>

የሰሞኑ የደብረፅዮን የሪፍረንደምና የመገንጠል ሐቲት አንድምታዎች!!!! ጌታሁን ገርማሞ

የሰሞኑ የደብረፅዮን የሪፍረንደምና የመገንጠል ሐቲት አንድምታዎች!!!!
ጌታሁን ገርማሞ

   አሁን ሕወሓት ባለችበት ሁኔታ ትግራይን መገንጠል አትችልም። ምክንያቱም ምንም እንኳን  የብሔሮችን ያለገደብ የመገንጠል መብት የሚፈቅድ አንቀፅ 39 በሕገመንግስቱ ቢካተትም አገነጣጠሉ ግን ተናጠላዊ (Unilateral) መሆን አይችልም። ማለትም የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት “Non colonial Unilateral secession”ን አያስተናግድም። መገንጠል የሚቻለው በሕገመንግስቱ ሥር ብቻ ሆኖ ነው። ለኤርትራ መገንጠል ግን ይህ ቅድመ ሁኔታ አልነበረም። ምክንያቱም የኤርትራ የመገንጠል ጥያቄ የተመሠረተው በ”Colonial secession” ላይ ነበር። በወቅቱ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ወክሎ ዕውቅና መስጠቱ እንደ አጋዥ ሁኔታ እንጂ እንደ ቅድመ ሁኔታ መወሰድ የለበትም። የተባበሩት መንግስታት ጥያቄው የቅኝ ግዛት ነው ብሎ ካመነ ያለ ኢትዮጵያም ዕውቅናም ቢሆን መገንጠሉን በሪፍረንደም አረጋግጦ ኤርትራን በሀገርነት መመዝገብን የሚከለክለው ምንም ምክንያት አይኖርም ነበር። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ቀደም ሲልም ከተባበሩት መንግስታት ቻርተርና ከዓለም አቀፍ ሕጎች አንፃር በተደጋጋሚ መፃፌ ይታወሳል…እዚህ ጋ ደፂም በንግግሩ ውስጥ “ዓለም አቀፍ ሕጎች” እያለ ጥቆማ ስለመስጠቱ ልብ ይሏል።
   ትግራይ የመገንጠል ጥያቄን ካነሳች ጥያቄዋ ከኤርትራው ይለያል፤ It will be a quest for non-colonial secession! በእርግጥ በ”Non-Colonial secession” ጥያቄ የተባበሩት መንግስታት የሀገርነት ዕውቅና የሚሰጥባቸው በጣም ውስን ሁኔታዎች አሉ፤ ለምሣሌ እንደ ኮሶቮ በዘር ላይ የተመሠረተ ጅምላ ፍጅት(Genocide) እና ዓይን ያወጣ ጭቆና ከተፈፀመ የሀገርነት ዕውቅና ሊኖር ይችላል። እነሱም ቢሆኑ በየቀኑ  የጄኖሳይድ ዲስኩርን ሲያሰሙ የነበሩት አንድም ለዚሁ ቅድመ ሁኔታ ለማመቻቸት ነበር። ነገር ግን ይህን ዲስኩር አሁን ውኃ በልቶታል፤ የራሱ የተባባሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጄኖሳይድ ሐቲቱ በበቂ ማስረጃ የተደገፈ አይደለም በማለት ፉርሽ አድርጎታል።
    ስለዚህም ተናጠላዊ መገንጠል እንደማይቻል ሕወሓት በሚገባ ተረድታለች ማለት ይቻላል፤ ከቀናት በፊት የተለቀቀው የደብረፅዮን ንግግርም የሚያረጋግጠው ይህን ነው፤ እስከአሁን ድረስ ተናጠላዊ መገንጠልን አከናውኖ በተባበሩት መንግስታት የሀገርነት ዕውቅናን የተጎነፃፈ ሀገር የለም፤ ምናልባትም ከባንግላዴሽ በቀር! ስለዚህም ሕወሓት ዲሲ ላይ የሽግግር መንግስት ዝግጅት ላይ ተፍ ተፍ የምትለው በለስ ከቀናት የኤርትራውን ዓይነት ዘዴ ለመድገም ነው። ያኔ ለኤርትራ ሪፍረንደም  አጋዥ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሕወሓት የተጫወታችውን ሚና ዛሬ ደግሞ ይህንኑ ሚና የሚጫወትላትን ስብስብ መዘጋጀት አለበት። ሕወሓት ሰራሹ የሽግግር መንግስቱ ዋና ዓላማና ተግባሩ ለትግራይ(ለኢትዮጵያ ሳይሆን) መፃኢ ዕጣ ፋንታ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ለዚህም ነው ደፂ በመግለጫው በተደጋጋሚ አዲስ አበባ ከገባን ዓላማችን ኢትዮጵያን ዳግም ማስተዳደርና መግዛት አይደለም የሚለን!
