ታሪክን ወደኋላ
ከ 85 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን በአድዋ ጦርነት ጀግንነታቸው ያስመሰከሩት እንዲሁም በ 2ተኛው የኢትዮ ኢጣሊያን ጦርነትም ወቅት በእርጅና ዕድሜያቸው ዳግም የዘመቱት ጀግናው ኢትዮጵያዊው አርበኛ
ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) በተወለዱ በ 75 ዓመታቸው ህይወታቸው ያለፈበት ዕለት ነበር።
ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) የተወለዱት በ 1854 ዓ.ም ነበር። በመጀመሪያ ደጃዝማች ባልቻ በአጼ ምኒልክ ጦር ተማርከው ነበር ወደ ቤተመንግሥት የገቡት። አፄ ምኒልክም የማረኩትን ከማስጨነቅ ይልቅ በእንክብካቤ መያዝና ማስተማር ይቀናቸዋልና ታዛዥና ታማኝ ሆነው ያገኟቸውን ባልቻን በግምጃ ቤታቸው እንዲሰለጥኑ አደረጓቸው።
ደጃዝማች ባልቻም በጥረታቸው ከበጅሮንድነት ተነስተው እስከ ደጃዝማችነት ማዕረግ ደረሱ። በአድዋ ዘመቻም ተሳትፈው በመድፍ ተኳሽነታቸውና በጀግንነት ስለታወቁ
” ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፤
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ።” ተብሎ ነበር የተገጠመላቸው።
ከአድዋ ጦርነት በኋላ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ በተለያየ ጊዜ ሲዳሞን እንዲሁም ሐረርጌንና ባሌን አስተዳድረዋል። በሰጌሌ ጦርነት ወቅትም ከተማ ጠባቂ ተብለው ተሹመው አዲስ አበባን አረጋግተው አቆይተዋል።
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በአድዋ ድል ከሆነ ከአርባ ዓመት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን ሊወር ሲመጣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ( አባ ነፍሶ) በእስተርጅና እድሜያቸው ከአርበኞች ጋር አብረው ሆነው ዘመተዋል። በጊዜው “እርስዎ አይችሉም ለኢጣሊያ ደግፉ” የሚሉ ሽንገላዎች ለደጃዝማች ባልቻ ቢቀርብላቸውም እርሳቸው ግን “ሸምግያለሁ መሞቴ እንደው አይቀር በሰማይ ጌታዬ ምኒልክ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ ማነው የተቀመጠው ብለው ቢጠይቁኝ ምን ብዬ እመልሳለሁ ” ብለው በዘመቻቸው ገፍተው በስተደቡብ አዲስ አበባ ረጲ ድረስ በመሄድ ሲዋጉና ሲያዋጉ ቆይተዋል።
በመጨረሻም ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ሀገራቸውን ከፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ነፃ ለማድረግ ሲዋጉ ቆይተው ጥቅምት 27 ቀን 1929 ዓ.ም አቤቤ በተባለ ቦታ በኢጣሊያ ጦር ተገድለዋል ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።
ያስቆረጥማል ጠላቱን ኮሶ
የዳኘው ጀግና ባልቻ አባ ነፍሶ።
በጦርነቱም ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ጆሯቸው በመቆረጡ ምክንያት ባለቅኔው ለደጃዝማች እንዲህ በማለት ነበር ያሞገሳቸው:-
ማን እንዳተ አርጎታል የእርሳሱን ጉትቻ
የዳኘው አሽከር አባ ነፍሶ ባልቻ።
ክብር ፣ሞገስና ዘላለማዊ ዕረፍት ለጀግኖች አርበኞቻችን !!!
#ታሪክን_ወደኋላ