የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ለአገዛዞች እንግዳ ጠባይ አይደለም
ከይኄይስ እውነቱ
አንድ ዓመት ያደረገውና ከፍተኛ እልቂት፣ ሰብአዊ ቀውስና አገራዊ ጥፋት ያደረሰው ጦርነት አሁን የሚገኝበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰበት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ዋናውን መዘዝን እናውጣ ቢባል ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ መንግሥት የሌላት መሆኑ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አገሮች በአገራዊ ሰላምና ጸጥታ መታወክ ጉዳይም (ከውጭ ከመጣ ኃይል ጋር የሚደረግ ጦርነት፣ የርስ በርስ ጦርነት፣ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ፣ወዘተ.) ሆነ በተፈጥሮ አደጋ (መሬት መንቀጥቀጥ፣ ሰደድ እሳት፣ በከፍተኛ ነፋስ ኃይል የሚፈጠር የባሕር ንውጽውጽታና የሚያስከትለው የውኃ መጥለቅለቅ ወዘተ.) ከወትሮው ወይም መደበኛ ሁናቴ ለየት ያለ ህልውናን የሚፈታተን ችግርና ተግዳሮት ሲገጥማቸውና ይህንንም አደጋ በመደበኛው የሕግ ሥርዓት፣ መዋቅርና አደረጃጀት እንዲሁም አቅም ችግሩን መቀልበስ የማይቻል ሲሆን እንደ ሁናቴው በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይም አደጋው በሚመለከተው አካባቢ ብቻ የጊዜ ገደብ ተበጅቶለት (አደጋው/ችግሩ እስኪወገድ ድረስ) ለዜጎች ደኅንነትና ጥበቃ ሲባል በመንግሥት ተግባራዊ የሚደረግ ከመደበኛው ወጣ ያለ ጊዜያዊና አፋጣኝ ርምጃ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ስሙም እንደሚነግረን በሕግና ሥርዓት የሚመራ እንጂ ሀገር አቀፍ ወይም አካባቢያዊ ሥርዓተ አልበኝነት ማስፈኛ ወይም ሽብርን ለመፈጸም ወይም ሊያጠቁ የሚፈልጉትን የኅብረተሰብ ክፍል መጉጃ ወይም የአገዛዞችን ሥልጣን ለመታደግ ወይም የሕዝብን መከራ ለማራዘም የሚደረግ አፍራሽ ተልእኮ ማስፈጸሚያ መሣሪያ አይደለም፡፡ ሕዝብን ማስፈራሪያና ማሸበሪያም አይደለም፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን አገዛዞች በተለይም በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም የሚገኙ ጨካኝ አምባገነኖች በተደጋጋሚ ለተጠቀሱት አፍራሽ ዓላማዎች መሣሪያ በማድረግ የሚገዙትን ሕዝብ ማሰቃያ እና በጉልበት የሠለጠኑበትን አገር ማመሳቀያ ሲያደርጉት ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ እቅጩን ለመናገር በአገዛዞች ሥር የሚኖር ሕዝብና አገር መደበኛ ሕይወትም ከአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አኗኗር የተለየ አይደለም፡፡ አስቀድሞም የሕግ የበላይነት ባለመኖሩ ዜጎችን በዘፈቀደ መግደል፣ ማሰር፣ ማሰቃየት፣ ማፈናቀል፣ ማሳደድ፣ ሰው ሠራሽ ረሃብና ጦርነት በመፍጠር ማንበርከክ ወዘተ. ዓይነተኛ መገለጫቸው ነው፡፡ የአእምሮና ሕሊና ቢስነታቸው ልዩ መገለጫ ደግሞ ሁሌም ከፈጠሩት ችግርና ምስቅልቅል ለመጠቀም/ለማትረፍ የሚሄዱበት ርቀት አስደንጋጭ ነው፡፡
ኢትዮጵያ አገራችን ወደገጠማት ፈተና ስንመጣ የኦሕዴድ አገዛዝ ባንድ በኩል (በዚህ ስብስብ ውስጥ ለአገዛዙ ያደሩ ዘረኛ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሙሉ ይጠቃለላሉ)፣ ኢትዮጵያን እንደ አገር ባጠቃላይ የአማራን ማኅበረሰብ እንደ ሕዝብ በተለይ ለማጥፋት የሚንቀሳቀሰው ደመኛ ጠላት ወያኔ/ሕወሓት በሌላ በኩል ስናያቸው መሠረታዊ የዓላማ ልዩነት የላቸውም፡፡ ወያኔ ጦርነት ዓውጆ አገራዊ ሽብር በመፍጠር፤ አገዛዙ ደግሞ ባሰማራቸው እና ሕጋዊና መዋቅራዊ ከለላ በሰጣቸው ኦነጋዊ የሽብር ኃይሎች