>

ያጤ ቴዎድሮስ የሩቅ ፍቅረኛ? ወይስ አጥፊ ባላንጣ....??? (አሳፍ ሀይሉ)

ያጤ ቴዎድሮስ የሩቅ ፍቅረኛ? ወይስ አጥፊ ባላንጣ….???

አሳፍ ሀይሉ

ያገሬ ታላቅ ንጉሥ አጤ ቴዎድሮስ ከዚህች ሐውልቷ በጀርባዬ ከቆመላት ወይዘሮ ጋር ከ150 ዓመታት በፊት የተለዋወጧቸውን ደብዳቤዎች እስከዛሬ አንብቤ አልጠግባቸውም።
ሴትዮይቱ እዚህ ባህርማዶ በግዛቷ ላይ “ሞዴል ሚስትና እናት” ከሚል መግለጫ ጋር በጥቁር አንበሣ የታጀበ ሐውልት ቆሞላታል። የእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶርያ።
ይህች ንግሥት ከአጤ ቴዎድሮስ ጋር መልካም ወዳጅነት መሥርታለች። ደብዳቤዎቿ ሁሉ በአጤ ቴዎድሮስ ነገሮች ሁሉ ጉጉት እንዳደረባት ያመለክታሉ። ደጋግማ ቆንስሎቿን ደብዳቤና ሥጦታ እያስያዘች ልካቸዋለች። ወደ ቴዎድሮስ።
የሚገርመኝ ቴዎድሮስ መልዕክተኞቿን አስረውባት እንኳ እስከመጨረሻው ስትለምን የነበረችው ጉዳያቸው በሠላም እንዲቋጭ ነበር። በቴዎድሮስ ላይ ያዘመተችው የህንድ ጦር የተትረፈረፈ ወጪ ቪክቶርያን ከፈረንሳዩ ናፖሊዮን ግብፅ ሲዘምት ካፈሰሰው ንዋይ ቀጥሎ ታላቋ ገንዘብ አባካኝ አድርጓት ተመዝግቧል።
ቪክቶርያ ቴዎድሮስን አሸንፋ እስረኞቿን ሁሉ ይዛ፣ ዕድል እጇ ላይ ካገባላት ምድር በሠላም መሰስ ብላ የመውጣቷ ምሥጢር፣ ከሌሎች ምክንያቶች በተጨማሪ፣ የንግስቲቱ ትዕዛዝ በቴዎድሮስ ጉዳይ ምንኛ ጥብቅ እንደነበር ያመለክተኛል።
ቴዎድሮስ በሽጉጣቸው ራሳቸውን አጥፍተው ከመሞታቸው በፊት ሙሽራ እንደሚቀበል አድርገውት በማያውቁት ሁኔታ ፀጉራቸውን ሹሩባ ተሠርተውና የክት ኩታ ልብሳቸውን ለብሰው የንግሥቲቱን ጦር ሊገናኙ በመሆናቸው፣ ሞታቸው ሳያሳስባቸው፣ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮባቸው እንደነበር በታሳሪዎቻቸው የተፃፉ እማኝነቶች ይገልፃሉ።
አጤ ቴዎድሮስ ካላጡት ሽጉጥ ይቺው ንግሥት ቪክቶርያ በላዩ ላይ በወርቅ ስማቸውን አስቀርፃ በላከችላቸው ሽጉጥ ህይወታቸውን ለማጥፋት መሥረጣቸው ግርም ብሎኝ አያባራም። የአጋጣሚ ይሆን?
አንዴ ለዚህች ወይዘሮ መልዕክተኞቿ አፄ ቴዎድሮስ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ንጉሥ መሆናቸውን ነግረዋታል። እና ቪክቶርያ ሳታስታውቅ ከብዙ ገፀበረከቶች መሐል ውድ የነገሥታት መጫሚያዎችን ጨምራ ላከችላቸው።
አጤ ቴዎድሮስ ሥራዋን አውቀው በቀጣዩ መልዕክተኛ በዕውቅ አንጥረኛ ሙሉ በሙሉ ከንፁህ ወርቅ የተሠራ ውብ ነጠላ-ጫማ ለንግሥት ቪክቶርያ በገፀ-በረከትነት ላኩላት። እንዴት ልቧ በፍቅር እንደሚቀልጥ ማሰብ ደስ ይለኛል።
በፀብ ጊዜ ደሞ ቴዎድሮስ መልሰው የቪክቶርያን መልዕክተኞች እስከ ባህረነጋሽ የሚሸኛቸው ወታደር ላኩና ሰዎቹ ወደታንኳቸው ከመሻገራቸው በፊት ጫማዎቻቸውን አውልቀው የጫማ ተረከዞቻቸው እንዲታጠቡ በማድረጋቸው ይታወሳሉ።
መልዕክተኞቹ ምክንያቱን ቢጠይቁ የተነገራቸው የቴዎድሮስ ቃል አንዲትም አፈር ከዚች ሀገር ይዛችሁ እንደማትወጡ ለማረጋገጥ ነው የሚል ነበር። ንግሥት ቪክቶርያ ይሄ ሁሉ እንግዳ ወሬ ይደርሳታል ስለ ቴዎድሮስ።
ስለ ሁለቱ ባህር የተሻገረ የተለየ ግንኙነት ሳስብ አጤ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ ንግሥት ቪክቶርያ ልጅ አለማየሁ ቴዎድሮስን አንቀባርራ ያኖረችበት እንግዳ የልግሥና ታሪክ ይመጣብኛል። ደሞ እንደ አጤ ቴዎድሮስ አንበሶችን መውደዷ! ጉድ እኮ ነው!
