>

በየቀኑ አንድ አንድ ዞን እየተወረረ “ጦርነቱን ለወታደራዊ ባለሙያዎች ተውላቸው” የሚባለው እስከ መቼ ነው?  (አቻምየለህ ታምሩ)

በየቀኑ አንድ አንድ ዞን እየተወረረ “ጦርነቱን ለወታደራዊ ባለሙያዎች ተውላቸው” የሚባለው እስከ መቼ ነው? 
አቻምየለህ ታምሩ

ጎበዜ ሲሳይ ያነሳቸውን ጥያቄዎች የሚያነሳ ነፍስ ያለው ሰው ብቅ ባለ ቁጥር የዐቢይ አሕመድ ተላላኪዎች “ጦርነቱን ለወታደራዊ ባለሙያዎች ተውላቸው” የሚል ማዘናጊያ ይሰጣሉ። እነዚህ ሕዝብን ለማደንዘዝ የተሰማሩ ቦዘኔዎች ሙያ የሚጠይቅ ነገር በባለሙያ መሰራት ቢኖርበትም ባለ ሞያው ግን  ባመጣው ውጤት የሚመዘን መሆኑን አያውቁም። ሕክምና የሚሰጠው የሕክምና እውቀት ባለው የጤና መኮንን መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም። ሆኖም የጤና መኮንኑ ለታማሚው ባመጣው ፈውስ ይመዘናል። የኢትዮጵያ የጦር መሪዎችም የሚመዘኑት ከዚህ አንጻር ነው።
የአንድን አገር አየር ኃይል፣ ተዋጊ ድሮን፣ ምድር ጦር፣ ፈጥኖ ደራሽ የፖሊስ ሠራዊት፣ የየአካባቢው ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ሙሉ በሙሉ ያሰለፈ፣ አለም ያመረተውን ደፍጥጦ የሚያነድ የጦር መሳሪያ መታጠቅ የሚችልና ደጀን በሆነ ሕዝብ መካከል የሚዋጋ  የአገር መከላከያ ሠራዊት  አየር ኃይል በሌለው፣ ድሮን በማይጠቀም፣ የሚፈልገውን የጦር መሳሪያ እንደልብ በማያገኝና ደጀም በማይሆነው ሕዝብ መካከል ጦርነት በሚያደርግ ቡድን እየተሸነፈና የደጀን ሕዝብ ከተሞችን አንድ በአንድ በአውዳሚው የጠላት ኃይል እያስወረረ የሚሸሽ ከሆነ ጦርነቱን  “ጦርነቱን ለወታደራዊ ባለሙያዎች ተውላቸው” ሊል ከቶ አይቻለውም።
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ታሪክ ውስጥ እንደ ዐቢይ አሕመድ  ያልተቆጠበ ድጋፉን የሚሰጠውን ሕዝብ በጠላት የሚያስወርር ገዢ፤ ደጀን ሕዝብ ሕይወቱን ያለስስት ለመስጠት ተነስቶ “ለጠላት አስረክባችሁ ከምትሸሹት ትጥቅ እኛን አስታጥቁንና እናንተንም ከጠላት እንታደጋችሁ” እያለ ከልጅ እስከ አዋቂ እየለመነ ራሱን ከወረራ የሚከላከልበትን ትጥቅ የሚያቀርብለት አካል አጥቶ ራሱን መከላከል እየቻለ ሕዝብ ልታደግህ የሚለው አገዛዝ ሕዝብ እንዲታደገው ፍቃደኛ ባለመሆኑ አስተዳድረዋለሁ የሚለውን ሕዝብ  በጠላት እንዲወረር ያደረገ አገዛዝ በምድር ላይ ይኖር ይሆን?
መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከጫካ በወጡ ሽፍቶት የተሸነፈው የሕዝብ ድጋፍ ስላልነበረው ነበር። ዐቢይ አሕመድ ግን አስተዳድረዋለሁ የሚለውን አገር ግማሹ ለጠላት ያስረከበውና  በየቀኑ ታላላቅ ከተሞችን ሲያስወርር የሚውለው ያልተቆጠበና ገደብ የሌለበት የሕዝብ ድጋፍ እየተቸረው ነው።
ፋሽስት ወያኔ ጦርነት ለመክፈት ሁለት ዓመታት ሙሉ እየተዘጋጀ እያየው ትጥቁ፣ ስንቁና ሠራዊቱ በብዛት የሚገኝበትን የሰሜን ዕዝ መጠበቅ ሲገባው ያስመታውን፤ ያ ሁሉ መስዕዋት ተከፍሎበት የተገኘውን ድል ማስጠበቅ ሲገባው ጦሩን አስመትቶ የሸሸውንና ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰባት ወረራና ውደቀት ተጠያቂ  የሆነውን የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ተጠያቂ ስታደርግ የምታገኘው መልስ “ጦርነቱን ለወታደራዊ ባለሙያዎች ተውላቸው” የሚል የተላላኪዎቹ  የመነቸከ ማስተባበያና ለአቅመ ማሰብ ያልደረሱ ኮልኮሌዎች የዘቀጠ ስድብ ብቻ ነው።
“ጦርነቱን ለወታደራዊ ባለሙያዎች ተውላቸው” የተባለለቱ  የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ወታደራዊ ብቃት በውጤቱ ባለሞያነቱ የሚለካው መቼ ነው? በየቀኑ አንድ አንድ ዞን የሚያስወርረው ጦርነት ለወታደራዊ ባለሙያዎች ተውላቸው እየተባለ የሚቀጥለው ወያኔ አዲስ አበባ አካባቢው እስኪደርስ ነው?
መቀሌ ድረስ በርሮ ጣራ ሥር ተከማችቷል ያለውን የጦር መሳሪያ አጋየሁ የሚለው አየር ኃይል ወራሪው ጠላት በመቶ በሚቆጠር መኪና ያውም በጠራራ ፀሐይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችንና ትጥቃቸውን ጭኖ በፈለገው ቦታ እንዳሻው ሲያጓጉዝና ሲያዘዋውር እንዴት አልታየውም?
መቀሌ ጣሪያ ስር የተከማቸን የጦር መሳሪያ ያየው ድሮን የፋሽስት ወያኔ አንበጣ ሠራዊት ከነ ትጥቁ ከኮረም እስከ ሐይቅ ድረስ ባለው አውራ መንገድ በመቶዎች በሚቆጠሩ መኪኖች ላይ ተጭኖ ሲተም፤ ያውም በቀንና በዋናው የመኪና መንገድ ላይ ሲጓጓዝ ሲወል፤ አልፎም  በቴሌቭዥናቸው በቀጥታ ሲያጋጉዙ የሚያሳዩንን ዘር አጥፊ አንበጣ  ሠራዊት ጣራ ስር የተከማቸን የጦር መሳሪያ የሚያየው ድሮን እንደምን አላየውም?  እነ “ጦርነቱን ለወታደራዊ ባለሙያዎች ተውላቸው” ለዚህ መልስ ይኖራችሁ ይሆን?
Filed in: Amharic