>
5:13 pm - Tuesday April 19, 7487

በአሸባሪው አመራሮችና በእኛ አመራሮች መሃከል ያለው ልዩነት...?!? (አሳዬ ደርቤ)

በአሸባሪው አመራሮችና በእኛ አመራሮች መሃከል ያለው ልዩነት…?!?
አሳዬ ደርቤ

 
*…. መንግሥት ዘመቻውን በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ፍላጎት ካለው…
 
➔እነዚያኞቹ ድል ሲያገኙ በፌስቡክም ሆነ በትዊተር ለውስጣዊና ውጫዊ ደጋፊያቸው ዜናውን ያበስራሉ፡፡ የእራሳቸውን ወጣት ሚሊታሪ አልብሰው ማረክን የሚል ፕሮፖጋንዳ ይነዛሉ፡፡ በጦር ጀት ቸብ ቸብ የተደረጉ ቀን ደግሞ ‹‹ገበያ ላይ በተጣለ ቦንብ አንድ ሰው ተጨፈጨፈብን›› የሚል ክሳቸውን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ያደርሳሉ፡፡
የእኛዎቹ ግን በታወከች አገር ላይ የፌስቡክ አካውንታቸውን ዲአክቲቬትና ሎግ አውት አድርገው ጤናቸውን ይጠብቃሉ፡፡ በውጫሌ ከተማ ብቻ 30 ንጹሐን ሲጨፈጭፉ ዜናው በውጭ ሚዲያዎች ቀርቶ በመንግሥት ሚዲያዎች እንዳይዘገብ ያድበሰብሳሉ፡፡ የተማረከውን የሽብር ጦር ይሸሽጋሉ።
 
➔እነዚያኞቹ በክልላቸው ውስጥ ያለውን ወጣት እየለቀሙ ያሰለጥናሉ፡፡ የዘመተውን ደግሞ በግንባር ተገኝተው ያዋጋሉ ወይም ያበረታታሉ፡፡
እኒህኞቹ ግን ቅስቀሳውንም ሆነ መረጃ የመስጠት ተግባሩን ለአክቲቪስቶች አስረክበው በV-8 መኪና ሲንፈሊፈላሰሱና እንቅልፋቸውን ሲቸለፍሱ ያድራሉ፡፡
 
➔እነዚያኞቹ ያላቸውን ትጥቅና ታጣቂ አሟጥጠው በማዝመት ከተሞችን በከባድ መሳሪያ እየደበደቡ ሕዝቡን ካፈናቀሉና ንጹሐንን ከገደሉ በኋላ ሐብቱን ዘርፈው ያጓጉዛሉ፡፡
የእኛዎቹ ግን በራሪ ወፋቸውን እና አብዛኛው ታጣቂያቸውን በአገር ፈንታ የአመራር ጠባቂ አድርገው በአክቲቪስቶቻቸው በኩል ‹‹የመንግሥትን ሥራ ለመንግሥት ትተህ እንደ ሕዝብ ትከት እንደሁ ክተት›› የሚል ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ ይውላሉ፡፡
 
➔እነዚያኞቹ የተለያየ ማንነትና አመለካከት የያዘ ሕዝባቸውን ወደ አንድነት አምጥተው ብሎም ለድርጅቱ ሕልውና የሚሰዋ ሕዝብ ፈጥረው ዘመቻቸውን ይመራሉ፡፡
እኒህኞቹ ግን አንድ መሆን የሚፈልገውን ሕዝብ በታትነው፣ አገራዊ ስሜትን አክስመው፣ በወረፋ ጥቃት ተፈጽሞበት በፈረቃ የሚሞት ሕዝብ ይደለድላሉ፡፡ በአገር ላይ የታወጀውን ጦርነት ለሁለት ብሔሮች አስረክበው ከወረራ በጸዳ ምድር ላይ ይንሸራሸራሉ፡፡
 
➔እነዚያኞቹ ለሕዝባቸው የተላከውን እርዳታ ለሠራዊታቸው ካከፋፈሉ በኋላ በጭነት መኪናው ሠራዊታቸውን እያጓጓዙ ‹‹እርዳታው አልደረሰንም›› እያሉ ይከሳሉ፡፡ 
እኒህኞቹ ግን በአሸባሪው ሃይል የተፈናቀሉና እህል እህል የሚሉ ዜጎቻቸውን በየመንገዱ ጥለው ‹‹ሬሽን ማድረስ ያልቻለው መኪኖቹ ስላልተመለሱ ነው›› እያሉ ያስተባብላሉ፡፡
 
እናስ…
አሸባሪው ቡድን ድል አድርጎ ቢመጣ ሕዝብን ሲቀሰቅሱና ዘመቻውን ሲያስተባብሩ የነበሩ አክቲቪስቶችንና ጥቂት ጋዜጠኞችን እንጂ የብልጽግና አመራሮችን ‹‹ምን በደሉኝ›› ብሎ እርምጃ ይወስድባቸዋል?
በጦርነት መሃከል የሚቃትት ሕዝባቸውን ሥራህ ያውጣህ ብለው፣ መረጃ የማግኘት መብቱን ነፍገው፣ የመረጣቸውን የወሎ ሕዝብ እሱ ያስተዳድርላቸው ዘንድ ፈቅደው፣ ከጥቅማቸው ውጭ ያለውን ሃላፊነት ለአክቲቪስቶች አስረክበው፣ ከደሙ ንጹህ ነኝ በሚል አቋም ድምጻቸውን አጥፍተው የተቀመጡ የፌደራልና የክልል ባለሥልጣናትን በየትኛው ጥፋታቸው ይቀጣቸዋል?
 
