>

" ሕወሓት ከመሰረቱ በውሸት የተካነ ቡድን ነው...!!!"  የሕወሓት መስራች ግደይ ዘረዓጽዮን

” ሕወሓት ከመሰረቱ በውሸት የተካነ ቡድን ነው…!!!”

የሕወሓት መስራችና አንጋፋው ፖለቲከኛ ኢንጅነር ግደይ ዘረዓጽዮን


ጀማል ታመነ

የሕወሓት መስራችና አንጋፋው ፖለቲከኛ ኢንጅነር ግደይ ዘረዓጽዮን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው ሕወሓት ከመሰረቱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ተወልዶ ያረጀበትን የሐሰት ድራማ እየሰራ ለሚዲያ ፍጆታ የሚያውል ቡድን ነው፤ ከአፈጣጠሩም በውሸት የተካነ ነው፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ጋር የወገኑ የውጭ ኃይሎችም የቡድኑን የሐሰት መረጃዎች ተቀብለው ሲያስተጋቡላቸው እንደቆዩ አውስተው፤ ከእነዚህ የሐሰት መረጃዎች መካከልም በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት እንደተፈጸመ ቡድኑ ሲነዛው የነበረው የሐሰት መረጃ አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጽህፈት ቤት በጣምራ ባወጡት ሪፖርት ሐሰት መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በተለይ የምዕራባውያን አገራት ሊቀበሉትና ሊያምኑት ይችላል ብሎ የሚያስባቸውን ጉዳዮች በሐሰት መረጃዎችን እያመረተ ይሰጣቸዋል፤ እነሱም ይህንንም አምነው ይቀበላሉ ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ከመሰረቱ ይጠቀምበት የነበረውን ውሸት አሁንም ይዞት ቀጥሏል የሚሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ በተለይ በቅርብ ጊዜ በወረራ በገባባቸው የአማራና አፋር ክልሎች ድል ማጣቱን ተከትሎ አደናጋሪ የሐሰት መረጃዎችን እየለቀቀ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ሕዝቡ በሽብር ቡድኑ ተስፋ እንዳይቆርጥና የሽብር ቡድኑ ኃይሎች ሞራል ለመጠበቅ ሲል መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የሽብር ቡድኑ የተሰጠውን የሰላም አማራጮች አሻፈረኝ ብሎ ከማእከላዊ መንግሥቱ ሸሽቶ ወደ መቀሌ መሄዱን የገለጹት ፖለቲከኛው፤ ለሰሜን እዝ የተሾሙ የጦር አዛዦችን ላለመቀበል ያደረገው ጥረት እና በእዙ ላይ የፈጸመው ጥቃት የማይዘነጋ ክህደት ነው ብለዋል።

የሕወሓት የሽብር ቡድን መክት በሚል የትግራይን ሕዝብ በማነሳሳት ከፍተኛ ጦር ማሰልጠኑን አንስተዋል። ይህንንም በተደጋጋሚ በስታዲየም በመገኘት ትርዒት አሳይቷል። ይህንን አዝማማያ አዋጭ አለመሆኑን ምክር ብንለግስም አለመቀበሉን ተናግረዋል።

ሕወሓት ከምስረታው ጀምሮ ያልተለወጠና በዚያው መስመር ብቻ ማለፍ የሚፈልግ ድርጅት ነው ያሉት ኢንጅነር ግደይ፤ በአሁኑ ወቅት የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ከሕፃን እስከ አዋቂ ያሉትን ወደ ጦር ግንባር በማሰለፍ እያጨረሰ ነው። ይህ ድርጊት እጅግ የሚያሳዝን ነው የትግራይ ሕዝብም ቀድሞ ሊረዳው አለመቻሉን አብራርተዋል።

የሽብር ቡድኑ ቀድሞ በሰራው ፕሮፓጋንዳ አሁን ላይ በርካታ የትግራይ ወጣቶች እያለቁ ነው፤ ቡድኑ እየሄደበት ያለው ጉዞ የጥፋት ነው ያሉት ኢንጅነር ግደይ ፤ የሽብር ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር ለማጋጨት የሚያደርገውን ጥረት ሊወገዝ የሚገባው ነው ብለዋል።

 

Filed in: Amharic