አገር ከማፍረስ በተጨማሪ የአማራውን ሕዝብ የገና ዳቦ አድርገውት ህልውናውን አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡ ወደድንም ጠላንም እውነታው ይሄ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ለአገር የጎን ውጋት የሆኑት ጠላቶች ደግሞ በዘመናችን ነቀርሳዊ ደዌ የሆነው በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የአድርባዮች ስብስብ ነው፡፡ በተለይም ፊደል ቆጥሬአለሁ የሚለውና አማራዊ ማንነት አለኝ የሚለው አድርባይ ወገኑን ለማሳረድ ለአገዛዙና ለወያኔ ካራ አቀባይ ሆኗል፡፡
አንድ ዓመት ያደረገውና ከፍተኛ እልቂት፣ ሰብአዊ ቀውስና አገራዊ ጥፋት ያደረሰው ጦርነት አሁን የሚገኝበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰበት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ዋናውን መዘዝን እናውጣ ቢባል ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ መንግሥት የሌላት መሆኑ ነው፡፡ የዚህ ዋና መገለጫው ደግሞ በነፋስ የተዘራ ዶቄት አድርጌዋለሁ ያለውን የጠላት ኃይል ስንቅና ትጥቅ ትቶለት እንዲንሰራራ ከማድረግ ጀምሮ፣ የወገንን ሕዝባዊ ኃይል ስንቅና ትጥቅ አልባ በማድረግ በጠላት በማስፈጀት፣ ድል ሲያስመዘግብ ደጋግሞ እንዲያፈገፍግ ትእዛዛዝ በመስጠት፣ የወገንን ቦታዎች ለጠላት አሳልፎ በመስጠት፣ ወገን በጠላት ፕሮፓጋንዳ እንዲሸበር ከማድረግ በተጨማሪ የአገዛዙም ሜዲያዎች ወገንን በማሳሳት ያልተናነሰ ጥፋት በመፈጸም የተሠራው መቼም ይቅር የማይባል ግዙፍ አሻጥር/ሳቦታዥ ነው፡፡ ባንፃሩም አገዛዙ በአዲስ መልክ አደራጅቼዋለሁ ያለው ‹‹የአገር መከላከያ ኃይል›› ከሳቦታዡና ትርጕም ካለው የጦር መሣሪያ አቅርቦት እጥረት በተጨማሪ በዘር የተደራጀ መሆኑ፣ የመጋቤ ዐሥር አለቅነት ማዕርግ የማይገባቸው በስም ግን ጄኔራል የሚለውን ታላቅ የጦር መኮንንነት ማዕርጋትን በተሸከሙ ብቃት በሌላቸው፣ የአገር ፍቅር በሌላቸውና በጥላቻና በዘረኝነት በሰከሩ የጦር መሪዎች የሚመራ ሠራዊት መሆኑ ሞራሉን የተንኮታኮተ አድርጎታል፡፡ ጠላት ለጥፋት ዓላማው የኔ ነው የሚለውን ማኅበረሰብ ሕፃናትን ሳይቀር አደራጅቶ ሲያሰልፍ (እንደሚታወቀው ባለፉት 30 ዓመታት ወያኔና አሽከሮቹ ዘርን መሠረት አድርገው ያደራጁት ሠራዊት ኢትዮጵያዊ አቋም የሌለው÷ በተለይም አመራሮቹ በዋናነት የወያኔ ትግሬ ሰዎች የሆኑበት÷ እውነቱን ለመናገር በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ ያልበለጸጉ÷ የአገር ፍቅር የሌላቸውና አንዳቸውም ጄኔራል ለሚለው ከፍተኛ የጦር መኮንንነት ማዕርግ የማይበቁ መሆናቸው ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል) ፤ በአገዛዙ በኩል ሕይወቱን በፈቃደኝነት ለመገበር ዝግጁ የሆነውን ሕዝባዊ ኃይል ስንቅና ትጥቅ እንዳያገኝ ማድረጉና ‹‹አፈግፍግ›› የሚለው የዐቢይ ሴራ ከቀጠለና የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁም ድብቅ ዓላማ ይህንን ኃይል በታትኖ ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ከሆነ ባገዛዙና በጠላት ኃይል መካከል የሥልጣን ጉዳይ ካልሆነ ልዩነት ሊኖር አይችልም፡፡ ባስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ የሚቋቋመው ወታደራዊ እዝ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ አለኝ የሚል ከሆነ ሕዝባዊ ኃይሉን ባለበት አደረጃጀት አቅፎ፣ በስንቅና በትጥቅ ደግፎ፣ ብቃትና ልምዱ ያላቸውን የቀደሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የጦር መኮንኖች ጠርቶ አመራር እየሰጠ ወያኔን መቅበር ነው የሚጠበቅበት፡፡
