>
5:21 pm - Thursday July 21, 9836

የናንተው ጉድ ነው - ቻሉት እንጂ፣ ታገሱት....!!! (አሳፍ ሀይሉ)

የናንተው ጉድ ነው – ቻሉት እንጂ፣ ታገሱት….!!!

አሳፍ ሀይሉ

ስንት ዓመት አብረውት የሰሩ የሥራ ባልደረቦቹን፣ ስንት ዓይነት ጥቅም ጊያቸው ሥር ተጠግቶ ሲመጠምጥ የኖረውን ከወደቀበት ያነሱትንና ዓለሙን ያሳዩትን ሽማግሌ አለቆቹን፣ ጭንቅል ጭንቅላታቸውን በጥይት እያስበረቀሰ አስገድሎ ፎቷቸውን ባደባባይ የሚያስለጥፍ…
እና የዘመኑ ጀግና ነኝ እያለ.. የሰውን ልጅ ወደ አቧራና ዱቄትነት ቀይሬያለሁ ብሎ የሚደነፋ፣ ባደባባይ የድሮኖች አጠቃቀሙን እየቀደደ የሚፎክር…  የለየለት አረመኔ በሽተኛ ሰው…
ዛሬ የእስክንድር ነጋን አውራ ጣት ሰበረ ብትለኝ ምን ይገርመኛል? የፍቅር ቀልድ ነች ይቺ ለሱ!
አንዴ 30ሺህ ሰዎች ከትግራይ ተፈናቅለው ሱዳን ገብተዋል.. ተብሎ ሲጠየቅ በፓርላማ ፊት “30ሺህ ምኔላት፣ ይቺ ለኛ ቁርስ ማለት እኮ ነች!” ብሎ የተናገረን ቁንጮ አረመኔ…
ዛሬ አንድ ሰውን አስደበደበ፣ አስቀጠቀጠ፣ ሌላ ቀርቶ አስኮላሸና አስገደለስ ብትለኝ ምኑ ይገርመኛል?
የሰውን ማንነት ለማወቅ ሰብዕናው ላይ አተኩር። ሰብዕናውን ልብ ብለህ ተመልከተው። ሰብዕናን ለማወቅ የሚጥሩ ሰዎች ክስተቶች በተፈጠሩ ቁጥር ያዙኝ ልቀቁኝ አይሉም።
የሰው ሰብዕና ማለት የሰውየው “የራስ-ልጓም” ሲገመገም ማለት ነው። ሰውየው እግዜርን ባይፈራ፣ ወይም እግዜርም እፊቱ ተቀምጦ እያየው ቢሆን.. ምን እንደሠራ፣ ምን ከመሥራትስ እንደማይመለስ ማወቅ ነው የሰውን ሰብዕና ማወቅ ማለት።
ላንግሌይ የሚገኘው የሲአይኤ ዋና መሥሪያ ቤት የዓለም መሪዎችን ሁሉ የያንዳንዳቸውን የሰብዕና ፕሮፋይል አደራጅቶ የሚይዝ ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት አለው። የከፋ ሰብዕና ከአደገኛ አቅም ጋር ተዳምሮ ሲያገኙት የመሪውን ነፍስ እስከመቅጠፍና ወደ መቀመቁ ለመክተት ሠማይን እስከመቧጠጥ ይደርሳሉ። ሰብዕናንማጥናትና ማወቅ ዋነኛው የፀጥታ ሰዎቻቸው የሥልጠና አካል ነው።
አንዳንዴ ምናለ ባደለኝና ላንግሌይ የኛውን አረመኔ ጉድ በተመለከተ የተነተነውን የሰብዕና ዓይነትና ማንነት ጉድ ባውቅ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር? እያልኩ እመኛለሁ። ከደረስኩበትና ማንም አስተውሎ ማየት ከሚችለው የተለየ ድምዳሜ ሲአይኤ ከየታባቱ ያመጣል? ብዬም አስባለሁ።
አረመኔ በሽተኛን አንተን ስለተመቸህ፣ ጠላቴ ነው ያልከውን በአረመኔ ጥርሱ ስለከረታተፈልህ ተሸክመኸው ለመዞር ፈቃደኛ ከሆንክ፣ ዕዳውንም ደግሞ ልትቀበለው ግድ የሚል ይመስለኛል። ህፃንን ሲወዱ ከነንፍጡ ነው እንዲሉ።
ለጠላቴ ፍቱን ጠላት ብለህ አዝለኸው የምትዞረው አውሬ.. አንዳንዴም አንተ የምትሳሳለትንም ጀግና ጣቱን ሲያሰብርብህ፣ ጭንቅላቱን ሲነድልልህ ይችላል። እባብን በኪስህ ይዘህ እየዞርክ ለምን ነደፈኝ እንደማይባለው ማለት ነው።
ዋናውን ሠይጣን መሪዬ አምላኬ ብለህ አዝለህ ከቀጠልክ.. ክፋቱንና አረመኔነቱን ሁሉ ደግሞ ቻል አድርገህ አዝለኸው መቀጠል አለብህ።
እና ቻለው፣ ቻሉት ሰውዬአችሁን ነው የምለው ሰዉን። ቻሉት ዕዳችሁን። ቻሉት ጉዳችሁን። ብሶታችሁን ዋጥ አድርጋችሁ ቻል አድርጉት። ያዘላችሁትን ጉድ። ከነምናምኑ ውደዱት እንጂ በነካ እጃችሁ? ነገና ከነገወዲያ ገና ምን ጉድ እንደሚያመጣባችሁ ምኑ ተነካና በቀላሏ ትደነግጣላችሁ?
“ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስቱን ጥዶ ማልቀስ”
ይህ መራሯን እውነት ለማወጅ ሲባል የተፃፈ ግልፅ መልዕክት ነው። ፎቶው ደሞ ከክምችት ክፍሌ የተገኘ። ከሀሳብ፣ ከእስክሪፕቶና ወረቀት ሌላ መሣሪያ የለኝም። ሌላ መሣሪያም አልሻም። ሠላምና ማስተዋል ለሀገራችን ይሁን።
ይኸው ነው።
Filed in: Amharic