>

በጦርነቱ መንስኤ ዜጎች ለከፋ ረሀብና ሞት እየተዳረጉ ነው...!!! D W 

በጦርነቱ መንስኤ ዜጎች ለከፋ ረሀብና ሞት እየተዳረጉ ነው…!!!

D W 

 

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የላሊበላ አካባቢ ነዋሪዎች ለከፋ ርሀብና በሽታ እየተጋለጡና እየሞቱ እንደሆነ ሰሞኑን ከስፋራው የመጡ  ተፈናቃይ አመለከቱ፣ የዓለም ቅርስ የሆኑት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትም ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡
 
የባሕርዳሩ ወኪላችን ያነጋገራቸው ቸኮለ ይርጋ የተባሉ ተፈናቃይ በላሊበላ ያለው ርሀብ፣ እርዛት፣ በሽታና እንግልት እየበረታ በመሄዱ ከረጅም የእግር ጉዞ በኋላ ሰሜን ወሎ ዞን መቄት መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ህወሓት በቁጥጥር ስር ባደረገው የላሊበላ አካባቢ ሰብአዊ ቀውሱ እጅግ በጣም እየሰፋ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ለበሽታና ለእንግልት እየተዳረገ ነው፡፡
ሕወሓት የዓለም ቅርስ ከሆኑት የላሊበላ አቢያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሆኖ ከባድ መሳሪያ ስለሚተኩስ ቅርሱ ለከፋ ጉዳት እየተዳረገ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ተቋም (UNESCO) ሊታደው እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ ከቱሪዝም አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሕይወቱን ይመራ አንደነበር አስታውሰው ያ በመቆሙ ነዋሪው ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ በከፋ ሁኔታ መጋለጡን ተናግረዋል፡፡
*   *    *
UN በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ጦርነቱ እየተባባሰ ባለበት አካባቢዎች የነብስ አድን የሰብአዊ ዕርዳታ የሚውል 40 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታ ገንዘብ ድጋፍ መመደቡን አስታውቋል። 
የUN የርዳታ ሃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ ፥ የገንዘብ ድጋፉ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በጦርነቱ በተጎዱ የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል እና ድርቅ ለተከሰተበት ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል አስቀድሞ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ የተለገሰ መሆኑን  ተናግረዋል።
ነገርግን በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ ለመደገፍ የሚያስፈልገውን የ350 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የሰብአዊ ድጋፍ ተግባራት የ1.3 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ክፍተት እንዳጋጠማቸው ኃላፊው በመግለጫቸው አሳስበዋል።
ግሪፊትስ ፥  ” በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ ቀውሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄዶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሕይወታቸው አደገኛ ጠርዝ ላይ ይገኛሉ ” ብለዋል። በመላ ሀገሪቱ መሰረታዊ ፍላጎቶች እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
ለአስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ የተመደበው ገንዘብ 25 ሚሊዮን ዶላሩ አዲስ ጥሬ ገንዘብ ከUN ማዕከላዊ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ የተገኘ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን የቀረው 15 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ተቀማጭነቱን ሀገር ውስጥ ካደረገ የሰብአዊ ረድኤት ገንዘብ አቅራቢ የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
ገንዘቡ በትግራይ ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በግጭቱ ለተጎዱ ወገኖች ከለላ እና የነብስ አድን ድጋፍ ይውላል ተብሏል።
የገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ በድርቅ በተጎዱት የደቡባዊ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ጨምሮ እንደ ኮሌራ ያሉ የውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ለእንስሳት መኖ አቅርቦትና እንክብካቤ ስራዎች እንደሚውል መገለፁን ዶቼ ቬሌ ሬድዮ ዘግቧል።
Filed in: Amharic