>

"የኢትዮጵያን ችግር በውጪ ጣልቃ ገብነት መፍታት አይቻልም...!!;"  (የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደሮች)

የኢትዮጵያን ችግር በውጪ ጣልቃ ገብነት መፍታት አይቻልም…!!;”
የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደሮች
E B C

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ችግር በውጪ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ሊፈታ እንደማይችል እና መፍትሄው ከውስጥ መምጣት እንዳለበት የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ አምባሳደሮች አምባሳደር ቲቦር ናዥ እና አምባሳደር ዶናልድ ቡት ተናግረዋል።
አምባሳደሮቹ የዘር መከፋፈል ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር እንደዳረጋት ገልፀው ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን አቻችለው በአንድነትና በሰላም መኖር የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያና በጊኒ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና በትራምፕ አስተዳደር ረዳት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ቲቦር ናዥ እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ እና ዛምቢያ አምባሳደር የነበሩት ዶናልድ ቡት ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ ድምፅ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያውያን ለውጪ ሀይል ግፊት የማይንበረከኩ መሆናቸውን ማስተዋላቸውንና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚና ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማን እና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ቀውስ እንድትወጣ እያደረጉት ያለውን ጥረት ያደነቁት አምባሳደር ቡት፣ ኢትዮጵያውያን ግን ለውጪ ግፊት በቀላሉ እጅ አይሰጡም ብለዋል።
በዚህ የሚስማሙት አምባሳደር ናዥ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር የምትወጣው መፍትሄው ከራሳቸው ከኢትዮጵያውያን ሲመጣ ብቻ መሆኑን አስምረውበታል።
ሁለቱም የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች ከአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ካሮል ካስቲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሲተገበር የኖረው ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር መሰረት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የደርግን መውደቅ ተከትሎ ስልጣን የያዘው የህወሓት መንግስት ይህን ስርዓት ማምጣቱን ያስታወሱት ናዥ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ ስርዓት አለመስራቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ችግር የተባባሰው የፖለቲካ አመራሮች ከህዝቡ ድጋፍ ለማግኘት ዘርን መጠቀማቸው ነው ያሉት አምባሳደር ቡት በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተሞከረው ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት የታሰበውን ውጤት አለማምጣት ለዚህ ልዩነት መስፋፋት አስተዋፅኦ እንዳደረገ አስምረውበታል።
ከኢትዮጵያ ውጪ ያለው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለኢትዮጵያ መሆን አለበት ብለው የሚያስቡትን አቅጣጫ ከማዘጋጀት ይልቅ፣ ህዝቡ በራሱ ችግሮቹን መፍታት የሚችልበትን መንገድ በማመቻቸት ብቻ እንዲያግዝ ዲፕሎማቶቹ አሳስበዋል።
Filed in: Amharic