>

የጎሳ ፖለቲካ መጨረሻው አያምርም! (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የጎሳ ፖለቲካ መጨረሻው አያምርም!

 

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

tilahungesses@gmail.com


በቅርቡ ከአንድ በምድረ አውሮፓ ኑሮውን ከመሰረተ ( እንደ ኑሮ ከተቆጠረ ማለቴ ነው፡፡ አደራችሁን ኑሮ ካሉት…….ከሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮ ጋር ለማነጻጸር እንዳታስቡ፣እኔ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ወንድሞች በሀገር ቤት ትዝታ እየተሰቃዩ መሆናቸውን ለማስታወስ ነው ነው እንጂ በኑሮአቸው የጎደለው ትንሽ ነው፡፡  ለማናቸውም ወደ ዛሬው አስተያየቴ ልውሰዳቸወሁ፡፡) ወዳጄ ጋር በስልክ ጨዋታችን መሃል “አንድ ደደብ ሰው ዘረኛ ቢሆንስ?” ብዬ ጠይቄው ሳልጨርስ “ኦ ኦ ኦ ኦ ከአውቶሚክ ቦንብ የበለጠ ጥፋት ያደርሳል…” ያለኝ ዛሬ ትዝ ብሎኝ ነው በዚህ በብርዳማው ጥቅምት ወር ሃሳቤን ላካፍላችሁ የፈለኩት፡፡

ወቅቱ የአንድ ምዕራፍ ማለቂያና የሚቀጥለው መጀመርያ ቀን ባይሆንም፣ጥቅምት ወር ሁለተኛው ወር በመሆኑ ለመታረም ግዜ ያለ ይመስለኛል፡፡  አውቀን ለመታረም ዝግጁ ከሆን ማለት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ስለዘረኝነት የታዘብኳቸውን ባጭሩ ላካፍላችሁ ስወስን፣ እንደ አስተማሪ የማታውቁትን ላስተምራችሁ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የበኩሌን ነግሬያችሁ ከናንተም ለመማር ነው፡፡ 

ጽሁፉ በአደጋ ወይም በተፈጥሮ ምክንያት የአዕምሮ ዘገምተኞችንና ህሙማንን አይመለከትም፡፡ 

በተጨማሪም የተናጠል ጥቃትን ለመከላከል በብሔር ወይ በሌላ ባመቻቸው መንገድ ለመደራጀት የተገደዱትንም ይህ ጽሁፍ አይመለከትም፡፡ በተረፈ ምናልባት ጥቂት የተጠቀምኩባቸው ቃላት ከበድ ካሉ በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ 

በዘልማድ እንደሚባለው፣ መሃይምነት ከስህተት፣ ወይም ከደደብነት ጋር አይገናኝም፡፡ 

ዘመናዊ ትምህርት ያልተማሩም ሆኑ በጣታቸው ይፈርሙ የነበሩ ቀደምት ወላጆቻችን ለዘመናት ሕግና ስርዓትን አስጠብቀው፣ ዳር ድንበራችንን አስከብረው አስተላልፈውልናል፡፡

መሃይሙም (የአቦጊዳ ሽፍታው) ሆነ ቀለም የቆጠረው (ፊድል ቆጣሪው) ሁለቱም ብልህና ብሩህ ካልሆኑ ደደብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ትምህርት ቤት ስለተሄደ ብቻ ከድድብና ማምለጥ አይቻለም፡፡ ድድብና ሰዎች ከነሱ ውጪ ያለውን ክስተት የሚገነዘቡበት መንገድ እና ሳያመዛዝኑ ሕይወታቸውን ለመምራት ወስነው የሚወስዱት ተግባርንና ተከትሎ የሚከሰተውን ውጤትን ያካትታል፡፡ 

ሰዎች እንደመሆናችን በሕይወት ዘመናችን እየተሳሳትንና ከራሳችንም ሆነ ከኛ ውጭ አይተንና ተነግሮን አርመንና ተጸጽተን የምናስተካክለው ስህተት እንጂ ደደብነት አድርጌ አልወስደውም፡፡ ደደብነትን እኔ የማየው ባጭሩ፣ በምንም አይነት መንገድ ስህተትን ለማረም የማይፈልጉና በቋሚነት “የሕይወት መመርያው” አድርጎ ተቀብሎ የሚጓዙትን ነው፡፡ 

