>
5:26 pm - Wednesday September 17, 3152

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን.በመግለጫው የእስረኞች አያያዝና ሁኔታ አሳስቦኛል አለ...!!!

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን.በመግለጫው የእስረኞች አያያዝና ሁኔታ አሳስቦኛል አለ…!!!

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ከተሞች በቁጥጥር ስር በመዋል ላይ የሚገኙ ሰዎች ሁኔታና የአያያዝ ሂደት እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ( አሰመኮ ) ገለፀ።
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋ ጅ ከታወጀ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ሰዎች ከስራ ቦታቸው፣ ከመኖሪያ ቤታቸው እና ከመንገድ ላይ ጭምር በቁጥጥር ስር ውለው በተለያዩ የከተማዋ ፖሊስ ጣቢያዎች ተይዘው እንደሚገኙ ማረጋገጡን ትናንት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራሉ ተብለው ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠሩ ሰዎችን ይዞ የማቆየት ስልጣን ለህግ አስከባሪ አካላት ቢሰጥም እስሩ ማንነት/ብሄርን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚመስል ሁኔታ መከናወኑን ማረጋገጡን፣ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች የቤተሰብ ጥየቃ፣ ልብስ እና ስንቅ ማቀበል መከልከሉ እና እስሩ ህፃናት ልጆች ያሏቸው እናቶች እና አረጋዊያንን ያካተተ መሆኑ በእጅጉ አሳስቦኛ ብሏል።
የህግ አስከባሪ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና መመሪያዎቹን በስራ ላይ ሲያውሉ እና ሲያሰፈፅሙ የህጋዊነት ፣ የጥብቅ አስፈላጊነትና ተመጣጣኝ እንዲሁም ከመድልዎ ነፃ መሆን የሚሉትን የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን ባከበረ መልኩ ሊሆን ይገባል ሲልም አስታውሷል።
በተጨማሪም የህግ አስከባሪ አካላት በማንኛውም ሁኔታ ሊገደቡ የማይችሉ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር፣ ተግባራቶቻቸውም በከፍተኛ የሙያ ስነምግባር በመመራት የማከናወን ኃላፊነት አለባቸው ብሏል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተው የመጀመርያው መግለጫው።
ኢሰመኮ በትለይ አረጋውያን፣ የህፃናት ልጆች እናቶች እንዲሁም የህክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን ጨምሮ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን አያያዝ በተመለከተ ፈጣንና ልዩ የማጣራት አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝባል።
ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገርን ሕልውና እና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በሚል በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውንና ለስድስት ወራት ተፈፃሚ የሚሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጽድቆታል።
ምክር ቤቱ የአዋጁን አፈፃፀም የሚመረምር ፣ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ሰባት አባላት ያሉት መርማሪ ቦርድ አቋቁሟል።
አዋጁን ተንተርሶ ስልጣንን አላግባብ መጠቀም ፣ ዜጎችን ማንገላታት እንዳይኖርም ይሄው መርማሪ ቦርድ ክትትል ያደርጋል ተብሏል።
Filed in: Amharic