>

ብልጽግና የሚወለደው ከፍትሕ ማህፀን ነው!!! ዳንኤል ሽበሽ

ብልጽግና የሚወለደው ከፍትሕ ማህፀን ነው!!!

ዳንኤል ሽበሽ
… አጠቃላይ የሀገራችን ችግር ሊፈታ የሚችለው፦
1. በፍትሕ (በንጹሕ ፍርድ)፣
2. በውይይት፣ በንግግር …፣
3. በፍትሐዊ-ሕግ አግባብ፣
4. ከፍ ሲል በፈጣሪ ጣልቃ ገብነት (እንደ ነጮቹ በ Divine intervention)፣ ይመስለኛል ።
ከትላንት ጥቅምት 9ቀን: 2014 ዓም ጀምሮ የእነ #እስክንድር_ነጋ የፍርድ ቤት ውሎን እየተከታተልኩ ነበር ። የበፊቱንም እንዲሁ ። በአስቸጋሪ #ፍትህ_ሥርዓት ውስጥ እንዳለፈ ሰው በርከት ያሉ ነገሮችን የታዘብኩ ሲሆን አንዳንድ መሻሻሎችንም ተመልክችያለሁ ። ለምሳሌ የችሎት ታዳሚዎች፣ ጋዜጠኞች እና ሰብዓዊ መብት ወኪሎች የሚስተናገዱበትን አግባብ፣ ተከሳሾች በነጻነት እንዲናገሩ መፍቀድንና ዳኞች በርጋታ #ቢሶታቸውን የሚያዳምጡበትን ሁኔታ ተመልክችያለሁ ። በርግጥ ፍትህ በራሷ በህላዊነታዊ (Existence) ማንነቷ እንጂ ካለፈው ወይም ከዛኛውና ከዚህኛው አንጻር ማነጻጸር ተገቢ ነው ብዬ ባላምንም ካለፈው አንፃር ደህና ነው፤ አይከፋም ። ስለ ፍርዱ ወደ ፊት መመለሴ አይቀርም ።
በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ ግን ዐቃቤነቱ ለህግ ሳይሆን ለካድሬ መሆኑን ታዝብያለሁ ። ወገኖቻችን የተፋጠነ ፍትህ እንዳያገኙ ሆን ብሎ ሲያዘገይና የተለመደውን መንገድ ለማስቀጠል እየጣረ መሆኑን ዳኞች እስኪስቁ፣ ታዳሚዎች እስኪሳልቁበት ድረስ ራሱንና ተቋሙን አዋርዷል ። ባጠቃላይ በዐ/ህጉ እጅግ አዝኛለሁ ። ይህ አስተሳሰብ ለሀገርም፣ ለመንግሥትም ሆነ ለራሱ ለብልጽግናም አይጠቀምም ። እጅግ እጅግ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው ። ለሰው ልጅ በሙሉ በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን #የነጻነት #የፍትህ ነገር የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ መሆኑን በጥልቀት መረዳቱ አይከፋም ። ሕግን ተፈትነው ወደ ወደቀ ፖለቲካ ደረጃ ለማውረድ እና ፖለቲከኞችን #በአሸናፍዎች ፍትህ ለማጥገብ መሞከር መዘዙ ብዙ ነው ።
#ሌላው በአጽንኦት ማሰብ ያለብን የምር ለፍትህ ከቆምን መጨነቅ፣ ማንባት ያለብን ስለ ፓርቲ ሳይሆን ስለ ሰው፣ ስለ ሀሳብና ስለ ፍትህ መሆን አለብን ብዬ አስባለሁ ። በአሁኑ ወቀት ለእነ #እስክንድርም ሆነ ሌሎችም በተዛባ ፍትህ ውስጥ እንዲሻገሩ ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም ። ለብቻቸው እንዲወጡት ለእነርሱ ብቻ የምንተወውና ብቻቸው እንዲጋፈጡ የምናጋፍጣቸው አይደለም ። ለእነ እስክንድር ያልሆነች ፍትህ፣ ለእሱ ያልሆነች ሀገር ለእኔ ትሆናለች ብዬ ስለማላስብ ።
ባጠቃላይ ዓሳ ከውሃ ጋር ያለው ቁርኝት ያህል የሰው ልጅም ከፍትህ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ለአፍታ እንኳን መዘንጋት የለብንም ። እንደ ራሳቸው የሕግ ባለሙያዎች አባባል ❝የዘገየች ፍትህ ደግሞ ፍትህን እንደመንፈግ❞ ትቆጠራለችና (Justice delayed is Justice denied !!!)… ።
ሀሳቤን ሳጠቃልል አሁን ሀገራችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ሁሉን ማውራት ጊዜው ባይሆንም #የተፋጠነ_ፍትህ ለእነ እስክንድር ነጋ እና ለጓዶቹ እንዲሆን እጠይቃለሁ !!!
የፍትህ እጦት ያፈረሳትን ሀገር ማንም አይገነባትም !
Filed in: Amharic