ሮላንድ ማርቻል
ጥቅምት 25/2014 (ዋልታ) ከ3 ዓመት በፊት በሕወሓት ፈላጭ ቆራጭነት ይመራ የነበረው መንግሥት የተከተለው የአገዛዝ ስርዓት ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ጦርነት ምክንያትና ተጠያቂ እንደሆነ በዓለም ዐቀፍ የምርምር እና ሳይንስ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪው ሮላንድ ማርቻል ገለፁ፡፡
የፈረንሳዩ ፍራንስ 24 ቴሌቪዥን ዘ-ዲቤት በተሰኘው መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
ጋዜጠኛው ማርክ ኦውን የኢትዮጵያ መንግሥትና የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ወደዚህ ጦርነት እንዴት ሊገቡ ቻሉ? ሲል ጠይቋል፡፡
የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን አገር ለማፍረስ አልሞ በመላ ኢትዮጵያዊያን ላይ ስለከፈተው ጦርነት ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት በሚነሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ላይ በርካታ ጥናቶችን የሰሩትና በዓለም ዐቀፍ የምርምር እና ሳይንስ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሮላንድ ማርቻል ማብራሪያ ሰተጥተዋል፡፡
እንደ ተመራማሪው ገለፃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት የነበረውና በሕወሓት የሚመራው መንግሥት ይከተል የነበረው የአገዛዝ ስርዓት ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ጦርነት ተጠያቂነቱን ይወስዳል፡፡
የሕወሓት ቡድን በሥልጣን ዘመኑ አምባገነን ነበር ያሉት ተመራማሪው ማርቻል በሕዝቡ ዘንድም የሚወደድ እንዳልነበር ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን የመጡበትም ምክንያት ሕዝቡ በሕወሓት አገዛዝ ላይ ያነሳው ተቃውሞ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተረከቧት ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ የተፈናቀሉ፣ እዚህም እዚያም ግጭቶች እና ስርዓት አልበኝነት የሚስተዋልባት እና በበርካታ ውጥንቅጦች የተሞላች እንደነበረችም ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡
ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት ቀላል አልነበረም ያሉት ማርቻል ትልቁ ፈተና ያጋጠመውም በሕዝብ ተቃውሞ ከሥልጣኑ ከተባረረው የሕወሓት እንዲሁም ራሱን የኦሮሞ ህዝባዊ ሰራዊት ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅሞ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከመክፈቱ በፊትና ከመጋቢት 2010 ወዲህ 113 ግጭቶች ከትግራይ ክልል ውጭ ሲከሰቱ በሁሉም ግጭቶች ውስጥ የሽብር ቡድኑ እጅ እንደነበረበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ እንደራሴዎች ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም አገሪቱ በፌደራሊዝም ስርዓት መመራቷን ዜጎቿ አጥብቀው የሚፈልጉት ቢሆንም አተገባበሩ ላይ ቅሬታ እንዳለባቸውም ተመራማሪው ጠቁመዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው ገለፃ በክልሎች መካከል ያሉ ወሰኖች ሲከለሉ የአካባቢውን ነባር ማኅበረሰብ ፍላጎት ያላገናዘበ፣ ለማስተዳደር ምቹ መሆን አለመሆኑ ያልታሰበበት እና ለአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ያደረ ነው፡፡ ይህም የሕወሓት ሕዝብን እርስ በእርስ እያናከሱና በጥርጣሬ እንዲተያዩ እያደረጉ ረጅም ዘመንን በአዛዥ ናዛዥነት አገርን የመግዛት ፍላጎት ውጤት ነው፡፡