>
5:13 pm - Monday April 19, 1824

እስክንድር እና ፌስታሉ...!!! (አቤል አለማየሁ)

እስክንድር እና ፌስታሉ…!!!

አቤል አለማየሁ

ፌስታልህን_ስጠኝ !    
 /ሜሮን ጌትነት/
      ፌስታል ልትገዛው የማይከብድህ ርካሹ ነገር ነው። ሽንኩርት፣ ዳቦ፣ ሥጋ በፌስታል ማንጠልጠል ደንብ ነው። የማድረግ አቅም እያለህ ልብስህን በፌስታል ከሸከፍክ ግን ምርጫ ነው። ርካሹን ሕይወት ለመኖር መወሰን፣ ስክነትና “በቃኝ” ማለትን ይጠይቃል። የእስክንድር መሠረቱን ካየህ ዕቃውን በፌስታል መያዙ ያደናግርሀል። ግን ሰውየው እስክንድር ነው፤ የከተማው መናኝ። በ’ይበቃል’ የታጠረ፣ ዓለምን የናቀ፣ አዕምሮው የላቀ፣ የማይሰበር ኮከብ።
      የሚመገበው ለመኖር ያህል ብቻ ነው። ያወጣውን ካሎሪ እንኲን ለመተካት ገበታ ላይ አይቀመጥም። ትንሽ ቀምሶ ብዙ ይሠራል። አንድ ሆኖ ብዙ ነው።  አንድ እንጨት አይነድም የሚለውን ብሒል (እውነታ) መቀበል የሚከብደኝ እስክንድርን ሳስብ ነው። ጋዜጣ ላይ አብሬው ሥሠራም ሆነ ሳገኘው፣ ነፍሱ ስትባዝን በስስት ዐየዋለሁ። ማልዶ ቢሮ ይገባል። የጋዜጣም ሆነ የፓርቲ ሥራን ጊዜ በጅቶ ኃላፊነቱን ይወጣል። ከውጪ አገር የሚመጡ ጋዜጠኞችም ሆኑ ከፍተኛ ልዑካን እስክንድርን ማግኘት ቀዳሚ አጀንዳቸው ስለሆነ እስክንድር እረፍት አልባ እንዲሆን ተጨማሪ ምክንያት ይሆኑታል። ነገ ለምትወለደው ዴሞክራሲ ዛሬ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ለራሱ የሚሆን ጊዜ የለውም። ለቤተሰቡ የሚሆን ጊዜ የለውም።
    ለሥልጣን አልታገለም። ለኢትዮጵያችን እና አዲስ አበባችን በተገቢው ቦታ፣ ተገቢው ሥርዓትና ተገቢው ሰው እንዲኖር ነው ሕልሙ። አራት ኪሎ እግር አብዝቶ፣ የግምጃ ቤት ተቆጣጣሪ እና የቱሪዝም ቢሮ ጠባቂ ስላደረጉት አፉን የሚለጉም ጥቅመኛ ፖለቲከኛ አይደለም። እንደ ሲሳይ አጌና ጒደኛውን በሠላሳ ዲናር ሸጦ፣ ክራቫቱን እያጠበቀ በመሪ ፊት የሚያጎነብስ ግብዝ አይደለም። 40/60 ለመሻማት መንገዱን አልጀመረም። የእግሩን አጥንት ይሆናል እንጂ ወኔውን ማንም አይሰብረውም። ተከታዮቹ የሚወርሱት ጥቅመኝነትን አይደለም። ተከታዮቹ የሚወርሱት አለመሰበርን ነው። ተከታዮቹ የሚወርሱት ፌስታሉን ነው። ፌስታሉ በቀላል ነፋስ የማይወሰድ፣ በወኔ የተሞላ፣ ድል ለዴሞክራሲ የሚል ጽሑፍ የሚያርፍበት ነው። ይኸው!!!

ፌስታልህን ስጠኝ !    

   /ሜሮን ጌትነት/
 
ከጠቆረው ገፅህ ከቆዳህ ላይ ውይብ
ከከሳው ሰውነት ከግንባርህ ሽብሽብ
በፅናት ውሃልክ ይታያል ተሰምሮ
ለቃል የመታመን፣ ላመኑት
የመኖር የአላማ ቋጠሮ።
እኔማ…
ከአንተ ጨለማ ውስጥ
በወሰድኩት መብራት
ከአንተ ሰንሰለት ስር ካገኘሁት ፍ’ታት
በአንተ አለመበገር ባገኘሁት ብርታት
ወግ ደርሶኝ ጀግኜ ጬኸቴን ብለቀው
ደርሶ የፈሪ ዱላ
እንደ እያሪኮ ግንብ ተናደ ጭቆና።
እናም ታዲያ ዛሬ…
ወልዶ ላሳደገ ምጥ እንደመካሪ
ቀን የሰጠኝ ቅል ሆንኩ ዞሮ
አንተን ሰባሪ
እርግጥ ገብቶኝ ቢሆን የአላማህ ውጤቱ
መች ያስፈራኝ ነበር ያንተ ብዕር
በልጦ ብረት ካነገቱ
ፍርሃት ባይሆን ኖሮ ስጋት
የሆነብኝ ‘ካፍረቴ እያላጋ
መቼ እዘነጋለሁ የከፈልክልኝን
መራር ትግልና የነፃነት ዋጋ።
አንተ ማለት… ፅናት! መንገድህ አላማ!
ለሌሎች ደህንነት ራስን የመስጠት-
የድምፅ የለሽ አርማ።
ያልከው ዲሞክራሲ …ያለምከው ነፃነት
እስኪመጣ ድረስ…የታገልክለት ቀን
የታሰርክለት ዕለት
በከፍታህ መጠን የሞራል
ልዕልናን እንዳስታውስበት
“ፌስታልህን ስጠኝ
ሙዚየም
ሰቅዬ ራሴን ልውቀስበት!”
ታሪክ ልንገርበት!
Filed in: Amharic