እንደዚህ አይነት ስብእና ያላቸው ሰዎች በየምንኖርበት ለማስተዋል ከሞከርን፣ ብዙ ቦታ ለመድረስ ዕድል ያለበት ሀገር እየኖሩ፣ እራሳቸውን ባማሻሻል ጥሩ ቦታ ደርሰው ወገናቸውን ለማገዝ ከሚያጠፉት ጊዜና ጉልበት ይልቅ፣ የሚያስደስታቸው ቡድንና ሰፈር እየቀያየሩ፣ ወሬ በማመላለስ፣ በማጋጨትና በማተራመስ የመርካት ባህሪ ያላቸው ደደቦች ናቸው፡፡

እነዚህ ክፍሎች ስንፍናቸውን መደበቂያ አማራጮች ስላሏቸውና፣ ለጊዜው አስጠግተው የሚጠቀሙባቸውም፣ በረዥሙ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት “ለማወቅ አይፈልጉም፡፡” በተለይ የቴክኒዮሎጂ ውጤት የፈጠረልን የማኅበራዊ ሚድያ፣ ለበጎ ተግባር ብቻ ሳይሆን፣ ለነዚህ አይነት ስብእና ላላቸውም ደደቦች ጭምር ሀገርንና ሕዝብን በጅምላ መሳደቢያና ማዋረጃ ጭምር እያደረጉት፣ ለትላንቱ ጥፋታቸው የሰደቡትን ሕዝብ ቢያንስ ይቅርታ እንኳን ሳይጠቁ ሀገርን እንምራ የሚሉት፣ ከታች ሲጀምሩ የሚያርማቸው በመጥፋቱና መደበቂያ ዋሻ እየቀያየሩ ስለመጡ ነው፡፡ ማህበራዊ ቀውስ ለነዚህ አይነት ሰዎች የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ 

ዘመናዊም ሆነ ባሕላዊ ትምህርት፣ በእርግጥ ነገሮችን ከፋፍሎና ተንትኖ ከብዙ አቅጣጫ ለመገንዘብ እንደሚረዳ ቢታወቅም፣ በተለያየ ምክንያት በልጅነት እድሜ አስተዳደጋቸው ተደናቅፎ ቶሎ መላ ካልተገኘለት ትምህርት ቀርቶ፣ ትምህርት ቤቱንም “ጭንቅላታቸው ላይ ቢገነባ፣” ከመደደብ የሚያቆማቸው ተአምር የለም፡፡ ባጭሩ “ደደብ በሳት ይጫወታል’’፡፡

ታዲያ ወዳጄ የነገረኝን ሳሰላስል፣ እውነትም ደደብነት እና ዘረኝነት ሲዋሃዱ ከአውቶሚክ ቦንብ እንደሚብስ ብዙ እውነታዎችን ማሰብ ይቻላል፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” 

“ፈቅደው ወይም የተሻለ መንገድ መስሏቸው ደደብ የሚሆኑ” ብዙ እንቅፋት ፈጣሪ ጭንቅላቶች በዓለማችን በመኖራቸው ምክንያት ብቻ፣ የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ሕይወትን አስቸጋሪ ሲያደርጉ፣ ከዚህ በላይ የሚብሰው፣ በነዚህ ደደብ ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ዘረኝነት ሲጨመርበት፣ በሂሮሺማና ናጋሳኪ ተጥሎ በነበርው ቦንብ ካለቁት ሕዝብ በላይ፣ ዘረኝነት በሰው ልጆች ላይ ያስከተለው እልቂትና ጥፋት የበዛና የከፋ መሆኑ ነው፡፡ 

