ወይም እኛ ወደ ሞት ሄደን እንገድለዋለን…!!!
ሙሃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት
ኢትዮጵያውያን ሁለተኛውን መርጠናል። አንዲት ነጥብ አለች ታሪክ የምትቀይር። ዕድል ተሰጥቶናል። የኛ ጥረት እየተነሣሣ ነው። ሁለቱ የሚገጥሙባት ነጥብ ላይ እየደረስን ነው። ይህቺ ነጥብ የኢትዮጵያን ታሪክ ትቀይራለች። ዓርብ ላይ ነን። እንደ ይሁዳ የሚሸጡ፣ እንደ ጴጥሮስ የለሁበትም የሚሉ፣ እንደ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ነገር ሁሉ ያለቀ መስሏቸው ጥለው የሚሸሹ ይኖራሉ። እኛ ግን ከዮሐንስ ጋር እንጽና። የኤምባሲዎቹ ማጓራት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድንፋታ፣ የዓለም ሚዲያዎች ፉከራ የሚቀየርበት ነጥብ ላይ እየደረስን ነው። ያንን ለማየት እንደ ዮሐንስ መጽናት ይጠይቃል።
ዮሐንስን ነገር ሁሉ አልቋልና ወደ ዓሣ አጥማጅነት እንሂድ ብለውት ነበር። አይሁድ ከውስጥ፣ ሮማውያን ከውጭ ሆነው ሽብር እየነዙ ነበር። በድል ስሜት እየሰከሩ ነበር። አለቀ ደቀቀ ብለው አጋና እየተማቱ ነበር። ነገር ግን በእነርሱ ልብ ያለቀው ነገር በዮሐንስ ልብ ገና እየጎመራ ነበር። ስለዚህ ዝም አላቸው።አርምሞው ተደሞ ነበረበት። ታሪክ ሲቀየር እየታየው ይገረም ነበር። በዚያ ሰዓት እንኳን ዮሐንስ እያሸነፈ ነበር። ታላቅ ስጦታ፣ ድንግል ማርያምን ያህል ስጦታ እያገኘ ነበር። ይሄንን ከእርሱ በቀር ያየ የለም። ለዚህ ነው ስለ ስጦታው ተቀባዩ ዮሐንስ ብቻ በወንጌሉ የነገረን።
እያገኘን ነው። የሚያውቀው ግን የደነገጠው ሳይሆን ጸንቶ ቆሞ የሚያገኘው ነው።