>

በጊዳ አያና ወረዳ ሁለት  የህዝብ ማመላለሻ መኪና ሙሉ አማራዎች በ ኦነግ ሸኔ ታግተው ወደ ጫካ ተወሰዱ...!!! (አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ)

በጊዳ አያና ወረዳ ሁለት  የህዝብ ማመላለሻ መኪና ሙሉ አማራዎች በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ታግተው ወደ ጫካ ተወሰዱ…!!!
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ከአንገር ጉትን እና ከኡኬ ቀርሳ አማራ ሚዲያ ማዕከል ለማጣራት እንደሞከረው ሁለት ቅጥቅጥ መኪና ሙሉ አማራዎች ታግተው ወደ ጫካ ተወስደዋል።
ከቀናት ከስቡ ስሬ ወረዳ በቆጅማ የሽብር ቡድኑ በንጹሃን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ40 በላይ አማራዎች በግፍ መጨፍጨፋቸው ይታወሳል።
ከጥቃቱ ተርፈው ወደ ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን መድረስ የቻሉትም በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ መንግስት አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ እንዲሰጣቸው መማጸናቸው ይታወቃል።
የመንደር 10 የመስተዳድር አካላት ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ከቀኑ 5 ሰዓት ኡኬ ቀርሳ ላይ እርዳታ ልትሰጡ ነው በማለት በሁለት መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ (ቅጥቅጥ) መኪና ረፋድ ላይ እንደወሰዷቸው ተገልጧል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት እርዳታ ልትሰጡ ነው በመባሉ  ሴቶች፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞች ሁሉ ይገኙበታል።
ከጊዳ አያና ወረዳ መንደር 10 ወደ ኡኬ ወርሳ ሲጓዙ መገንጠያ በምትባል አካባቢ እንደደረሱ ነው በሽብር ቡድኑና በዘር ማጥፋት ተባባሪዎቹ ከእነ መኪናቸው ታግተው ወደ ሀሙሲት ጉቶ ጊዳ ወረዳ የተወሰዱት።
የኡኬ ቀርሳ ነዋሪዎች እንደገለጹት በርካታ ወንዶች ወደታገቱበት አካባቢ በማቅናት የተኩስ ልውውጥ በማድረግ ላይ ናቸው።
ነዋሪዎች ከመንግስት አካላት መካከል የመንደር 10 አመራሮች የሆኑትን አቶ ዲንቃን፣ የመንደር 10 ከተማ ከንቲባን አቶ ዋጅራን እና የመንደር 10 ሊቀመንበር አቶ በቀለን ጠይቁልን ቢሉም ለጊዜው አድራሻቸውን ለማግኘት አልተቻለም።
አሚማ በደረሰው መረጃ ልክ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ክፍል እና ለምስራቅ ወለጋ ዞን መስተዳድር መረጃውን በማድረስ የታጋቾችን ህይወት እንዲታደጉ ጥሪ አድርጓል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ እና የአንገር ጉትን ከተማ ከንቲባ አቶ ዋሴ የሚጠራ ስልካቸውን ለማንሳት አልፈቀዱም።
Filed in: Amharic