ሳስበው ዕድል ቢያገኙ ኖሮ አጤ ቴዎድሮስና ንግሥት ቪክቶርያ የሠሎሞንንና የንግሥተ ሳባን ታሪክ አይደግሙት ይሆን? እያልኩ በራሴ ከልክ ያለፈ ምኞት ፈገግ እላለሁ።
አጤ ቴዎድሮስ በጥቅምት 20 ቀን 1855 ዓ.ም. ይባባ (ጎጃም) ላይ ለዚህች ከጀርባዬ ሐውልቷ ለቆመው ለንግሥት ቪክቶርያ የፃፉት ደብዳቤ እንዲህ የሚል መማጠኛ ነበረበት፦
“የተከበርሽ ንግሥት ቢክቶርያ፣ … እነ አቶ ቡላዲን (ፕሎውደን)፣ እነ ሊቀመኳስ ዮሐንስ የክርስትያን ንግሥት ታላቅ ሰው ክርስትያን የሚወዱ አሉ እናስተዋውቅሀለን እያሉኝ እጅግ እወዳቸው ነበረ። የእርስዎን ወዳጅነት ያገኘሁ እየመሠለኝ።
“ሞት አይቀርምና የጠሉኝ ሰዎች እኔን ይክፋው ሲሉ ገደሉዋቸው። እኔም በእግዚአብሔር ኃይል  ደመኞቼን አንድ ሳልተው ፈጀሁዋቸው። የገዛ ዘመዶቼን (እነ ጋረድን ሳይቀር) የእርስዎን ዝምድና ስፈልግ።…
“ቱርኮች ከባህር ሆነው መልዕክተኛዬን አላሳልፍም ብለው ቸግሮኝ ሳለ፣ ኬምሮን (ካሜሮን) መጣልኝ። ደብዳቤዎንና የፍቅር ገፀበረከት ይዞ። በእግዚአብሔር ኃይል እጅግ ደስ አለኝ። … – ዛቲ ጦማር ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ ዘ አቢሲንያ.. ። ጥቅምት 20 ቀን 1855 ዓ.ም.።”
(- ይህ ደብዳቤ የተገለፀው፣ በተክለፃድቅ ከተፃፈው “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀኃሥ” የሚል መፅሐፍ ገፅ 26 ላይ ነው። )
ቴዎድሮስ የቪክቶርያን ልብ በልተው ከጎጃም የላኩትን ደብዳቤ ለንግሥቲቱ ልዩ መልዕክተኛ ለደንካን ካሜሮን በእጅህ አድርስልኝ ብለው ቢሰዱት፣ እርሱ በባቡር ላከው።
ተመልሶ ሲመጣ ጠየቁት “አደረስክ ወይ መልዕክቴን?” ብለው። ካሜሮን “እንዲፈጥን ብዬ በባቡር ነው የላኩላት” ብሎ መለሰ። አጤ ቴዎድሮስም ለመዋቀስ ብለው “እንዴት አደራ ብዬ የሰጠሁህን መልዕክት በሌላ ትሰዳለህ?” ብለው ቢገስፁት፣ ካሜሮን ሆዬ ጥጋብ የነፋው ነበርና እንዲህ ብሎ በግልፍት መለሰላቸው፦
“እርስዎ ከመልዕክቱ መድረስ እንጂ ከእኔ ማድረስ ምን አለዎት? እኔኮ ዓለምን አንቀጥቅጣ የምትገዛው የተከበረችው የእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶርያ መልዕክተኛ ነኝ እንጂ፣ የእርስዎን መልዕክት አድራሽ የግል ተላላኪዎ፣ ወይም ሚኒስትርዎ አይደለሁም!”
ቴዎድሮስ በቁጣ ዙፋናቸው እስኪንቀጠቀጥ በቁጣ እየፈከሩ ወታደሮቻቸውን “በል ንሳ ይሄን ነጭ ጥጋበኛ!” ብለው ሲያዙ፣ ካሜሮንን በጥፊና በዱላ እያዳፉ አሠሩት። አጤ ቴዎድሮስም በካሜሮን ፊት እየተንደቀደቁ ሲፈክሩ እንዲህ እያሉ ነበር፦
“እኔ መይሳው! አንድ ለእናቱ! እኔ ላንተ ተናንሼህ (ንቀኸኝ) ነው? የላኩህን መልዕክት በእጅህ አለመስጠትህ?.. እንኳን ይኸ አንድ ነጭ ወታደር… እርሷ ራሷ ንግሥትህስ ብትሆን ለኔ ተናንሳ ነው? ባህሯን ተማምና ነው እንጂ! መጥታ ተሜዳ ፊቴ አትቆምም! እኔ አንድ የናቱ!”
(- ይሄ የቴዎድሮስ የፍከራ ቃል ፉዜላ ካሳተመው የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ገፅ 30 ላይ፣ እና በቻርለስ ቲ ቢ ከተፃፈው The British Captive in Abyssinia ከሚለው መፅሐፍ ገፅ 204 ላይ የተገኘ ነው)።
በዚያን ዕለት የካሜሮን ጥጋብ ባመጣው ጦስ ከካሜሮን ጋር 4 እንግሊዞች፣ 2 ጀርመኖች፣ 2 ፈረንሳዮችና 1 ኢጣልያዊ በድምሩ 9 ነጮች ታሠሩ። በጋፋት ደሞ 8 ሚሲዮናውያንና አገር አሳሾች ታሰሩ።
ቪክቶርያ በበኩሏ የውስጥ እግሯን ሳይቀር ክፉ እንዳይነካት የወርቅ ጫማ በሚያለብሷት ኢትዮጵያዊ አፍቃሪዋ ላይ መጨከን አልፈለገችም። በካሜሮን ፋንታ ሌሎችን ቆንሲሎች፣ ሀኪሞችና የጦር መኮንኖች ላከችላቸው።
የቪክቶርያ መልዕክተኞች ከምጥዋ በቦጎስ፣ በከረን፣ በከሰላ፣ በመተማ አድርገው አጤ ቴዎድሮስ ሰፍረውበት ከነበረው በዘጌ በኩል ቆራጣ ላይ ደረሱ።
ሲደርሱ፣ አጤ ቴዎድሮስ ቁጥሩ 10,000 የሚደርስ ፈረሰኛ ወታደር አሰልፈው፣ ራስ እንግዳ በሰልፈኛው መሐል አልፈው የንግሥቲቱን መልዕክተኛ እንግዶች ተቀብለው ንጉሠ ነገሥቱ ወዳሉበት ዙፋን እንዳደረሷቸው፣ ደስታና ፌሽታ ታላቅም ግብዣ እንደተደረገላቸው ከላይ የጠቀስኩት እንግሊዛዊ እማኝነቱን ገልፆ እናገኘዋለን።
አቀባበሉና ድግሱ ካበቃ በኋላ ራሳም የተናፋቂዋን የንግሥት ቪክቶርያ ደብዳቤ ለአጤ ቴዎድሮስ አቀረቡ። ሲከፈት የቪክቶርያ ደብዳቤ አጭር ቃል የያዘ ነበር። የተፃፈው በእንግሊዝኛ ነው። ራሳም ወደ አረብኛ ተረጎመው። የንጉሡ ሸሪክና ሠላይ ሣሙኤል ጊዮርጊስ ደግሞ ከአረብኛ ወደ አማርኛ ተረጎመው። የቪክቶርያ ደብዳቤ ለቴዎድሮስ እንዲህ ይነበባል፦
“ካሜሮንን ሾሜ መላኬ በሁለታችን መካከል ወዳጅነት እንዲፈጥር ነበር። አሁንም ራሳምን ልኬዋለሁና እስረኞቹን ፈትተው ከነራሳም ጋር ሲልኩልኝ፣ በሁለታችን መካከል ወዳጅነት ታድሶ የጠየቁኝንም እፈፅማለሁ።”
ይህች ከጀርባዬ የቆመች ንግሥት። ይህች ሞዴል ሚስትና እናት በሚል ባገሯ የተወደሰች ወይዘሮ። ካገሬ ጀግና ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ በፍቅር ወድቃ ይሆን? ቴዎድሮስስ ሰዎቼ ታሰሩብኝ ብላ በርራ ወደ ሀበሻ ምድር እንድትመጣላቸው ከጅለው ይሆን? አላውቅም።
የምዕራባውያን ፊልም ሠሪዎችበአንዲት እግር ጫማ ታሪክ ላይ ተንተርሰው ጉድ የሚያሰኙ ታሪካዊ ፊልሞችን ለዓለም አቅርበው አስደምመውናል። የምናፍቀው አንድ ቀን የኛም ሀገር የጥበብ ባለሙያዎች ከቱባ ታሪካችን ጋር ተገናኝተው ዓለምን የሚያስደምም ታሪካችንን ለትውልዱ ከሽነው የሚያቀርቡበትን ዘመን ነው። እርግጠኛ ነኝ አይቀርም። አንድ ቀን።
ታላቅ ነበርን፣ ታላቅም እንሆናለን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ።
Filed in: Amharic