>

"ሕወሓት የፈራው እየደረሰበት ነው....!!!" (ሙሉቀን ሙጬ)

“ሕወሓት የፈራው እየደረሰበት ነው….!!!”

ሙሉቀን ሙጬ

ይቺን አጭር ሃሳቤን ለመሰንዘር ስነሳ “ሕወሓት የፈራው ደረሰበት”  ብዬ ርእስ ላስይዝ አስቤ ነበር። ይሁን እንጅ ይህ አይነቱ ድምዳሜ ካሁን ቀደም ባደረኩት መዝጊያ ሃሳብ ላይ ያጋጠመኝን ‘በህግ አምላክ’ የሚል ማሳሰቢያ አስታውሶኝ ከፈት አድርጌዋለሁ – “እየደረሰበት ነው” ነው ያልኩት፤ ውስጤ ግን የሚያምነውን ያምናል።
ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን “ኢትዮጵያ ከመፍረስ አደጋ ድናለች” የሚል አውድ ሰንዝሬ ከምወዳቸው ወገኖቼ በኩል ‘አደጋው ገና ነው ሃሳብህ መሬት ላይ ያለውን እውነታ አያንጸባርቅም’ ከሚሉ ትጥቃቸውን ካጠበቁ ወገኖቼ አጋጥሞኝ ከዚያ በኋላ የተከተሉትን ወራቶች እየተመልከትሁ ምላሴን ይዠ ቆይቻለሁ። የእኔ ግምገማ በዚያን ወቅት ሲግመለመል የቆየው ዓለም አቀፍ ፖለቲካ ለይቶለት ኃያላኑ መንግሥታት ከሁለት ሲከፈሉና ኢትዮጵያ ያንዱን ወገን ሽፋን ማግኘቷን ስለተመለከትሁ የመፍረስ አደጋው አልፏል ብዬ ደምድሜ ነበር። በተጨባጭ እየሆነ ለቆየው ሁሉ አሁንም ልክ ነበርሁ የምል እጥፍ የማልል ‘ደረቅ’ ብሆንም በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ግን በኢትዮጵያ ምክንያት አካባቢያዊ ወይም ዓለም አቀፍ ጦርነት ቢጀመር የኢትዮጵያ ህልውና በአሸናፊው ወገን እጅ የመውደቋ እጣ ፈንታ እውን ሊሆን ስለሚችል ህዋሳቴ እስካሁንም ድረስ እየነዘረ ‘አንት ወረኛ ምንድን ነበር ያልከው’ ይለኝ ይሆን እያልኩ እሰጋለሁ።
ለሕወሓት አሳፋሪና ነውረኛ ክስመት ሁኔታዎች ሁሉ እያመለከቱ ነው። ምክንያቶቹ ብዙና ዘርዘር ብለው መቅረብ የሚገባⶨው ቢሆኑም ከአጠቃላይ መገለጫው ተነስተን እንተክዛለን። አጠቃላይ መገለጫው ምንድን ነው ስንል አቅፈውና ደግፈው የልብ ወዳጅ በመምሰል ጨዋታቸውን ይጫወቱበት የነበሩት አሽቃባጮቹ እንደ ሰይጣን አርባ ክንድ በመርቅ ላይ ያሉ መሆኑን እንገነዘባለን። ይህንም ሃቅ ሕወሓት ራሱ በሚገባ የተረዳው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። እንደምናስታውሰው ባለፉት ሳምንታት ካንዴም ሁለቴ ይህን የተጋረጠበት ተወርውሮ የመጣል አደጋ ለመቀልበስ እያማረች በተቀነቀነች መሠሪ መልዕክት ምዕራባዊ ደጋፊዎቹ እንዳይለዩት ለማስፈርራት የማሳጣትና የማጋለጥ ሙከራ አድርጓል። ከዚህም አኳያ የሚለገሳቸውን የሳታላይት አገልግሎት በተመለከተና የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል መፈንቅለ መንግሥት እንዲያካሂድ በእነሱ በኩል ሚና እንዲኖራቸው ቀርቦላቸው የነበርን ምክረ ሃሳብ ይመለከታል። ይሁን እንጅ የፈሩትን አደጋ በማስፈራራት ተከላክለው ያስቀሩት አይመስልም።  እንዴት ለምትሉ መፍሰስ የጀመረውን ምልክት ተመልከቱ፦
