>

ፈጣሪ ሆይ! አሜሪካ ለኢትዮጵያ እንዳታስብላት አድርግ፤ እባክህ!  (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

ፈጣሪ ሆይ! አሜሪካ ለኢትዮጵያ እንዳታስብላት አድርግ፤ እባክህ!
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
.


አሜሪካ የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳስቧት ያለ እንቅልፍ ስታድር አመት አልፏታል፤ ይህን ስመለከት የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት፣ ባይደን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ከመሰለኝ ቆይቷል፡፡አጥብቃ ስለኢትዮጵያ መግለጫ ታወጣለች፤ መልእክተኛ ትልካለች፤ የምጽአት ዜና ትፈጥርላታለች፡፡
.
አሜሪካ ስለኢትዮጵያ ታስባለች፡፡ ዛሬ እንኳን በቀን ሁለት ጊዜ በሰጠችው መግለጫ ያሳሰባትን፣ እንቅልፍ የነሳትን ነግራናለች፡፡ አሜሪካ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የትግራይ ተወላጆች መዋከብ አሳስቧታል፤ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ሀርቡ እና ከሚሴ፣ አፋር . .  የተረሸኑት የአማራ፣ የአፋርና የኦሮሞ ወጣቶች አያሳስቧትም፡፡ በኢትዮጵያ በየክልሉ የሚጠራው ብሄር ተኮር ክተት ያሳስባታል፤ አሸባሪው ህወሀት አማራ ላይ ያወጀው ‹‹ሂሳብ ማወራረጃ›› እልቂት አያሳስባትም፡፡ በራሱ በህወሀት የተነሳ ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ማድረስ አለመቻሉ ያሳስባታል፤ በህወሀት የሚዘረፈው የአማራ ሀብት፣ የሚታጨደው ሰብል አያሳስባትም፡፡  ‹‹የተከበበችው›› አዲስ አበባ ጉዳይ ያሳስባታል፤ የወልዲያ፣ የደሴ፣ የከምቦልቻ፣ ከሚሴ፣ ጭፍራ፣ . . .  ጉዳይ አያሳስባትም፡፡ . . .
አሜሪካንን ለምን እንዲህ አሰብሽ ብለን መጠየቅ የዋህነት ነው፤ ኢምፕሪያሊስቶች የሚያስቡት እንዲህ ነው፡፡ ለሀገራት ሲያስቡ እስከመጨረሻው ነው፤ ስለሊቢያ አስበዋል፤ ስለአፍጋኒስታን አስበዋል፤ ስለኢራቅ እንቅልፍ አጥተዋል፤ ስለየመን አስበዋል፤ . . . .
.
ልብ እንበል! ስለሀገራችን- ስለአማራ፣ ስለኦሮምያ፣ ስለትግራይ፣ ስለአፋር፣ ስለሱማሌ፣ ስለሀረሪ፣ ስለጋምቤላ፣ ስለቤንሻንጉል፣ ስለሲዳማ፣ ስለደቡብ ህዝቦች፣ ስለደቡብ ምእራብ፣ ስለአዲስ አበባ፣ ስለድሬዳዋ ማሰብ ያለብን እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እንጠይቅ! ባህር አቋርጦ አሜሪካና አውሮፓ ስለእኛ ስለምን ያስባል? ምን ፈልጎ? . . .  ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ፣ ከምእራብ እስከ ምስራቅ ጫፍ ስለኢትዮጵያ ማሰቢያው፣ በአንድነት መነሻው ጊዜ ዛሬ ነው፡፡  . . . .በህብረት ለሀገራችን እናስብ፤ እንስራ፤ እንድናለን፡፡
Filed in: Amharic