በነገራችን ላይ በየክፍላተ ሀገሩ ወያኔና ወራሹ ኦነጋዊ ኦሕዴድ ‹‹ልዩ ኃይል›› እያሉ ያደረጁት የአገር መከላከያ ሳይሆን የአገዛዞች ደኅንነት አስጠባቂ ኃይል ሙሉ በሙሉ ሕገ ወጥ መሆኑን (በነሱ የማስመሰያ‹ሕገ መንግሥት› እንኳን ሕጋዊ አለመሆኑን) ደጋግመን ብንጮኽም ሰሚ በማጣት ዛሬ አገር-አከል የሆኑት ክፍላተ ሀገሮች ‹ልዩ ኃይል› በሚል ሽፋን አገርን ለማሸበር የራሳቸውን ‹‹የመከላከያ ኃይል›› ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ አገዛዙ ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ ወያኔ ‹ኦሮሚያ› በሚል በፈጠረው ግዛት ብቻ በብዛትም በዘመናዊ መሣሪያም የተደራጀው ሕገ ወጥ ‹ልዩ ኃይል› ወያኔን ለማንበርከክ በቂ ነበር፡፡ ይህ ኃይል ግን ከወያኔ ጋር የዓላማ ልዩነት ስለሌለውና የጋራ ጠላታቸው አማራው በመሆኑ፣ የአመራር÷ የአደረጃጀትና ጥራት ያለው የጦር መሣሪያ ጉድለት ያለውን የ‹አገር መከላከያ ሠራዊት› እንዲያግዝ በዘረኝነት የናወዘውና ስንኩል ሰብእና ከተላበሰው ዐቢይ ፈቃድ አላገኘም፡፡ በዚህ ባለቀ ሰዓት በጦርነቱ ቀጣናዎች ውስጥ የሚገኘው የአማራውም ሆነ ሌላ ሕዝባዊ ኃይል በመደበኛ የጦር አደረጃጀት ውስጥ እንዲገባ የሚጠየቅበት ሰዓት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ‹የአገር መከላከያ ሠራዊት› ከሚባለው ውጭ ያሉት ኃይሎች በሙሉ ሕጋዊ አደረጃጀት የሌላቸው ናቸውና፡፡ በጦርነቱ መጀመሪያ ‹የአገር መከላከያ ኃይሉን› (ያለበቂ ስንቅና ትጥቅ) የታደገውና ጠላትን ያርበደበደው ይህ ሕዝባዊ ኃይል መሆኑን ከሀዲው አገዛዝ የሚዘነጋው አይመስለኝም፡፡ የአገርና የሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት ሰዓት ሕዝባዊ ኃይልንና ሚሊሺያን መጠቀም ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፡፡
ጠላት ወያኔና አማራውን በወለጋና በመተከል የሚጨፈጭፉት ኦነጋዊ አሸባሪ ኃይሎች ከተወገዱ በኋላ የአገር መከላከያ ሠራዊታችንን በብቃትም፣ በጥራትም፣ በብዛትም ማጠናከሩ ከታመነበት (የውጭም ጠላት አለብንና) ‹ልዩ ኃይል› የተባለውንና ሌላም ሕገ ወጥ የሠራዊት አደረጃጀት በሙሉ በመከላከያ ሥር በማድረግ ከዘር በፀዳ ሁናቴ ኢትዮጵያዊ አቋም ኖሮት እንደገና ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላለብን ዘመቻ የሕዝባዊ ኃይሉን አደረጃጀት የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁን የሐሰት ምክንያት (pretext) በማድረግ የሚፈጸም ቀጣይ ሳቦታዥ ካለ ለአገዛዙና ለአሸከሮቹ ወዮላቸው፡፡ ለጊዜው የሕዝብ በተለይም የአማራው ሕዝብ ሰቈቃ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ፍጻሜውን ግን (በሕይወት ከቈየን) አብረን እናየዋለን፡፡ ይህ ጦርነት የአገር ህልውናን ብቻ ሳይሆን ቀጣይ የኃይል አሰላለፍን (power dynamics) ሊወስን የሚችልበት ገጽታ ያለው ይመስለኛል፡፡
በእኔ እምነት በአሁኑ ጊዜ ሕዝብን አደራጅቶ ኢትዮጵያን የሚታደግ ኢትዮጵያዊ ኃይል ያለ አይመስለኝም፡፡ ለገዛ ድብቅ ዓላማውም ይናገረው የኦነጉ አሮጌ ትርጕም ያለው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት የለም ያለውን /አገዛዙ እንዳይኖር በማድረጉና ይህንኑም በማረጋገጡ/ እስማማበታለሁ፡፡ ብዙ የተበላሸ ነገር ቢኖርም በሕዝብ ግን ተስፋ አልቈርጥም፡፡ የሚያደራጀው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ያገኘ ጊዜ ታሪክ ሠርቶ ኢትዮጵያን ይታደጋታል፡፡ ምክንያቱም የቀደሙ ደጋግ አባቶች እንደነገሩን ‹ብዙ ሕዝብ እግዚአብሔር› ነውና፡፡
ጸልዩ በእንተ ሰላማ ለብሔረ ኢትዮጵያ፡፡