ሸንቁጥ አየለ
ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ለመንግስት ባስተላለፈዉ ጥሪ :-
” ጥብቅ መልዕክት ለመንግስት፣አሁንም አልረፈደም። የትግራይ ተወላጆችን፣ ከህወሀት ጋር ግንኙነት የሌላቸውንም ቢሆን በጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያዎች እንዲሰባሰቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ” ብሏል::
ይሄን የሱን ሀሳብ የሚደግፉ አንዳንድ ሰዎችም ይስተዋላሉ::
——–
ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን የትግራይ ተወላጆችን አስመልክቶ ለመንግስት ያስተላለፈዉ ጥሪ ህዉሃት በአማራ ህዝብ ላይ ካወጣዉ ማኒፌስቶ እንኳን የከፋ መራራ ዘረኝነት ነዉ::
ይሄ ጥሪ ዛሬ ኦነግ በወለጋ የአማራን ህዝብ ሰብስቦ ከሚፈጀዉ ጭፍጨፋ እኩል የለዬለት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነዉ::
————————
ህዉሃት ለማሸነፍ ማንኛዉንም ከፋፋይ አጋጣሚ: ተንኮል እና እድል እንደምትጠቀም ጥያቄ የለዉም::
ስለሆነም ህዉሃት የምትሰራቸዉን ተንኮሎችና ደባዎች በተመጣጣኝ የሰለጠነ ስትራቴጂዎች እና ወታደራዊ ስልቶች ብሎም ህዝባዊ ንቅናቄዎች ማክሸፍ ይገባል::
ሆኖም የትግራይን ነገድ እንደ አንድ አጠቃላይ ኢላማ በመዉሰድ ወደ ማጎሪያ ዉስጥ ይግባ የሚል እንዲህ አይነት ዘረኛ ጥሪ ማቅረብ ታሪክ ይቅር የማይለዉ ስህተት ነዉ::
————–
ዛሬ ጊዜ የሰጠዉ ኦህዴድ ከወሎ ወደ አዲስ አበባ ጦርነት ሸሽተዉ የሚገቡ አማራዎችን በመታወቂያ እየለዬ ወደ አዲስ አበባ አትገቡም ምክንያቱም አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት የሚል ቆሻሻ ዉሳኔ በማሳለፉ በርካታ ጦርነት የሸሹ ዜጎች በመንገድ ላይ እየተስቃዩ ነዉ::
ይሄ የኦህዴድ እርምጃ የመነጨዉ አዲስ አበባን የኛ ብቻ ከሚል ቆሻሻ ህሳቤ ነዉ::
——
ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዉያን ሁሉ ናት::መላዉ ኢትዮጵያ የመላዉ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ሀገራቸዉ ነች::
—-
ካንሰር ሀሳብ ተሸካሚዉ ህዉሃት የጎሳ ፖለቲካን ተሸክሞ አምጥቶ
ኢትዮጵያዉያንን ሀገር አልባ አድርጓቸዋል::ትግራይ የትግሬ ብቻ::ኦሮሚያ የኦሮሞ ብቻ የሚል ቆሻሻ ሀሳብ በኢትዮጵያ ህዝብ መሃል ደፍቷል::
እናም ይሄንኑ አስተሳሰብ ዛሬ ልዩ ልዩ ሀይሎች ተቀብለዉ ተግባራዊ እንዲሆን ሀሳብ ያቀርባሉ::
——
መላዋ ኢትዮጵያ የትግሬዎች ሀገር ነች::ትግሬዎች በገዛ ሀገራቸዉ ወደዬትኛዉም ማጎሪያ ካምፕ ሊገቡ አይገባም::መላዋ ኢትዮጵያ የአማሮች ሀገር ነች::መላዋ ኢትዮጵያ የኦሮሞዎች ሀገር ነች::መላዋ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያን የማትሸራረፍ እና የማትቀናነስ ሀገራቸዉ ነች::
—-
በማንኛዉም መከራ ወቅት : በማንኛዉም የርስ በርስ ግጭት ወቅት:በማንኛዉም የክፉ ቀን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዉያን ሁሉ ነች::
——————
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ !