>

‹‹ሕወሓት ገፋ ሲባል አንድም ሰው አልደወለልኝም...!!!››  ጠ/ሚ/ር ዐቢይ

‹‹ሕወሓት ገፋ ሲባል አንድም ሰው አልደወለልኝም…!!!››
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ

*…. ጥቅምት 22/2014 (ዋልታ) ባለፈው 15 ቀን አሸባሪው ሕወሓት ልጠቃ ነው ሲል ከዓለም የማይደውል አልነበረም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሽብር ቡድኑ ገፋ ሲባል ግን ድምፃቸው ጠፍቷል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሰጡት ማብራሪያ ‹‹ባለፈው 15 ቀን አሸባሪው ሕወሓት ሊያጠቁኝ ነው ሲል እኔ መቀመጫ አልነበረኝም ከዓለም የማይደውል አልነበረም፤ እነሱ ገፉ ሲባል ሰላም ነው አንድም ሰው አልደወለልኝም›› ሲሉ ነው ዓለም ዐቀፍ ነኝ የሚለውን ማኅበረሰብና ፅንፈኛ የምዕራባዊያን አገራት መሪዎችን ሚዛን የሳተ አቋም ያስረዱት፡፡
የሽብር ቡድኑ ተጠቃሁ ሲል ጫና ለማሳደር ‹ተው አታጥቃ› የሚለው ሰው እንደሚበዛ  በማስቀደምም ‹‹እነሱ (አሸባሪው ሕወሓት) ገፉ ሲባል ሰላም ነው፤ እኛ ልንገፋ ነው ሲባል ግን ሽብሩ ብዙ ነው›› ሲሉ አክለዋል፡፡
መንግሥት መሆን ከዚህ አንፃር ጉዳት ቢኖረውም ‹‹አይዛችሁ ሥራችሁን ስሩ በመልካም ዜና ደግሞ መልሰን እንገናኛለን›› ሲሱ ነው ለከፍተኛ ባለሥልጣናቱ መመሪያ የሰጡት፡፡
ኢትዮጵያ ላይ ተላላኪ መንግሥትን የመፍጠርና ደካማ አገር የማድረጉ የውጭ ፍላጎቶች አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ግልፅ ሆነው ወጥተዋል፡፡ የተከፈተባቸውን ጦርነት በመመከት ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል የሚጥሩት መንግሥትና ኢትዮጵያዊያን ላይ ጫና ማሳረፍና በተባበሩት መንግሥታት ኃላፊዎች በኩል ሳይቀር የሽብር ቡድኑን የመደገፉ አካሄድ ፈጦ የመጣውም ከዚሁ ፍላጎት መሆኑ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡
ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃንም የዚሁ ፍላጎት ማሳኪያ ስልት ሆነው በግልፅ አገር የማፍረስ ሥራ ውስጥ መጠመዳቸውም ሌላው ማሳያና ለኢትዮጵያዊያን ዛሬም ያልረፈደ የማንቂያ ደውል ነው፡፡
Filed in: Amharic