በዚህ እጅግ ፈጣን ተላላፊና በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ መንጋዎችን አስከትሎ ጥፋት ማደርስ የሚችል፣ እስካሁን መድሃኒት ያልተገኘለት ቀሳፊ የዘር በሽታ፣ በብዙ ሀገሮችና ሕዝቦች መሃከል የእርስ በእርስ አውዳሚ ጦርነቶችና ግጭቶች ፈጥሮ፣ ለሰው ልጆች መሞት፣ መሰደድ፣ መፈናቀልና ለንብረት መውደም ትልቅ ምክንያት ሆንዋል፡፡

ይህ ጥንብ የዘረኝነት በሽታ፣ በተለይ ደደብ ጭንቅላት ሲያገኝ፣ ትምህርት፣ ዕምነት፣ እስፖርት፣ ትዳር፣ ጓደኝነት፣ አብሮ አደግነት፣ እድርና የእቁብ ድንበር የማያግደውና፣ የሰውን ልጅ ባንዴ ከሰውነት ደረጃ አውርዶ ወደ የእንሰሳት ባህሪ የሚቀይር በሽታ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አካባቢውን እና ጂኑ እንዳይቀላቀል የሚከላከል እንሰሳ ብቻ ነውና፡፡ 

ዘረኛ ለመሆን ዋናው መሠርቱ ጥላቻና እያደሩ መጥበብ ሲሆን፣ በላዩ ላይ የውሸት ትርክቱ፣ ዘፈኑ፣ ከበሮው፣ ቀረርቶውና ሽለላው ሰዎችን እስከሚበጠሱ አክርሮ ስለሚያነሳሳቸው፣ እንደ አደገኛ የሴክት ስብስብ፣ በጋራ ለማበድ (collective madness) የተመቻቹ ናቸው፡፡ 

ዘረኝነት ባጭሩ አንድን ብሔር መርጦ እንደ ታቦት ማምለክና፣ ከዚያ ውጪ ያሉትን በጠላትነት ፈርጆ እንዲጠፉ እስከመታገል የሚያደርስ ፋሽስታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ 

የዚህ አይነት አክራሪ እንቅስቃሴ መሪዎቻቸው፣ የእንደነዚህ አይነት የደደብ ሰዎችን ጭንቅላት በቀላሉ መጠቀም መቻል፣ ለም መሬትን በነፃ እንደ ማግኘት ነው የሚቆጥሩት፡፡ 

አክራሪ መሪዎቹ፣ ከሚመቻቸው የታሪክ ወገብና ምዕራፍ እየተነሱ ስሜትን ኮርኩረው የፈለጉትን ማሳመን ብቻ ሳይሆን፣ አዕምሮዋቸውን ለመቆጣጠርያ በሚረዳ የፋሽስት ርዕዮት የተካኑ ስለሆኑ፣ የተከታዮቻቸውን ህሊና ሰልበው፣ እንደኮንፒዩተር የፈለጉትን ጭንቅላታቸው ውስጥ መጫንና መደምሰስ ይችላሉ፡፡

ባጭሩ የቡድኑ አባላት፣ በመሪያቸው ትእዛዝ በጭፍን መመራት እንጂ፣ በራሳቸው ማሰብና ማመዛዘን የማይችሉ፣ እንደ ነጭ ወረቀት የሰጧቸውን መቀበልና የነገሯቸውን እንደ የገደል ማሚቶ የሚያስተጋቡ ለመሪዎቻቸው የመገልገያና የጥፋት እቃዎች ናቸው፡፡

ዘረኝነት ውስጥ ምክንያት(ሎጂክ) ስለሌለ፣ ዘረኛ ለመሆን የግድ ለቆሙለት ነገድ በቦታው መወለድ፣ አካባቢውን ማወቅ፣ ካለፉ ትዝታዎች ጋር የሚያያዝ ትስስር አስፈላጊ አይደለም፡፡ በየግል “የተጫኑት” ምክንያትና በምናባቸው ከፈጠሩት ዓለም ጋር ያቀናጁት አዲሱ ትርክት ነው ዋና መሠረታቸው፡፡ አማራ ክልል ተወልዶና ከብሮ የኖረ ትውልደ ኦሮሞ ወይም ከሌላ ብሔር ሶማሌ ሊሆን ይችላል፣ አማርኛ ፈተና ስለወደቀ፣ ወይ ሊያፈቅራት የፈለጋት አማራ እህት እንቢ ስላለችው አማራ ጠል አክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላ ምክንያት ላቅርብ አንድ በኦሮሞ ክልል ተወልዶና ከብሮ የኖረ ትውልደ ትግሬ ወይም ከሌላ ብሔር ጉራጌ ሊሆን ይችላል፡፡ ኦሮምኛ ቋንቋ ፈተና ስለወደቀ ወይ የከነፈላትን ኮረዳ አፍንጫህን ላስ ስላለችው የትግራይ ብሔርተኛ ሊሆን ይችላል፡፡በ1966ቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ካባ ስር የተደበቁ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ እንዲሁም ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ሴራና ሸፍጥ በተቀናበረ የሀሰት ትርክት( ጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ማለቴ ነው፡፡) ምክንያት አይምሮአቸው ተመርዞ አክራሪ ብሔረተኞች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ለአክራሪነታቸው የሚሰጡን ምክንያት ግን ከመሰረታዊ ሃቁ የራቀ፣ ነገር ግን ለዚህ ተግባር የጫኑትን ወይም የፈበረኩትን ታሪክ ነው፡፡

አርሲ ወይም ባሌ፣ ሲዳሞ የአካባቢውን ወተት እየጠጣ ያደገ አማራውም፣ እንደ ኦሮሞው ምክንያት ወይም እራሱ ብቻ በሚያውቀው የተለየ ሁኔታ፣ የኖረበትን ማኅበረሰብ በጅምላ ጠልቶ፣ ኖሮበት ቀርቶ አይቶ የማያውቀውን ለአማራ ማህበረሰብ ተሟጋች አክራሪ የአማራ ብሔርተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላውም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድ የጎጃም ነጭ ጤፍ እና ማር ተመግቦ ያደገ የሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ተወላጅ እንዲያው ደርሶ አማራ ጠል ሊሆን ይቻለዋል፡፡ ዘረኝነት ብዙ ጊዜ በስሜት መነዳት እንጂ ከምክንያት ጋር ትስስር ስለሌለው፣ ሁሉም የሚሰጡት ምክንያት በግል ወይም በቡድን የተጫኑትን ነው፡፡

ይህ ማለት ግን፣ በደል ለሚደርስበት ማህበረሰብ የሚታገልና በደሉን ድምጽ ሆኖ የሚያሰማ ሁሉ አክራሪ ብሔረተኛ ነው ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ዘረኛ ማለት “ከኛ ብሔር ውጪ” የሚሉትን በጅምላና በጠላትነት ፈርጀው የሚንቀሳቀሱትን ያጠቃልላል፡፡ 

“አንዱ አቃፊ፣ ሌላውን ታቃፊ፣ አንዱ የአንድነት ምሶሶ፣ ሌላውን የሳር ክዳን፣ አንዱ የማእዘን ሌላውን የጉልቻ…. ወዘተ፣ እየተባባሉ፣ “የኛ” የሚሉትን፣ ጀግና፣ ቆንጆ፣ ደፋር፣ ተዋጊና ከሌላ እንደሚሻልና ፈጣሪ እራሱ አዳልቶ የተሻለ አድርጎ መርጦ እንደፈጠራቸው፣” አምነው ለማሳመን ሲጥሩ ማየትና መስማት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ የሚጠቅሷቸው ጥሩም ሆኑ ያልሆኑ ነገሮች በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ እንደሚኖሩ መቀበል አይችሉም፡፡ 

የአንዱ አካባቢ ዘረኝነት ከሌላው አካባቢ ጎልቶ አደጋው ጭምር የሚታይ፣ አንዱ ግልጽ ሌላው ስውር ይሁን እንጂ፣ ከዘረኞች ነፃ የሆነ ማሕበረሰብ የትም የለም፡፡ ነገር ግን የዘረኞቹ ዋና መገለጫቸው፣ በጠላትነት የፈረጁት ማኅበረሰብ ውስጥ እንጂ፣ “የኛ” ብለው “በፍቅር መርጠው የወደቁለት” ማህበረሰብ ውስጥ ዘረኝነት የለም ብለው ሁሉም ይከራከራሉ፡፡ ተው በዘር መከፋፈል ለሀገራችን አይጠቅምም ተብለው ሲወቀሱም፣ እራሳቸውን እንደ የሕዝብ ተወካይ በመቁጠር፣ ቆመንለታል የሚሉት ሕዝብ እንደተሰደበ፣ በሕዝብ ውስጥ ተደብቀው አቧራ አስነስተው ሴራ ይጎነጉናሉ፡፡ ጥፋታቸውን የሚነግራቸውን ነጥለው ይረባረቡበታል፡፡ ዘረኞች ሰውን የሚመዝኑት በተግባሩ ሳይሆን፣ በወጣበት ማህበረሰብና በስሙ ነው፡፡ የጽሁፉን መልዕክት ከማንበባቸው በፊት በስሙ አቋም ይይዛሉ፡፡ 

ሕዝብ አንዳንዴ ዘረኞችን ተከትሎ ለጊዜው ቢሳሳትም፣ ሃቁ ሲገባቸው የሚያርማቸው ወይም የሚቀጣቸው ያው ያሳሳቱት ሕዝብ ስለሚሆን፣ አሁንም ዘረኛ ሕዝብ የለም፡፡

ነገር ግን በሁሉም ማህበር ውስጥ፣ በበታችነት እና በትምክህት ስሜት የሚሰቃዩ አሉ፡፡ ብዙዎቹ ይህ የዘረኝነት ችግኝ በውስጣቸው የሚተከለው፣ ገና በለጋ እድሜያቸው፣ እሳት ዳር ቁጭ ብለው ከዘረኛ የቤተሰብ አባል እየሰሙ ያደጉት ተቀብሮ ይኖርና፣ ትልቅ ሆነው ለዚህ ችግኝ ተስማሚ ሁኔታ ሲፈጠር፣ “እኛስ ከማን አንሰን?” በሚል፣ የቁጭት ወሃ ጠጥተውና፣ በበቀል ማዳበሪያ ፋፍተው ባጭር ጊዜ ይራባሉ፡፡ 

ትክክለኛ ግብረ ገብነትን ያካተተ ትምህርት፣ የአንድነት መንፈስ በዳበረበት ቤተሰብ እና አካባቢ በማደግ፣ ወይ በትክክለኛ መንፈሳዊ ዕምነት የሚመሩ፣ ከዚህ ወረርሽኝ ያመልጣሉ፡፡ 

አብዛኛው መንጋ ተከታይ በጉዳዩ አስቦበትና ገብቶት ሳይሆን፣ ያለፈ የሆነውንና ያልሆነው ተቀይጦ የቀረበለትን የታሪክ ቱሻ በማመን፣ ወይም የተረኛው ገዢ መደብ ከወጣበት ማህበረሰብ በመገኘታቸው የሚኩራሩት እና አሸናፊ እያዩ መሃል ዥዋዥዌ የሚጨውቱትን የዋህ ጭፍሮች ያጠቃልላል፡፡ 

ከዚህ ውጪ ያሉት አደገኛ ጥቅም አሳዳጆች፣ ከዚህ አይነት እንቅስቃሴ ጋር ቁርኝት የሚፈጥሩት አምነውበት ሳይሆን ለግል ጥቅም፣ ሲሰርቁና ሲያጭበረብሩ የሚደበቁበት ዋሻ፣ የሚቀኑባቸውን የሚያጠቁላቸው አጋር፣ የበታችነት ስሜታቸውን የሚደብቁበት ማስመሰያ ጭንብል ስለሚያገኙ እና የስልጣን ቅንጥብጣቢ የሚጠብቁትን ያጠቃልላል፡፡

ይህ ወያኔ ይዞብን የመጣው አደገኛ የዘር በሽታ፣ በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ እንደ እሳት የሚፋጅ የዘር ጥላቻ ችግኝ ለ30 ዓመታት ተክሏል፡፡ ይህ በስፋት የተሰራጨው የዘረኝነት ስሜት ለማምከን፣ እረዥም ጊዜ፣ ጉልበትና የመንግስትንም ከፍተኛ ትብብር ይጠይቃል፡፡ 

ለማያውቀው የሌላ ሀገር ሕዝብ ነፃነት ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሕዝባችን፣ ፊልምና መጽሃፍ እያነበበ (ለማዘር ኢንዲያና ዋክት በልጅነት  የእድሜ ዘመኔ በሲኒማ ኢምፓዬር፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ፣አዲስ ከተማ ሲኒማ እና ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ውስጥ ብዙ ገዜ ስቅስቅ ብዬ እንዳለቀስኩ በእዝነ ልቦናዬ እንላቀስኩ አስታውሳለሁ) ሌላውም የያንዬው ኢትዮጵያዊ ወንድሞቼ በተለይም የአዲስ አበባ አራዳዎች፣ አስመራ፣ድሬዳዋ፣ ሀረርና ጅማ ፣የፊልም አፍቃሪያን እናቱ እንደሞተችበት ሲያለቅስ የምናቀው ወገናችን፣ ለየግሉ ብቻ እንዲያስብ፣ እንዲጨካከን፣ እንዳይተማመንና አብሮ እንዳይቆም በረጅሙ ተሰርቶበታል፡፡ ለዘር አስተዳደር ሕጋዊ ሽፋን ሰጥተው ለረዥም ጊዜ፣ ጥላቻን በራዲዮ፣ በቴሌቭዥን፣ በስራ ቦታዎች፣ ከፓርላማ እስከ ገበሬና ቀበሌ ማህበር አዳብረውት በደረሱበት ውጤት ሕዝባችን ፍዳውን እያየ ነው፡፡ በወርሃ መስከረም 2014 ዓ.ም.የተቋቋመው መንግስት ከዚህ ችግር ያወጣን ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች፣ ምኞትና ተስፋዎች፤ የጦፉ ክርክሮች በስፋት ይደመጣሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ ጠቅለል ሲደረጉ…… 

1ኛ. በመስከረም 2014 ሕጋዊ የሆነው አዲስ መንግስት ወያኔ የጫነብን ዘርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌደራል አስተዳደር በቅርብ ጊዜ ውስጥ ያስወግዱልናል ብሎ በተስፋ መጠበቅ ይቻል ይሆን? ግዜ የሚያሳየን ይሆናል፡፡ 

2ኛ -ወያኔ እና ባለፈው ስርዓት ተደራጅተው ከትህነግ ጋር አብረው የጥቅም ተካፋይ ሸሪክ ሆነው ይጠቀሙ የነበሩት፣ የዘር ፖለቲካ ስርዓት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ 

3ኛ -የተወሰኑ ጥገናዊ ለውጦች በማድረግ ቁጥር አንድና ሁለትን ማቻቻል የሚሉም ነው፡፡

በእርግጥ ወቅቱ በመንግስትም ላይም ሆነ በሕዝባችን ላይ ያለው የውስጥና የውጪ ግፊት ሁሉም ስለሚያውቀው፣ “ሲሮጡ የታጠቁት…” አይነት መፍትሄ፣ ሁሉንም ነገር ባንድ ጀንበር ይፈታ ብለን ባንጠይቅም፣ የሕዝብን ይሁንታ ያገኘው በዶክተር አቢይ የሚመራው መንግስት ኢትዮጵያን ለማዳን የመጨረሻ ጊዜና ዕድሉ በእጃቸው ስለሆነ፣ እኛም የሚሰማንን ስጋትና ጥያቄዎች ማስተላለፍ የዜግነት ግዴታችንም ጭምር ነው፡፡ 

