ትህነግና ተረኛ ተጋላቢ ፈረሶቹ….!!!
(ክፍል አንድ)
ቹቹ አለባቸው
እንደአንድ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታዛቢ በተለይም ደግሞ እንደአማራ የትህነግን ውሎና አዳር ለመከታተል ጥረት ባደረኩ ቁጥር ሁሌም ግርምትን የሚጭርብኝ ብልጣብልጥ አካሄዱ ነው፡፡ አቻነትን የማይቀበልና የብልጫ ድርሻ ልውሰድ ባይ በመሆኑ የፖለቲካ አጋርነትና ትብብር ታሪኩ በክፋት እንጅ በበጎ የሚነሳ አይደለም፡፡ ይህ ከደደቢት በረሃ እስከ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት፤ ከመቀሌ ግዞት እስከ አሸባሪነት ዘመኑ የታየና በመታየት ላይ ያለ እውነታ ነው፡፡
ጦረኛ ተፈጥሮ ከበላይነት እና ቀዳሚነት (እኔነት-ኢጎ) የተጠናወተው ትህነግ በጫካ ዘመኑ
በአጋርነትና በትብብር እንስራ ብሎ የጠራቸውን ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ (ግገሓት) አመራሮች በሌሊት እስከማረድ የደረሰ አረመኔ ቡድን ነው፡፡
ከጀብሓ፣ ከሻቢያ ጋር ያደረጋቸው የትግል አጋርነቶችም ቢሆን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ መጨረሻቸው አላማረም፡፡ የበላይነት ፍላጎቱንና የብቻ ሥልጣን ጠቅላይነቱን ለማረጋገጥ 80 ከመቶ የትግራይ ተወላጆች የሞሉት ‹ኢዲዮ› ጋር ያደረገው ተደጋጋሚ ጦርነት የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች የእርስ በርስ እልቂት አሳዛኝ ትዕይንት ሆኖ በታሪኩ ሲጠቀስ ይኖራል፡፡ ድርጅቱ የበላይነቱን በማያስረግጥ የትግል መድረክ ላይ የመገኘት ዝንባሌ እንኳ የሌለው ‹እኔ ብቻ› ቀዳሚ እና የበላይ ልሁን ባይ ነው፡፡
በ1983 ሰኔ ወር ላይ ለይስሙላ ባዘጋጀው የሽግግር ምክር ቤት፣ በአንድ ዓመት ልዩነት የነበሩትን ድርጅቶች በማባረር የበላይነትና ቀዳሚነቱን የሚያስጠብቁ አጋሮችን በራሱ እንደፈጠረ የሚታወስ ነው። ኦነግ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ)፣ የአፋር ነፃነት ግንባር (አነግ)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን)፣ የምዕራብ ሶማሌ ነፃነት ግንባር (ምሶነግ)፣ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን)፣ የኦሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦሕዴግ)፣ የኦሮሞ እስላማዊ ነፃነት ግንባር (ኦእነግ)፣… ወዘተ እንደትህነግ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች ቢሆኑም (የጃራ አባ ገዳን ፓርቲ በልዩነት ይዘን) የፓርቲዎቹ አጋርነት ከጅምሩ የበላይነቱን የማያስጠብቅ በመሆኑ የሽግግሩ አብሮነት በአሳዳጅ ተሳዳጅ ድራማ እንዲፈጸም አድርጓል፡፡
ከጅምሩ 19 የሚደርሱ የድርጅት ስም የተሰጣቸውን ታጣቂዎችን ከያሉበት አሰባስቦ ‹የኢትዮጵያ ህልውና አጣብቂ ውስጥ ገብቷል› ብሎ ምዕራባውያንን ለማሳመን ሰርቶበታል፡፡ ትሕነግ ከያዛቸው አላማዎች አኳያ፣ አገር ለመያዝ የሚያበቃ ስዕል እና ተቀባይነት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፣ ስትራቴጂካዊ ግንባር እና ታክቲካዊ አጋር ለመፍጠር አበክሮ ሲሰራ ቢቆይም፣ እርሱ የኢትዮጵያ አዳኝና ወኪል እንዳይሆን እንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን ኃይሎች፣ የሽግግር ም/ቤት ምስረታው የፊርማ ቀለሙ ሰይለቅ ከአዲስ አበባ አሳድዷቸዋል፡፡
ትላንት አጋሬ ናቸው ያላቸውን የፖለቲካ ኃይሎች በትረ-ሥልጣኑ ላይ ራሱን ካደላደለ በኋላ፣ በጦርነት ሲዋጋቸውና ሲያስጨንቃቸው ኑሯል፡፡ በተለየ ሁኔታ ከኦነግ እና ኦብነግ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የኦሮሞና የሱማሊ ወጣቶችን በጥይት አረር ለብልቧቸዋል፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የአገሪቱን ወጣቶችና የተማረውን የህብረተሰብ ክፍል ሲያሳድድና ሲያስገድል ኖሮ በሽብርተኛነት አስፈረጇቸዋል።
በመጋቢት 2010 ሥልጣን ከእጁ ሲወጣ ‹አጋር ሁኑኝ እያለ› ከወደመቀሌ ሲያላዝን ከረመ፡፡ ከ1984/85 ጀምሮ ለመግደል ሲያሳድዳቸው የነበሩትን የፖለቲካ ኀይሎች 2011 ላይ ‹‹የፌዴራሊስት ኃይሎች›› በሚል የዳቦ ስም ለአጋርነት ለመለመን እንደትህነግ ሞራል አልባ መሆንን ይጠይቅ ነበር፡፡ በዚህ ሳያበቃ የለየለት አሸባሪ ከሆነ በኋላ ከጦር ውረራው ጎን ለጎን ፀረ-አማራና ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖችን በአሜሪካ ድጋፍ ሰጭነት አደራጅቶ የአጋርነት ውድቀት ታሪኩን ሊደግመው ተረኛ ተጋላቢ ፈረሶችን አዘጋጀቷል፡፡ አፋርን እየወጋ የአፋር አጋር፣ አገውን እያሳደደ የአገው አጋር፣… ወዘተ የሚፈልግ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን፣ ይሉኝታም ሆነ ነውር የማያውቅ ስለመሆኑ እያሳየን ነው፡፡
በርግጥ ትህነግ ታሪክን በመድገም ደረጃ ይሳካለት ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት በዚህ በክፍል እንድ ጽሁፍ ተረኛ ተጋላቢ ፈረሶቹን የፖለቲካ ቁመናና ማህበራዊ መሰረት እንፈትሻለን፡፡
1. የጥምረቱ አካላት ማንነትና ያላቸው ማህበራዊ መሰረት፡-
በትላንትናው ዕለት በ Washington press club በአሜሪካ አርክቴክትነት፣ በትህነግ አጋፋሪነት የተመሰረተው ‹‹ጥምረት›› የሚከተለውን ዝርዝር ይዟል፡- ትህነግ፣ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (OLA-ኦነግ ሸኔ)፣ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲ አንድነት ግንባር፣ የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ የጋምቤላ ሕዝቦች የነፃነት ጦር፣ ሶማሊ ስቴት ሬሲስታንስ (Somali state resistance) ናቸው፡፡
ከእነዚህ ስብስቦች ውስጥ በትናንቱ መድረክ ከታዩት ከትህነጉ ብርሃነ ክርስቶስ ውጭ አንዳቸውም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በአደባባይ ተሳትፎ ሲያደርጉ ያልታዩ ፀጉረ-ልውጦች ናቸው፡፡ ፀጉረ-ልውጥ ስል አዲስ ተጋላቢ ጎፈር ፈረሶች ናቸው ማለቴ ነው፡፡
ስብስቡን አጠር አድርገን ስንመለከተው፡-
ትህነግ በፍፁም ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የወደቀ አጥፍቶ መጥፋትን ግቡ ያደረገ ኃይል ነው፡፡ የገዛ ሕዝቡን ጭዳ ማድረግን እንደትግል ግብ የቆጠረ ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ የገባ በደም የሰከረ መሆኑን በተግባር በማስመስከር ላይ ነው፡፡
ትልቁን የኦሮሞ ሕዝብ በማሳነስ የሚታወቀው ኦነግ ራሱን እንደአሜባ እያራባ ለአጠራር ቢያስቸግረንም፣ የአሁኑ ተረኛ የትህነግ አጃቢ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (OLA-ኦነግ ሸኔ) ሁኗል። ስብስቡ የአብዛኛዉን የኦሮሞ ህዝብ አመኔታ ያገኘ አይደለም ፡፡ እስካሁን ባለው ታሪኩ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ንጹሃን አማራዎችን አልፎ አልፎም የኦሮሞ ተወላጆችን ከመግደል ውጭ በወታደራዊ ኦፕሬሽን ከተማ ሲቆጣጠር አልታየም፡፡ ይሄም ሆኖ ዛሬም ትላንት ካሳደደዉ ትህነግ ጋር ጋብቻ ፈፅሟል።
የአፋር ስም የያዘው ‹‹ፓርቲ›› ስሙን ያወጣለት ራሱ ትህነግ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በስሙ መካከል ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› የሚል ይገኝበታል፡፡ ያም ሆነ ይህ ዲያቆን ዳንዔል ክብረት እንዳለው ኢትዮጵያ አፋርን መሆን የሚገባት ጊዜ ላይ በመሆኗ፣ አፋር የአሸባሪ ወኪል በስሙ እንዲጠራበት አይፈቅድም፡፡ በዚህ የህልውና ጦርነት የድል አብሪ ሁነው የተገኙት አፋሮች ናቸው፡፡ እንደኤርታሌ የማይደፈሩ ስለመሆናቸው ራሱ ትህነግ የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡
የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ የሚባለው ጉድ ፍጥረት ደግሞ ከኤርትራ እስከ መተከል የመጣ የሄደው ኃይል መጠቀሚያ ሁኖ ቆይቷል፡፡ አሜሪካን ሀገር አንዱን ስደተኛ ስብስቡ ውስጥ ጎተትው አስገብተውት ታይቷል፡፡
የቅማንትና የአገው ወኪል ነን ያሉ ነጠላ ግለሰቦችም ቢሆን የሕዝብ ሳይሆን የትህነግ አጀንዳ ተሸካሚ ስለመሆናቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በተግባር አሳይተዋል፡፡ የአገውም ሆነ የቅማንት ሕዝብ በትህነግ ሲጠቃ የኖረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በሁለንተናዊ አብሮነቱ ከወንድሙ የአማራ ሕዝብ ጋር ዕጣ ፈንታው የተቆራኘ ነው፡፡ በመሆኑም ከትህነግ ጋር ያበሩ ሁሉ ደመኛ ጠላቶቹ ናቸው፡፡
10ኛው የኢትዮጵያ ክልል ሁኖ የተመዘገበው ሲዳማ በህልውና ዘመቻው ቁልፍ ባለድርሻ ሁኖ ታይቷል፡፡ ትህነግን ለመደምሰስ የሰው ኃይል ከማዋጣት እስከ ሀብት ማሰባሰብ ድረስ የሀገረ-መንግሥቱ አለኝታ ሁኖ ተግንቷል፡፡ ነውር የማያውቀው ትህነግ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የሚል የዲያስፖራ አክቲቪስቶችን ይዞ በ Washington press club ትራጆ-ኮሜዲ ትያትር አሳይቶናል፡፡ የሲዳማን ሕዝብ ግን ራሱን በራሱ ለማስተዳደር በታገለበት ወቅት ግንቦት 16/1994 ሎቄ ላይ በትህነግ መሪነት የተፈጸመበትን ጭፍጨፋ ያውቃል፡፡ የሎቄ ሰማዕታት የሚፋረዱት ስብስብ በሲዳማ ሕዝብ ልብ ውስጥ ቦታ የሚኖረው አይመስልም፡፡
በትላንቱ ተረኛ የተጋላቢ ፈረሶች ስብስብ ሌላኛው ገራሚ ትዕይንት የጋምቤላ ሕዝቦች የነፃነት ጦር የሚል ስያሜ የያዘው ነው፡፡ በመድረኩ ንግግር ሲያደርግ ‹በጋምቤላ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል›› ሲል ተናግሯል፡፡ አዎ እውነት ነው ጋምቤላ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ ፈጻሚውም ትህነግ ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ ትህነግ በ1996 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል በአንድ ኦፕሬሽን ከአራት መቶ በላይ የአኝዋክ ተወላጆችን በጅምላ ሲጨፈጭፍ እና በሺህዎች ሲያሰር፣ አሜሪካ ምንም እንደማትጨነቅ በዝምታ አስመስክራለች። ዛሬ ደግሞ ገዳይና ሟችን ከያሉበት አገናኝታ ለግልቢያ እያመቻቸች ነው፡፡
የትህነግ ሰምንተኛው ፈረስ ለስሙም እንግዳ የሆነው ሶማሊ ስቴት ሬሲስታንስ (Somali state resistance) ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ሙሀመድ ኡጋስ በሚባል የታክሲ ሹፌር የተወከለው ይህ ጉድ ፍጥረት ለስሙ የኮንፌዴሬሽን አቀንቃኝ ቢሆንም መዳረሻ ፍላጎቱ (ቢያስን በምናብ) የሲያድባሬ ቅዥት ‹ታላቋ ሶማሊያ› ነች፡፡ ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሱማሌ አልፎ ጅቡቲንና ሁለቱን (ሶማሊላንድና ፖንትላንድ) ራስ ገዝ አስተዳደሮችን የሚያስቆጣ ብቻ ሳይሆን ጦር የሚያማዝዝ አጀንዳ ነው፡፡ የሞቃዲሾው መንግሥትም ቢሆን ውስጣዊ ፈተናዎቹን ማለፍና ቀጣነዊ ህብረት እንጅ ለዚህ መሰሉ ቅዥት ቦታ ያለው አይመስለኝም፡፡ Somali state resistance የሙስጠፌን አስተዳደር የሚቃወም ብቻ ሳይሆን የሚሻገር ፍላጎት ያለው እንደሚሆን መሰማቱ የተደገሰውን ጥፋት ያሳያል፡፡
ትህነግ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ፣ በኦብነግ ስም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላ ሲጨፈጭፍ እና ሲያስር አሜሪካ ምንም እንደማትጨነቅ የጅምላ ግድያዎቹን በዝምታ በማለፍ አስመስክራለች። ዛሬ ድግሞ የቀጠናው makers and breakers ሁና ለመቀጠል አራጅና ታራጅን በአንድ ለማሰለፍ ላይ ታች እያለች ነው፡፡
በአጠቃላይ ትህነግ Washington press club ውስጥ በአሜሪካ አመቻማችነት ሊያሳየን የሞከረው ትዕይንት በጥንቃቄ ካልተያዘ በንቀት ብቻ ማለፉ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡ ‹የተናቀ ምን…› እንዲሉ ሁኔታዎች በእንጭጩ እንዲቀጩ ካልተደረገ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃ ቀንድም አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በጉዳዩ ላይ አሜሪካ እና ጥቂት ግን ደግሞ የማይናቁ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት እጃቸውን ያስገቡበት ጉዳይ ነውና፡፡
የዲሞክራቶቹ ነገር…
ትህነግ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሲያወጅ፤ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ሲጨፈጭፍ ዲሞክራቶቹ ገና ከመመረጣቸው፣ በባይደን ቡራኬ፣ በሱዛን ራይስ አርክቴክትነት
