>
5:13 pm - Thursday April 19, 1032

የሀሳብ ነጻነት ለዘላለም ይኑር...!!! (ሸንቁጥ አየለ)

የሀሳብ ነጻነት ለዘላለም ይኑር…!!!

ሸንቁጥ አየለ

ኢትዮ 360 ን  የህዉሃት ሚዲያና ካድሬዎች  በዘርፍጅት አዘጋጅነት እየከሰሱ ነዉ። የአቢይ ቅልብ እና ድልብ ሚዲያና ካድሬዎች ደግሞ ኢትዮ 360ን ለወያኔ የሚሰራ ሚዲያ ነው የሚል ክሳቸዉን ያንቆረቁሩታል።
በተለይም የአቢይ አገዛዝ ኦህዴድ/ኦነግ ተባብረዉ በኦሮሚያ የሚጨፈጭፉትን የአማራ ህዝብ ብሶት የሚያነሱ ማናቸዉም ግለሰቦችን ሚዲያዎችን ህሊና ቢስ በሆኑ ከርሳም ካድሬዎቹ ሲቀጠቅጥ ይዉላል ያድራል።
ልክ ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ እኩል እንደሚወድ መንግስት ስለ ኢትዮጵያዊነት ይዘምራል። ሚሊዮን አማሮች ከኦሮሚያ አሁን ድረስ ሲጨፈጨፉና ሲያልቁ ግን ዉስኪ እየተራጨ ዳንኪራ ይመታል። ይሄ ሁሉ ወንጀላቸዉ እንዳይተነተን፡ ህዝቡን በመናፍቃዊ የፕሮፖጋንዳ ስልት አይኑን ጨፍነዉ የአማራን ነገድ አጠንፍፈዉ እስኪጨርሱ ሁሉም ሃገር እንዳይፈርስ ዝም ይበል ይላሉ።
 ሀሳብ የሌለዉ ማህበረሰ፡ የሚናገሩ ሰዎች የሌሉት ህዝብ ፡ የሚሞግቱና የሚከራከሩ የሚያነቁ ሰዎች የሌለዉ ህዝብ እንደ ከብት አፉኖ ታስሮ ታርዶ እንደሚያልቅ የሚያዉቁት ጥንተ ጠላቶቻችን አማራዉ እየታረደም ቢሆን ሀገር እንዳይፈርስ ዝም በሉ ይላሉ።
የሀሳብ ነጻነት ለዘላለም ይኑር።ኢትዮ360 ጻፍ ተናገር። ስለ ህዝባችን ጩህ። ህዝብ እየተከታተለ ነዉ። ለምሳችሌ እኔ ልክ ስራዬን ስጨርስ ማታ ላይ እስፖርቴን እየሰራሁ /ትሬድ ሚል ላይ እየሮጥሁ/ ኢትዮ 360 ምናለ ፕሮግራምን እከታተላለሁ። ሌሎች ቻናሎችንም ለማገናዘቢያ አደምጣለሁ።
ኢትዮ 360 ላይ አንድ የተለዬ ነገር ሀሳብ አለ። ሃብታሙና ኤርምያስ ልዩነት ሲኖራቸዉ ሁለቱም በመሰላቸዉ መልክ ሀሳባቸዉን ያቀርባሉ። የሀሳብ ልዩነት ወይም አንድነታቸዉ አይደለም ቁም ነገሩ። ዋናዉ ግን ሁለቱም ሀሳብ አላቸዉ። በማደምጥበት ጊዜ በሁሉም ሃሳብ እስማማለሁ ማለት አይደለም። በጣም የማይስማማኝን ሃሳብ በራሴ ፔጅ ላይ ለመግልጽ እሞክራለሁ።
እዚህ ላነሳዉ የሞከርኩት ግን አንድ ነገር ነዉ። የወያኔ እና የብልጽግና ሀሳብ ጠል ካድሬዎች ሀሳብ ስለሌላችሁ ሌሎች እንደናንተ ዝም እንዲሉ አትወትዉቱ። የሰዉ ልጅ የሀሳብ ነጻነት የሰዉ ልጅ ክቡርነት መገለጫ ነዉ። የሀሳብ ነጻነት ለዘላለም ይኑር።
ምርጡ የፖለቲካ ሰዉ ወይም ምርጡ የጦር መሪ መጀመሪያ የሚያደምጠዉ የሚተቹትን ግለሰቦች እና ሚዲያዎች ነዉ። ከነዚያ ይማራል፡ ይዘጋጃል፡ ሳይፈራም ቀርቦ ይከራከራል።ያሳምናል። ትችት ግን ኣይቆምምና ከቀጣይ ትችቶች ቀጣይ ትምህርቶችን ይቀስማል። የራሳን ሀሳበ በተችዎች ሀሳብ ይፈትነዋል። የሚያመነጨዉ ስትራቴጂም በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ይሆናል።
ኢትዮ 360 ዝም ብለህ ሃሳብህን አቅርብ። የሚማር ይማርበት። የሚማረር ይማረርበት። የሀሳብ ነጻነት ለዘላለም ይኑር።ሃሳብ መሸከም የማይችል ሀገር ከመፍረስ አይድንም። ሃሳብ የሚሸከም ሀገር ግን የመጨረሻዉ ጠንካራ ሃገር ሆኖ ይቀጥላል።
Filed in: Amharic