ሊገነቡና ሊጠናከሩ የታቀዱት ተቋማትን ጨምሮ፣ ችሎታ ካላቸው የተለያዩ ተፎካካሪዎች ጋር አብሮ ለመስራት የጀመሩት እንቅስቃሴ የሚበረታታ እና ተስፋም የሚሰጥ ነው፡፡ መርኅ-መርኅ-ሃዊ ተፎካካሪ የመንግስት መስታወት መሆኑን ሳይዘነጋ! ከዚህ ባሻግር መሻሻል የሚገባቸው ህጎች በተለይም ህግመንግስቱ የሚሻሻልበት መንገድ መፈለግ ያለበት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመሩት የትምህርት ሚንስቴር ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ የህግ መሻሻል አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ከዓለም አቀፍ ቱጃር ጉልበተኞች፣ እስከ አሁን ተስፋ ያልቆረጡ ትኅነግና አክራሪ ኦነገ ሸኔ ‘ቢችሉ ወደ ስልጣን ለመመለስ ባይችሉ ሀገራችንን ብትንትኗን ለማውጣት፣ የሚችሉትን አጋጣሚ እየተጠቀሙ እስከመቃብራቸው ድረስ እንደሚዋደቁ እራሳቸው እየነገሩን ነው፡፡ 

የብዙዎቻችን ስጋት፣ ወያኔን በጦርነት ብቻ አሶግዶ፣ ለአገዛዝና ሕዝብን ለመከፋፈል እንዲመቻቸው የፈጠሩትን የዘር ፖለቲካ ርዕዮቱን ሳይቀይሩ፣ ከዚህ ስር ከሰደደ የሀገራችን ችግር እንወጣለን ብሎ አዲሱ መንግስት ያምናል ብሎ መጠርጠር እራሱ ያስፈራናል፡፡ 

ምክንያቱም እንደዛ አይነት ግልጽነትና ቁርጠኝነት የሌለው አካሄድ፣ መንግስትን ከሁለት ያጣ ሊያደርግ የሚችልበት አደገኛ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን የመሰለ እድል ዳግም የሚመጣበትም መንገድ ያለ አይመስልም፡፡ አይበለውና አንዴ ከእጅ ካመለጠ ቦኋላ እንደገና እንደ ሀገር እንኳን መቀጠል ብንችል ብዙ ዋጋ ካስከፈለ ቦኋላ ይመስለኛል፡፡

የናዚዮችንና የፋሽስቶችን ርዕዮት ጠጋግኖ ዲሞክራሲያዊ ማድረግ እንደማይቻል ሁሉ፣ የትህነግና የፅንፈኞቹ ኦነጋውያን የፈጠሩት አግላይ የዘር ፖለቲካ፣ በሕዝብ ላይ ተሞክሮ ሀገርን ለጥፋትና ለውድቀት የዳረገ ስለሆነ ከነሰንኮፉ ኮተቱን ነቅሎ ለማስወገድ፣ የአዲሱ መንግስት አጀንዳ ከመጀመርያዎቹ ረድፍ በእቅድ እንደተያዙ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ሕዝብ እና ፈጣሪ ለዚህ ከፍተኛ ሃላፊነት እንድትመረጡ ሲተባበሯችሁ፣ ሀገራችንን ለማዳን ድፍረትንና ዘዴን አጣምራችሁ እንደምትወጡት ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ 

ግልጽና የማያሻማ አብዛኛውን ክፍል ወደ መሃል አምጥቶ ሊያስማማና ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሚያስቀጥል፣ በዜግነትና በችሎታ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ስርዓት የሚጀመርበትን ወቅት ሊሆን እንደሚችል ተስፋችንን እየሰነቅን ፍላጎታችንን ስናሳውቅ፣ በመላው ዓለም ውድቀታችንን አሰፍስፈው እየጠበቁ ያሉትን የሀገራችንን ጠላቶች አንገት አስደፍቶ፣ አንድነታችንን እንደገና ወደነበረበት ተመልሶ፣ ዕርቅና ሠላም ወርዶ፣ እኩልነት እድገትና ብልጽግና በኢትዮጵያችን ለሁሉም እውን እንዲሆን እንመኛለን፡፡ 

ሀሰቱ ስለበዛ እውነቱ ሆነ ዋዛ

ኢትዮጵያ እደዊሃ ሃበእግዛብሔር

 

Filed in: Amharic