በነ ብላይኬን ፊት አውራሪነት፣ በጀፍሪ ፊልት ማን እግረኝነት፣ በአምባሳደር ጌታ ፒቲ መረጃ አቀባባይነት “ትግራይ ላይ እልቂት ታውጇል!” እያሉ መጮህ ጀመሩ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ዓለማቀፍ የምርመራ ሪፖርት ይፋ ሲደረግ በትግራይ ጀኖሳይድ እንዳልተፈጸመ አረጋገጠ፡፡ በርግጥ ይህ ሪፖርት የራሱ ፍላጎቶች ቢኖሩትም፣ አሜሪካኖቹና የምዕራቡ ሚዲያ ኢትዮጵያን ለመወንጀል ሲጓዙበት የነበረውን የተሳሳተ መንገድ ያጋለጠ ሁኗል፡፡
ብሌንኬን እና ሱዛን ራይስ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር “ድርድር” እንዲደረግ ሲያስፋራሩ መቆየታቸው አልሳካ ቢል ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እስከመጣል ደርሰዋል፡፡ እስከ 2025 ድረስ ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚ ከሆንበት African Growth and Opportunity Act (AGOA) ሰርዘውናል፡፡ ይህ በትንሹ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ከሥራ የሚያሰናብት በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት ቅይጥ (hybrid warfare) ስለመሆኑ፣ በጦርነቱ ውስጥ የአሜሪካ እጅ እየረዘመ ስለመምጣቱ አመላካች ነው፡፡
ከአሸባሪና ወራሪ ኃይል ጋር ተደራደሩ የሚሉት አሜሪካኖች ዛሬ ደግሞ ይባሱኑ የ1983ቱን ሁኔታ የሚያስታውስ ‹‹የሽግግር ድልደላ›› ላይ ገብታለች፡፡ ነገሩ እኔ ያቀረብኩላችሁን አስገዳጅነት ካልተቀበላችሁ የሚል ማስፈራሪያ መሆኑ ነው፡፡ ይህን ነው “የአሜሪካ ዲፕሎክርሲ” ማለት። የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ አጭበርባሪነት ከግብዝነታቸው የሚመነጭ በሽታቸው ስለመሆኑ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ካሪቢያን እና አፍሪቃ ድረስ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ታይቷል፡፡ ከሰሞኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ (የኢትዮጵያ ጉዳይ ተከታታይ የተደረገው) ጀፍሪ ፊልት ማን ያመጣው ወያኔያዊ አጀንዳ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት በማጣቱ አሜሪካ ዜጎቿ ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ላይ ነች፡፡ ይህ ጥሪ የተላለፈው ከፊልት ማን የመልስ ጉዞ ጋር መሆኑ ማስጠንቀቂያው ኢትዮጵያን በሌላው ዓለም የማሳጣትና ሽብር ውስጥ የመክተት ስልት መሆኑ ነው፡፡ መቼውንም ቢሆን ከአሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ጋር ድርድር የማይታሰብ ነገር ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳያችን በራሳችን መንገድ እንወጣዋለን። ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የማይገረሰስ ልዖላዊነት ያላት ሀገር ነች። ምንም እንኳ የቁስ ደሀ ብንሆንም ክብራችን አሳልፈን አንሰጥም። ነጻ ሀገር ነጻ ሕዝብ ነን!!
(ጽሑፉ ይቀጥላል… በቀጣይ የጥምረቱ ዓላማ/ግብ ምንድን ነው? የጥምረቱ ግብ የመሳካት ዕድሉ ምን ያክል ነው? ይሄን ሴራ በማክሸፍ ከኢትዮጵያዊያን ምን ይጠበቃል? በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እይታየን አጋራለሁ)