>

ሸኔ እና "ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ"...!!! አንዱአለም ቦኪቶ ገዳ

ሸኔ እና “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ”…!!!

አንዱአለም ቦኪቶ ገዳ

*…. አሁን ከ30 አመት በኋላ  ኦነግ  አሁንም የራሱ ሮድ ማፕ ሳይኖረው ቁልጭ ቁልጭ እያለ የራሰቸው እቅድና አላማ ያላቸውን ጎልማሶች ከሚሴ ጋር ጠብቆ  “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ” እያለ ይገኛል….
ልጅ እያለን አሰላ ውስጥ የጦፈ የእግር ኳስ ሊግ ነበር፡፡ ኒያላ፡አርዱ ፡አርሲ ፖሊስ፡ብቅል ፡ከነማ ወዘተ፡፡
ካለማጋነን የጁቬንትስን ማሊያ በሚለብሰው እና ንብረትነቱ የጣሊያናዊው አባ ሲልቪዮ የሆነው ኒያላ እና አርሲ ፖሊስ ሲጫወቱ የነበረው ሙቀት ሸገር ላይ በቡና እና በጊዮርጊስ  ፣ወይ ያኔ  ሮም ላይ ላዚዮ እና ሮማ ሲገናኙ ከነበረው ድምቀት አይነተናነስም፡፡እኔም በወቅቱ የአባ ሲልቪዮ ት/ቤት(ሚሽን) ተማሪ እንደመሆኔ ቅልጥ ያልኩ የኒያላ ደጋፊ ነበርኩ፡፡ቅዳሜ ወይ እሁድ ደርሶ የአሰላ አረንጔዴው ስታዲየም ደርሼ የምወደውን የእግር ኳስ ክለብ ከተቻለ ሙሉውን ካልተቻለ ሊያልቅ 15 ደቂቃ ሲቀረው  ገብቼ እስከማይ ድረስ በጣም እጓጓ ነበር፡፡(ድሮ ስታዲየም ጨዋታው ሊያልቅ 15 ደቂቃ ሲቀረው በሮች ይከፈቱና በነጻ ይገባ ነበር፡፡)
ችግሩ ምን መሰላችሁ ….በእኛ ቤት ፕሪንስፕል  ስታዲየም ገብቶ ኳስ ማየት፡ብስክሌት መንዳት፡ሰፈር ውስጥ አባሮሽ መጫወት፡ወንዝ ሄዶ ከልጆች ጋር መዋኘት በሙሉ የዱርዬ ስራዎች ናቸው፡፡ ማዘር መላው የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን የፈለሰፉት ሰዎች የድሮ ዱርዬዎች ናቸው ብላ ሳታስብ አትቀርም፡፡
እና አንዲ በልጅነቷ የምትወደውን የኒያላ ቡድን ሲጫወት ለማየት እንኳንስ 0.50 ሳንቲም ከቤተሰብ ሊሰጣት ይቅርና ስታዲየም እንደገባች እራሱ ከታወቀባት የሚጠብቃት በርበሬ መታጠን ነበር(ድሮ ግን በርበሬ እርካሽ ከመሆኑ የተነሳ የቅጣት መሳሪያ ሁላ ነበርኣ!) ፡፡
ችስታዋ አንዲ ቅዳሜ የኒያላ ጫወታ ካለ “ጓደኛዬ ቤት መጻፍ ላነብ ነው” ብላ ስታዲየም ትሄድና ከረዥሙ ሰልፍ ፈንጠር ብላ ትቆማለች፡፡ ከዛ አንድ ጎልማሳ ወደ ስታዲየም ሲያመራ ሮጥ ብላ እጁን ትይዝና “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ” ትላለች፡፡የድሮ ሰው ደግሞ ደግ ነው፡፡ አዋቂ ሰው ስታዲየም ሲገባ ልጁን በነጻ ይዞ መግባት ስለሚችል ፈታሾቹን እስከታልፍ እጅህ ይይዝህና ልክ ፈታሾቹን እንዳለፍክ ይለቅሃል..ከዛ ብርር ነው ወደ ካታንጋ…. ከዛ በኋላ ማን ይዞህ እንደገባ ራሱ ትዝ አይልህም፡፡
ኦነግ የሚባል የልጅነት ታሪኬን የሚያስታውሰኝ እንደው ሲፈጥረው “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ” የሆነ ድርጅት አለ፡፡
60 አመት ሙሉ ምን ትርጉም ያለው ስራ ሲሰራ እንደቆየ ፈጣሪ ይወቅ …
ብቻ ማንም ወደ አዲስአበባ እያቀና ይምስለው ብቻ …ጠጋ ይልና እጅ አፈፍ ያደርጋል…
ከዛ “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ” ብቻ ነው ጥያቄው….
እኔ በ1983 ዓ.ም. 50 ሳንቲም ሳይኖረኝ “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ “ስል ኦነግም እንዲሁ የህወሃትን እጅ ይዞ “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ” ብሎ አዲስአበባ ገብቶ በአመቱ “ጨወታው ደበረኝ” ብሎ ወጥቷል….
አሁን ከ30 አመት በኋላ እኔ እንኳን ችግሬ ተቀርፎ በቀን 50 ሺብር ማጥፋት ስጀምር(ሎል) ኦነግ ግን አሁንም የራሱ ሮድ ማፕ ሳይኖረው ቁልጭ ቁልጭ እያለ የራሰቸው እቅድና አላማ ያላቸውን ጎልማሶች ከሚሴ ጋር ጠብቆ  “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ” እያለ ይገኛል….
አሁን ላይ ለኦሮሞ ህዝብ እታገላለሁ የሚለው  ኦነግ/ሸኔ “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ” ብሎ የሚይዘው እጅ ግን በኦሮሞ ደም እስከ ክንዱ የተጨማለቀ እጅ ነው…!
ወንድሜ ከድሮ ልምዴ ልምከርህ
ዛሬ ላይ “ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ” አያዋጣም!…ብሮ ፈታሾቹ እንደ ድሮው አይደሉም…!ጋሼህን እና ጋሼውን የያዝክበትን ክንድህንም  ጭምር አብረው ይጎምዱልሃል፡፡
መልካም ቀን
Filed in: Amharic