  ታዲያ በሕወሓት ትልም መሠረት ሪፍረንደሙን ቀጥሎ የትግራይ ቀጣዩ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
1. የሪፍረንደሙ ውጤት የትግራይን መገንጠል የሚያመላክት ቢሆን እንኳ ሕወሓት የመደራደር አቅሟን አጎልብታና አዲስአበባ ውስጥ የአሻንጉሊት መንግስት አቋቁማ እንደ በፊቱ “opportunist secessionist” በመሆን በፌዴራል ሥርዓቱ ልትቀጥል ትችላለች…ራሺያ ውስጥ ታታሪስታን ሪፍረንደም አካሂዳ(61% የታታሪስታን ሕዝብ መገንጠልን ደግፎ ነበር) መገንጠል እንደምትችል ለራሺያ ካሳየች በኋላ የድርድር አቅሟን አጎልብታ ከራሺያ ጋር በፌዴራል አወቃቀር ለመቀጠል እንደተስማማችው ማለቴ ነው።
2. ሕወሓት አዲስአበባ አሻንጉሊት መንግስት ካስቀመጠች ለትግራይ ከፌዴራሊዝም አወቃቀር ይልቅ ኮንፌዴሬሽን ምርጫዋ ሊሆን ይችላል።
3. ይህ ካልሆነ የሕወሓት ምርጫ መገንጠል ሊሆን ይችላል።
  ይህ እንግዲህ ሕወሓት እንደ ሕልሟ አዲስ አበባ ከገባች ልትፈፅመው የምትወጥነው አካሄድ ነው። ምናልባት ሕወሓት እዚያው ትግራይ ሆነ አቅሟን አደራጅታ ከቀጠለች ዲፋክቶ መንግስት መሆን ሌላ ምርጫዋ ሊሆን ይችላል። ይህ ዲፋክቶ መንግስት በተወሰኑ ምዕራባውያን ሀገራት(አሜሪካና እንግሊዝ) ዕውቅና ሊሰጠው ይችላል።
   ብዙዎች ትግራይ ከተገነጠለች ካላት ጂኦ-ፖለቲካዊ ማነቆዎች የተነሳ ለብቻዋ ደሴት ሆና መኖር አትችልም የሚል ግምት ሲያራምዱ ይደመጣል፤ ይህ ከትግራይ ጀርባ “አይዞሽ፤ አለንልሽ” የሚሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ስለመኖራቸው ካለመገንዘብ የሚመጣ ዕሳቤ መስሎ ይታየኛል። ለምሣሌ ትግራይ ሀገር መሆኗ ይቅርና በኮንፌደሬሽን እንኳን ብትዋቀር ለአሜሪካ ልክ ጂቡቲ እንዳደረገችው የጦር ቤዝ ብትሰጥስ? ወይንም ከግብፅ ጋር ድርድር ተደርጎ ትግራይ ውስጥ የግብፅ ጦር ቤዝ ቢያገኝሳ? ግብፅ ትግራይ ውስጥ እግሯን አስገባች ማለት ራሺያ ቴክሳስ(አሜሪካ) ውስጥ ወታደራዊ ቀጠናን አቋቋመች እንደማለት ይቆጠራል…(በነገራችን ላይ አሜሪካ ውስጥ የቴክሳስ ስቴት የመገንጠል ጥያቄን እያነሳች እንደሆነ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን?…Texit: Why and How Texas Will Leave The Union, Daniel Miller, Griffing John 2018 መፅሐፍ ማንበብ ይቻላል)
  ለመሆኑ ራሺያ ቴክሳስ ውስጥ ወታደራዊ ቀጠናን ብታደራጅ የአሜሪካ ምላሽ ምን ይሆን? እንኳን ቴክሳስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ራሺያ የጦር ቤዝ ብታደራጅ አሜሪካ ምላሿ ቀላል አይሆንም። ግብፅም በስመ ልማትና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እግሯን ትግራይ ውስጥ ካስገባች ኢትዮጵያ በቀጠናው ደህንነቷን የማስጠበቅ አማራጭ መጠቀም ግዴታዋ ነው።
    ስለዚህም መንግስት የሕወሓቶችን ሁሉንም ዓይነት “scenarios” ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ ማጤን አለበት። የሕወሓት ሰዎችን በተለይም የጄኔራል ፃዲቃንና የደብረፂዮንን ንግግሮች በሚገባ በመፈተሽ አካሄዳቸውን ከወዲሁ በመተንበይ ለቀጣይ እንቅስቃሴዎች አቅጣጫን መተለም  አንድምታዎች!
Filed in: Amharic