በመጀመሪያው ዙር ዘመቻ ሳይወዱ በግዳቸው በቴሌቪዥን ቀርበው ‹‹ጁንታ›› ብለው ከሰደቡት በኋላ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙር ዘመቻ ‹‹ይቅርታ›› ጠይቀው፣ ጠብህ ከአፋርና ከአማራ ጋር እንጂ ከእኛ ጋር አይደለም ብለው፣ ሕዝባቸውን ከዘመቻ፣ እራሳቸውን ከዛቻ አርቀው የተቀመጡ የክልል አመራሮችን ባይሸልማቸው እንኳን እንዴት ሊወነጅላቸው ይችላል?
 
እንደ ሙስጠፌና ታዬ ደንዲኣ ካሉ አንዳንድ አመራሮችና የጦር መሪዎች ውጭ አብዛኞቹ የክልልና የፌደራል አመራሮች በግል አካውንታቸው ይቅርና በመንግሥት ሚዲያ ሥሙን የሚያጎድፍ ንግግር አድርገው በማያውቁበት ሁኔታ በቪ-8 መኪናቸው ካልሆነ ‹‹በአክቲቪስት መራሹ ሥርዓት›› ውስጥ አመራር እንደነበሩ እንዴት ሊያውቅ ይችላል?
 
መንግሥት ዘመቻውን በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ፍላጎት ካለው…
➔በአሸባሪው ሃይል የተለኮሰው ይህ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ እንደመሆኑ መጠን ዘመቻውንም አገራዊ በማድረግ የኢትዮጵያን ሕልውና ማረጋገጥ የሚሹ ወጣቶች ሁሉ የሚሳተፉበትን መንገድ ማመቻቸት፤
 
➔ሁሉም ክልሎች ተጨማሪ ልዩ ሃይሎችን፣ ታጣቂዎችንና ተመላሽ ወታደሮችን መልምለው ዘመቻውን እንዲደግፉ ማድረግ፤
 
➔በተረጋጋ ምቹጌ ውስጥ ሆኖ አገር አፍራሽ ወጣት እየለቀመ የሚልከው አሸባሪ የሰውነቱ ላብ እንዲጨምር የሚያደርጉ ጥቃቶችን በማጠናከር፣ ቀኑን ሙሉ ሰማይ ሰማዩን እያዬ ኦዞን አለመሳሳቱን እና ድሮን አለመምጣቱን ሲያረጋግጥ እንዲውል ማድረግ፤
 
➔የመንግሥትን ሥልጣን ይዘው በአሸባሪው መሪዎችና በምዕራቡ ዓለም መሪዎች ዓይን ውስጥ ላለመግባት የሚጥሩ አመራሮችን የዛቻውና የዘመቻው አካል በማድረግ ለአገራቸው ብቻ ሳይሆን ለሕልውናቸው የሚታገሉበትን እድል መፍጠር፤
 
➔በማሰልጠኛ ጣቢያ ያሉ ወታደሮችን በፍጥነት ሥልጠናቸውን ጨርሰው የሚወጡበትን ስልት መቀየስ፤
 
➔በወራሪው ሃይል ጥቃት ቀያቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ወጣቶችና ፋኖዎች በአንድ ለአምሥት ተደራጅተው ‹‹ለአንድ ቡድን አንድ ክላሽ›› የሚያገኙበትን እድል መፍጠር
 
➔የመንግሥት ሚዲያዎች ከተለምዶ ፕሮግራማቸው ወጥተው በግንባር በመገኘት መረጃ እንዲያደርሱና ብሔራዊ ስሜትን እንዲለኩሱ ማድረግ፤
 
➔የእራስን የዘመቻ ካሌንደር በማዘጋጀት ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገርና ይህ ዘመቻ አሸባሪውን ደምስሰን የአገራችንን ሕልውና የምናረጋግጥበት ይሆን ዘንድ የማይታጠፍ ውሳኔ ማሳለፍ፤
 
➔ከሱዳንና ግብጽ ባለፈ በምዕራቡ አገራት የሚደገፈውን አሸባሪ ለመደምሰስ የማንም እገዛ ባያስፈልገንም አንዳንድ የጎረቤት አገራት የጀመሩትን ወታደራዊ ትዕይንት እንዲያጠናክሩ በማድረግ የአሸባሪውን መንፈስ ማወክ፤
 
➔የጠላትን ወሬ ከማስተባበል ወጥቶ የፕሮፖጋንዳ ብልጫ መውሰድ፤
 
➔ከስር ባለው ፎቶ ላይ የአሸባሪው መሪዎች ወሎ ምድር ላይ ቆመው ጦራቸውን ሲያበረታቱ እንደሚታዩት ሁሉ፣ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሩም ግንባር ላይ እየተገኘ ወታደሩንም ሆነ ወጣቱን እንዲያበረታታ ማድረግ
Filed in: Amharic