>

ፈቅደው የሞቱትን ልትገድሏቸው አትችሉም...!!! (አባይ ነህ ካሴ)

ፈቅደው የሞቱትን ልትገድሏቸው አትችሉም…!!!

አባይ ነህ ካሴ
ፈሺስታዊ ቀይ ስሕተት በቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጸመው ሕወሐት አሁን ይቅር ከማይባልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ብፁዕ አቡነ በርናባስን አፍኖ በመውሰድ የት እንዳደረሳቸው አልታወቀም፡፡ ብፁዕነታቸው ከሕዝባቸው ጋር መከራ መቀበልን ከመረጡት የዘመናችን ስጦታ ከኾኑት አበው አንዱ ናቸው፡፡
ጥቅምት ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. ልናነጋግርዎት እንፈልጋለን ብለው በመኪና ወዳልታወቀ ቦታ ይዘዋቸው ሔደዋል፡፡ እንደወጡ አልተመለሱም፡፡ በሕዝባቸው መካካል ኾነው እዚያው በሰቆጣ መከራውን ችለው በመከራ ያለውን ሕዝብ እያስተባበሩ እያቻቻሉ ያለው ከሌለው እንዲካፈል እያግባቡ አባታዊ ተልእኳቸውን ሲወጡ እንደነበር እዚያው የነበሩ አረጋግጠውልናል፡፡
እኒህን አባት መንካት ተዋሕዶን መንካት ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ በአስቸኳይ ሊያወግዘው ይገባል፡፡ ጉዳዩን ከፖለቲካ ጦርነት ወደ ሃይማኖታዊ ጦርነት ስቦ ለማስገባት የሚደረገው ሒደት እጅግ አስነዋሪ ነው፡፡ ጫፋቸውን መንካት ብዙ ዕዳ ያስከፍላል፡፡
አሁን በተለይም የትግራይ ልጆች የኾናችሁ የተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መኾናችሁን ልታውቁት ይገባል፡፡ የታፈኑት የእናንተም የእኛም የሁላችንም አባት ናቸውና፡፡  ከተዋሕዶነት ይልቅ ዘሩ የበለጠበት ካለ ምርጫው የራሱ ነው፡፡ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ይህ ነገር ጽዩፍ ነውና፡፡
ፈቅደው የሞቱትን ልትገድሏቸው አትችሉም፡፡ እርሳቸው ለዓለም የሞቱ የእግዚአብሔር ሀገር ሕያው ናቸው፡፡ ስቃይ ታጸኑባቸው ይኾናል እንጅ አትገድሏቸውም፡፡ ታሪካዊም፣ ሃይማኖታዊም ቀይ ስሕተት ከፈጸማችሁ ዕዳና በደሉ በእናንተ ላይ ይኾናል፡፡
Filed in: Amharic