የተደበደብኩበት እውነተኛ ምክንያት!
ለሰሚው ግራ እንደሚገባ እረዳለሁ። በእኔ ዕድሜ ተደብዳቢም ሆነ ደብዳቢ የሚባል ሰው አያምርበትም። መደባደብ የሕፃናት ዘመን መለያ ነው። ግን እኮ በአንድ እጅ ማጨብጨብ አለመቻሉም ሌላ እውነታ ነው። በየትኛውም ዕድሜ ቢሆን፣ የግድ መደባደብ የሚፈልግ ካለ፣ ደብዳቢና ተደብዳቢ ይኖራል። ምንም ማድረግ አይቻልም። በዚህኛው ትዕይንት ደግሞ፣ አስደብዳቢም የተጨመረበት ስለሆነ፣ ነገሩን አወሳስቦታል።
***
ተደብዳቢ የሆንኹበትን ሂደት አልገባበትም። የአስደብዳቢዎቼ ወጥመድ ውስጥ መዘፈቅ ነው የሚሆነው። ለመማታት መጀመሪያ የሰነዘርሁት እኔ እሆናለሁ ብሎ የሚያስብ ይኖራል ብዬ አልገምትም። አውዱን ለማስቀመጥ ይህ ይበቃል። ሊደበድበኝ አስቀድሞ ስለሰነዘረብኝ በዙ ማለት ከንቱ ልፋት ነው የሚሆነው። ታላቁ መፅሐፍ እንደሚለው የሚያደርገውን አያውቅምና ወደ ቀናው መንገድ እንዲመለስ ፈጣሪ ይርዳው። በዚህ ልለፈው።
***
ከደብዳቢው በስተጀርባ ስላሉት አስደብዳቢዎቼ ግን፣ ቢያንስ ትንሽ ማለት አለብኝ። ለሕዝባችን ጠቃሚ መረጃ አለኝ።
***
በዚህ ጊዜ፣ ሀገራችን የሞትና ሽረት ትንቅንቅ ላይ ናት። ትንቅንቁን እነ ዐብይ አህመድ ካሸነፉ፣ ኢትዮጵያ በኦ.ህ.ዴ.ድ. በሚመራ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሥር ሆና እንደ ሀገር ትቀጥላለች።
***
በአንፃሩ፣ ሕወሓት ካሸነፈ፣ ሁለት አማራጮች ይኖራሉ። ሕወሓት በቀዳሚነት በሚፈልገው አማራጭ፣ ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ ወደ አራትና አምስት ሀገራት ትበተናለች። ይህ የማይሆን ከሆነ፣ እንደ ቦዝኒያ ትሆናለች። ፈረንጆቹ እንደ ቦዝኒያ መሆንን “ቦዝንፊኬሽን – Bosnification” ይሉታል። ይህ ማለት፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ በይፋ የለም ባይባልም፣ በተግባር ግን እንደ ሌለ የሚቆጠር ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ለእኛ እንግዳ አይደለም። በታሪካችን “ዘመነ መሳፍንት” በሚለው መጠሪያ እናውቀዋለን።
***
ጉዳዩ ይህንን ያህል ክብደት እያለው፣ እንደ እኔ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ሰው ዝም ማለት አይችልም። ፖለቲካ ያለ ሀገር ሊኖር አይችልም። ሁለቱም የሕወኃት መንገዶች ሀገር የሚያጠፉ ናቸው። ግን ይህ ማለት ኢትዮጵያን የምንፈልጋት ሰዎች ለእነ ዐብይ ጭፍን ድጋፍ መስጠት አለብን ማለት ነው ወይ? እኔ “አይደለም፤ ድጋፋችን ጭፍን መሆን የለበትም” ባይ ነኝ። በተለይ እነ ዐብይ ጦርነቱን መምራት እንዳቃታቸው በግልፅ እየታየ ባለበት በዚህ ጊዜ።
***
ይህ አቋሜ ነው ደብዳቢ እንዲላክብኝ ያስደረገው። ለአሁኑ ይህን ብቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወቅልኝ። ሌላውን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ለጊዜው አጥንቴ ተሰብሯል። በዚህ ብቻ በማለፉ ቸሩ መድኃኒዓለምን አመሰግነዋለሁ። ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ጥቃት ማድረስ ይከብዳቸዋል።
***
ከጎኔ ለቆማችሁት ሁሉ፣ ልባዊ ምስጋና ይድረሳችሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠበቅ፣ ይባርክ!