>
5:29 pm - Thursday October 11, 6412

"አጥር ላይ ያላችሁ ወዮላችሁ...!!!" (የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ዛቻ ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች) አሳፍ ሀይሉ

አጥር ላይ ያላችሁ ወዮላችሁ…!!!”

(የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ዛቻ ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች)
አሳፍ ሀይሉ

ቆይ ለመሆኑ.. ዲያቆን ዳንኤልን የፕሬስ ድርጅት ቦርድ አባል አድርጎ ማን ሾመው? – ጌታቸው ረዳ ነው?!!
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በወያኔ ዘመን ምን ሲሠራ ነበር? – ገዳማትን እየዞረ ሲበረብር፣ ዓለምን እየዞረ ሲጎበኝ፣ መንፈሳዊና ስሜት አነቃቂ መፅሐፍትን ሲያትም፣ በፈለገው ቦታ የፈጣሪን ገድል ሲሰብክ፣ ፕ/ር መስፍንን ሲያብጠለጥል፣ ሀገረ ስብከት ውስጥ ያሻውን ሲፈልጥ፣ የነበረና በሥርዓቱ ታፍሮና ተከብሮ የኖረ ሰው ነው!
ታዲያ በወያኔዎች የጥቅምና የሥልጣን አጥር ላይ ተንጠላጥሎ ቆይቶ፣ ወደ ኦሮሚፋዎቹ ቤተመንግሥት፣ አጠያያቂ በሆነ የአዲሳባ የምርጫ ውጤት፣ የተቀዳሚ ሙፍቲን እጅ ስሞ ማሩኝ ብሎ፣ ወደተረኞቹ ጎራ የተሸበለለ ሰው… እንዴት አጥር ላይ ተንጠልጥሎ ስለሚጠብቁ ሰዎች አውግዞ ይፅፋል? በምን የሞራል አቅም?
አባባሌ፣ ዝም ቢባልስ? በበሉበት መጮህ አመላችን ሆኖብን ይሆን? ዝም ማለት ሲቻል የራስን ገበና ባደባባይ ሳይጠየቁ እየወጡ መዘባረቅ በእውነት ያሳፍራል!
ለነገሩ በአብይ ምላስ የሚደሰኮሩ ውሸቶችን ሲቸከችክ የሚውል ሰው፣ የደቆነበትን ፈጣሪንና የእውነት መሐላውን ክዶ፣ አስር ዓይነት ቅጥፈት ከገዢው ጋር ተጣብቆ የሚቀባጥር ሐሰተኛ ምስክር፣ ሌላ ምን የተለየ ነገር እንዲናገር ይጠበቅ ኖሯል?
እኔ የሚገርመኝ ግን፣ ይህ ሰው እንዴት ብሎ በጌታቸው ረዳ በኩል ተንጠላጥሎ፣ ከአብይ ተወዳጅቶ፣ የቤተክርስትያንን ቅጥር ዘልሎ፣ እንዴት በቤተመንግሥት አጥር ላይ ፊጥ ብሎ እንደተገኘ ብቻ ነው።
ለነገሩ ትልቁን ትቶ ከልክ በላይ ትንሹ ላይ መስፈርም አይገባም። የአሣ ምኑ ከወደአናቱ እንደሚባለው ነው። የሥርዓቱ ቁንጮዎች ሁሉ ከወያኔ ጋር የቤተመንግሥት አጥር ላይ ተንጠልጥለው ሲበሉና ሲጠጡ የኖሩ የሥርዓቱ አሳሞች መሆናቸውን ድፍን ዓለም ያውቀዋል።
አሁን “ወያኔ-ገዳይ!” እያለ ባልዋለበት የሚፎክረውን ዋናውንስ ቀጣፊ ማን ሾመው? በወያኔ-ኢህአዴግ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራውን ሲበላ፣ እሱ የት ነበር? በምን ዓይነት ምቾትና ሥልጣን ላይ ነበር?
ሌላስ ማነው የወያኔ አጥር ላይ ተንጠላጥሎ ያልበላ? ጄነራል አባዱላ ገመዳ ነው? አህመድ ሺዴ ነው? ሬድዋን ከማል ነው? ወይስ ሽመልስ አብዲሳና ደመቀ መኮንን ናቸው? ማነው በወያኔ አጥር ላይ ዕድሜልኩን ተንጠላጥሎ ጥቅም ሲልስ ያልኖረው ከመሐከላቸው?
ሕዝጆሮና አዕምሮውን ከደፈነ “ቀን እስኪያልፍ የፈለገው ይቀባጥር፣ የፈለገው ይግዛኝ” ነው። የጀርመን ናዚ መሪዎችን ተከትሎ ጆሮውንና ህሊናውን ደፍኖ የተከተለው ሕዝብ፣ ሒትለር ሞቶም፣ በርሊን ፍርስራሿ ወጥታም አናምንም ባዮች ነበሩ። እዬዩም አያዩም። እየሰሙም አይሰሙም።
ራሺየያኖችና አሜሪካኖች ደርሰው ከምድር ውስጥ መጠለያ ጎትተው ሲያወጧቸው የፀረ ማደንዘዣ ኬሚካል መላ አካላቸውን እየረጯቸው ነበር። ምክንያቱም ሒትለር የሆነ ማደንዘዣ ሕዝቡን ካላስነካው በዚያን ተራራ የሚያህል ውሸት እንደበግ አይነዳማ!!
(የበርሊንን ፀረማደንዘዣ መድሃኒት ርጭቱን ለማየት የሚሻ ሰው፦ “Hitler – A Career” የሚለውን በ1977 እ.ኤ.አ. የተሠራ የታወቀ ጥናታዊ ፊልም በቀላሉ ከኢንተርኔት ላይ ፈልጎ አግኝቶ የተቀረፀውን እውነተኛ ቪዲዮ ለታሪክ ጉድ እያለ ማየት ይችላል)።
የሚገርመኝ ከቤተክርስትያን ሰባኪነት ወጥቶ፣ ምንም ብትሆን ትንሽ ፈሪሃ እግዜር ያለው ሰው፣ በአንዴ “መንግሥተ ሠማያት በርባለችና ንስሃ ግቡ!” በማለቻ ዕድሜው፣ እንዴት የቤተመንግሥት አጥር ላይ ቆሞ “አጥር ላይ ያላችሁ ወዮላችሁ!” እያለ ዜጋን ወደሚያሸማቅቅ የቆረበ ፖለቲከኝነት ለመሸጋገር እንዴት እንደሚበቃ ብቻ ነው?
አጅሬው የሆነ የሚያስነካቸው ነገርማ መኖር አለበት! አንዱን የሚያስቀባጥር፣ ሌላውን ጫማውን የሚያስም፣ የሆነማ የሚያስነካቸው የህሊና ማደንዘዣ መኖር አለበት።
“ያዳቆነ ሰይጣን፣ ሳያቀስ አይተውም” አለ ያገሬ ሰው!
ሆሆ! ባይናችን ላይ ፍጥጥ ተብሎ? ራስፑቲንን ካልተካሁ??  ጉድ እኮ ነው! ጊዜ! ጊዜ የማያሳየን ጉድ የለም። ጊዜ ይስጠንና የዚህን ሁሉ መጨረሻ ያሳየን።
“ይህ የናንተ ዘመን፣
ለካስ ከስሮ ኖሯል- የዘመን መናኛ፣
ያጠናፈረው ነው – የመታው መጋኛ!
የደገመው ዳፍንት፣
ከፍ ብሎ አጋሰስ- ዝቅ ብሎጌኛ!”
   ( ዮሃንስ አድማሱ)
ፈጣሪ አምላክ ፈፅሞ ይማረን!
እርሱ አያልቅበትምና!
Filed in: Amharic