– በሁለት አካሎች ሲጣራ የቆየው የሰባዊ መብት ጥሰት በሕወሓት ላይ ሚዛን መቶ ይፋ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አሜሪካን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን አግንቷል፤
– አሜሪካ በኢትዮጵያ እግር ወድቃ መፍትሄ እያፈላለገች ነው፡
– አውሮፓ ኅብረት በሕወሓት ብቃትና መፍትሄነት ጥርጣሬ ፈጥሯል፤ ወደ ኢትዮጵያ ፊቱን እያዞረ ነው፡
–  አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሕወሓትን ሊቀብረው ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍሯል፡
– እስራኤል በግልጽ ለሠራቺው ጥፋት ጸጸቷናን እየገለጠች በቀጣዩ ለኢትዮጵያ ቅርበትና ፍቅር  በድርጊቷ ለመግለጥ እተዘጋጀች ነው፤
– ዓለም አቀፉ መገናኛ እየተሽኮረመመ ነው፤ የጠ/ሚሩ መገናኛ ወኪል በሲ.ኤን.ኤን  ላይ መቅረብና ጥንብ እርኩስነታቸውን በራሳቸው መድረክ ላይ በአደባባይ ለመግለጽ መብቃት የመገናኛውን ዓለም ጨዋታ ለሚያውቅ ሩቅ መንገድ ተሂዷል፤
– ወዘተ..ወዘተ እየተመለከትን ነው፤
ዋናው ነገር ይህ እንዲሆን ምን አበቃው የሚለውና እስከየትስ ሊሄድና ሊዘልቅ ይችላል የሚለው ነው። መጨረሻውን መናገር ይከብዳል- ምናልባትም ጊዜው ላይሆን ይችላል። ነገር ግን አሁን ላለንበት ሁኔታና ለሚታዩት እድገቶች ምክንያቱ ምንድን ነው ለሚለው ጥቂት አቢይ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህም ውስጥ፦
፩ኛ) ከኢትዮጵያ በኩል የታየው አልበገሬነት የጫወታው አቅጣጫ እንዲለወጥ ግድ ማለቱ፡
፪) ኢትዮጵያ (መንግሥት ወይም ሌላ እንዳልል አንዳንዶቻችሁ ጸጉራችሁ ስለሚቆም ነው) የተገፋባት ናዳ ደርምሷት እንዳያልፍ አስተማማኝ ጥግ መያዟ – ጓደኞቿን መምረጧ፤
፫) የአፍሪካ ደጀንነት መስተጋባቱና በዚህ በኩል ጥረት መደረጉ፤
፬) ኢትዮጵያዊያን በአንጸባራቂ አንድነት ሏዓላዊ ሀገራቸውንና ነጻነታቸውን ለመከላከልና ለመጥረበቅ ያሳዩት አልበገሬነት፤
፭)   በኢትዮጵያ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን አካባቢያዊና ዓለም ዓቀፋዊ አደጋ ምዕራቡ ዓለም ከልቡ መገንዘቡ፤
፮) ፖለቲካ አካአቢያዊ ነውና ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ የድምጽ አሰጣጥ ፖለቲካ ላይ የተጫወቱትና ያስመዘገቡት ውጤት በዴሞክራቶች ላይ የፈጠረው ስጋት — ቅደም ተከተላቸውን ሳይጠብቅ ዋና ዋናዎቹ እነዚህ ይመስሉኛል።
Filed in: Amharic