>

አንተ ወንድሜ ነህ ( ዘምሳሌ)

አንተ ወንድሜ ነህ

    ዘምሳሌ


በሀገሬ መሬት በክንድህ ሸክፈህ
ከጎኔ የምትቆም ወገኔ ነው ብለህ
በናት ሀገር ምድር ህይወትህን ሰውተህ
ሞተህ የታደከኝ እራስ አሳልፈህ
ለሀገር ቃል ገብተህ
አመታት ያለፍከው እንደጧፍም ነደህ

አንተ ወንድሜ ነህ

በከሀዲው ምድር
በነውረኞች መንደር
አብሮ ያኗኗረህ ተንኮሉን በመቅበር
በጥቅም ታውሮ ተሸብቦ በዘር
ህሊናውን ሽጦ የሀገር ጦር ሲዳፈር

ለኢትዮጵያ የወገንህ
በሴረኞች ትብታብ ያልታሰረ ክንድህ
እራስ አሳልፈህ የምትኖር ላገርህ
በነፍሰገዳዩ ባንዳ የተከዳህ

በድንገተኛው ተኩስ
ቃልኪዳንህ ሳይፈርስ
ሀገርን ልታድን ለወገንህ ልትደርስ
የቆምከው ለሕዝብህ ያልሳሳኸው ለነፍስ

አንተ ወንድሜ ነህ
በዚያች ቀውጢ ሰዓት
ድንገተኛው ጠላት
ደርሶ ካደባበት
ካደርክበት ስፍራ ለርሱ ከሞትክበት
በመርዘኛ አቋሙ ሸፍጥ በተሞላበት
ባጎረስከው ፈንታ በተነከስክበት

በእንግዳው ፍጡር ሀገርን በከዳው
በሀገር አፍራሹ በወያኔ ጁንታው
ደም  ባንቀዠቀዠው
የሞት ጣዕር በያዘው
ገና ከጅምሩ በሕዝብ የተተፋው

የኢትዮጵያ  በሽታ
የሀገራችንም ፀር በየሁሉ ቦታ
በጠባብ አዕምሮ በጥጋብ ከፍታ
በለከት የለሹ ፉከራ ድንፋታ

ታግሰኽ የኖርከው
ዕድል የሰጠኸው
ባጎረስከው ፈንታ እጅ የተነከስከው
ለእምዬ ኢትዮጵያ  በፅናት የቆምከው

አንተ ወንድሜ ነህ
ምንግዜም ማትተወኝ
እኔም የማልተውህ
የኢትዮጵያ  ጀግና
ወደርም የሌለህ

የሀገሬ ወጥቶ አደር
ያለኸው በግምባር
ሆነህ የኛ ማገር
የምጠብቅ ድንበር
አንተ ወንድሜ ነህ – አንተ ወንድሜ ነህ!
ዘምሳሌ ግጥም
መታሰቢያነቱ ለኢትዮጵያ ሲሉ ለተሰዉትና
ለሚዋደቁት ወገኖቻችን !

Filed in: Amharic