንጂ ዘላቂ ድል ስለማይገኝ የሮዋንዳ ታሪክ ተደግሞብህ ጣጣ ከምታመጣብን፤ ሕልውናህን አስከብር›› ብላችሁ ቁርጡን ትነግሩት ዘንድ ለመጠየቅ ነው፡፡ በመንግሥታዊ እሳቤ ውስጥ ተቀፍድዶ በሕግ አልባ አገር ውስጥ ‹‹በሕግ አምላክ›› እያለ ወደ መቃብር የሚወርደው ታላቅ ሕዝብ እንደ ጠላቶቹ ወራሪና አሸባሪ መሆን ባይቻለው እንኳን ሕልውናውን አስከባሪ ይሆን ዘንድ ‹‹መዋቅራዊ አፈናችሁን አንሱለት›› ለማለት ነው፡፡
በመጨረሻም ከምትራሩለት አሸባሪ እጅ የጣላችሁት ሕዝብ ከቤቱ በተፈናቀለና በራቀ ቁጥር ወደ ቤተ-መንግሥቱ እየተጠጋ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡
Filed in: Amharic