>

"ኢትዮጵያ ታበፅሕ እደውያሃ ኃበ እግዚአብሔር" (ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች) ምህረት አበረ

“ኢትዮጵያ ታበፅሕ እደውያሃ ኃበ እግዚአብሔር” (ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች)
ምህረት አበረ

ይህ ከላይ የጠቀስኩት ጥልቅ መልዕክት ምንም እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተቀዳ ቢሆንም ሙሉ የመልዕክቱ ይዘትና ትርጉም በኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ተቀባይነት ያለው ይመስለኛል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አማኝ ነው፤ የእምነት መጽሐፉ ሊለያይ ቢችልም ሁሉም ግን የእምነቱ ‘ወጋግራ’ (ምሰሶ) እግዚአብሔር ነው። በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የሚጠቀሱ ጥልቅ ሃይማኖታዊ መልዕክቶ ሁሉንም እንደሚመለከቱ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱሱም እንዲሁ ነው።
በቅርቡ አገር ውስጥ ያልች አንዲት እህት በጣም ዐይን ገላጭ የሆነ ሃሳብ አቅርባለች። ይኸውም ይህን ከላይ የጠቀስኩት የሕዝባችንን ሥነ ልቦና የሚገዛና ጽናትን የሚያጎናጽፍ  መልዕክት በኢትዮጵያ ብር ላይ ይቀመጥ የሚል ነው። በበኩሌ በዚህ ከዓለም ሁሉ ተለይቶ ለእኛ ብቻ የተሰጠን ምድራዊ የተስፋ ቃል በዚህ መንገድ ቢገለጽ በእጅጉ እስማማለሁ። ለዚህም ምክንያቶቼ በጥቂቱ፦
፩ኛ) ሕዝባችንን በስነልቦናዊና መለኮታዊ ዕምነቱ ዳር እስከ ዳር ያተሳሥራል፤
፪ኛ) የላቡ ጭማቂ በሆነውና  በየዕለቱ በእጁ ላይ በሚውለው የብር ኖት ላይ ይህን መንፈሳዊ ቃል አብሮ መስጠት የገንዘባችንን ብርቅነትና ዋጋ (ክብደት) በጣም ከፍ ያደርገዋል፤
፫ኛ) ህልቆ መሳፍርት የሌለው ዓለም አቀፋዊ ድንቅነትንና ክብርን ይፈጥራል፤
፬ኛ) ማንነታችንን ለዓለም ህብረተሰብ ያለማሰለስ እያስታወሰና እያስተማረ ይቀጥላል።
አሁን ያለንበት ሁኔታ የጦርነትና የሃዘን ጊዜ ቢሆንም፤ በመከራችን ውስጥ እያለን እህታችን ያነሳቺው ሃሳብ ለችግራችን መውጫ ቢረዳ እንጅ ስለማይጣረስ ተግባራዊ እንዲሆን ዘንድ ድምጻችንን ብናሰማና ለተግባራዊነቱ ብንዘምት ደስታ ይውጠኛል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥትን እጅ ጠምዝዞ ይህን ተግባራዊ እንዲያደርግ ቢያስችል መሠረቱን አጸና፤ በስብእና ፍጥረቱ በምነቱ ፊት ያለውን ታማኝነትና ክብር አረጋገጠ።
Filed in: Amharic