>

የፀጥታው ምክርቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ አስቸኳይ ውሳኔ አሳለፈ!

የፀጥታው ምክርቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ አስቸኳይ ውሳኔ አሳለፈ!

አሳፍ ሀይሉ

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክርቤት ()UN Security Council) በኢትዮጵያ ጉዳይ ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ባወጣው የአባላቱ የጋራ መግለጫ፦
፠ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ተወግዶ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት በሁሉም ተዋጊ ወገኖች እንዲደረስ፣
፠ በዚህ በኩል የመንግሥታቱ ድርጅት ዋነ ፀሐፊ ለተፋላሚዎች ያቀረቡትን የሠላም ጥሪ በልዩ አድናቆት እንደሚመለከተውና እንደሚደግፍ፣
፠ ጥቃቶችን ለማባባስ የሚደረጉ ከፋፋይና ግጭት ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግሮች እንዲቆሙ፣
፠ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ተጠናክረው ግጭቱ ወዳለባቸው ተጎጂዎች በአስቸኳይ እንዲደርሱ፣
፠ የአፍሪካ ኅብረት ያሳለፈው የተኩስ አቁም ጥሪ እንዲከበር፣ የግጭቱ አድማስ አሻቅቦ የበለጠ ሰብዓዊ ኪሣራ እንዳያደርስና፣ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ ኅብረቱ ተገቢውን ሚና እንዲወጣ ሙሉ ድጋፉን እንደሚሰጥ፣
፠ በናይጄሪያው የቀድሞ መሪ በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የሚመራው የአፍሪካ ኅብረቱ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ተዋጊ ወገኖችን በማደራደር የሚያደርገውን ጥረት በአድናቆት እንደሚመለከተውና ተፋላሚዎች ለጥረቱ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ፣ እንዲሁም
፠ ግጭቱን ለማብረድ የመንግሥታቱ አባል ሀገሮች ሁሉ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነፃነትና የግዛት አንድነት በማክበር የሚከናወኑ መሆናቸውን አባል ሀገሮቹ ሁሉ ያለንን ጠንካራ አቋም እናረጋግጣለን፤
በማለት መግለጫውን ደምድሟል።
– የመረጃው ምንጭ በተባበሩት መንግሥታት የአልጀዚራ ከፍተኛ ዘጋቢ፣ አማንዳ ፕራይስ፣ ኒውዮርክ፣ November 5, 2021.
ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ከላይ በተገለፀው መልኩ ኢትዮጵያውያን ከገባንበት የእርስበርስ ሰቆቃ ለመገላገል የተባበረ ጥረት እያደረጉና፣ የሺህዎችን ነፍስ የቀጠፈውንና፣ ብዙዎችን ለአካል መጉደልና ሰቆቃ የዳረገውን፣ ወደ 4 ሚሊየን የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን መፈናቀል ምክንያት የሆነውን፣ ወደ 400ሺህ የሚሆኑ ወገኖቻችንን በረሀብ ሁኔታ ውስጥ ቀናቸውን እንዲገፉ የዳረገውን ሰቆቃዊ ጭፍጭፍ በቅርበት እየተከታተሉት ይገኛሉ። ለሁሉም የሠላም አማራጮች ብዙ እጆች ተዘርግተዋል።
ይህም ሁሉ የሚደረገው ለኢትዮጵያውያን ቅን ከማሰብና ዜጎቻችንን ብሎም ሀገራችንንና ቀጣናችንን ከከፋ አደጋ ለመጠበቅ ነው። ይህን ተረድተን ኢትዮጵያውያን ከግጭቶች በመራቅና ለጋራ ሀገራዊ ሠላም በመነሳት ለራሳችንና ለልጆቻችን የምትበጀንን የጋራ የሠላም ሀገር ለማቆም የበኩላችንን አስተዋፅኦ እንድናደርግ ዓለም ሁሉ በትኩረት እየተጠባበቀን ይገኛል።
ይህን እጅግ አሳሳቢና ታሪካዊ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝራሱን ከደም አፋሳሾች በማራቅና ለፍትህ፣ ለእኩልነትና፣ ለወገን ትብብር በመሥራት ከዓለመቀፉ ሕብረተሰብ ጎን እንዲቆም ብዙ ወዳጅ ሀገራትና ሕዝቦች፣ እንዲሁም አፍሪካዊና ዓለማቀፋዊ ተቋማት ጥሪያቸውን እያቀረቡልን ነው።
ሠላም፣ መከባበር፣ መቻቻል፣ እና ፍትህ ወዳድነት አይለዩን! ደም አፋሳሾቻችን ለፍርድ ይቀርባሉ። ፈጣሪ ኢትዮጵያን አይተዋትም። ወገን ቀን አለ። ለፍቅር ቀና በል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic